1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎ፦ የወርቅ ማፊያዎች

ሰኞ፣ ነሐሴ 29 2009

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገወጥ የወርቅ ንግድ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ጎረቤት ሃገራት ጦር ሠራዊት ጄነራሎች ይራኮታሉ። ጎስቋላ የሀገሪቱ ነዋሪዎች በቀን አብላጫውን ሰአት ጽልመት በዋጠው ጉድጓድ ውስጥ ለማሳለፍ ይገደዳሉ። የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በጭለማው ጉድጓድ ውስጥ ሲማስኑ በጨለማው ጉድጓድ መዋጣቸው የተለመደ ነው።

https://p.dw.com/p/2jEda
Afrika Kongo Goldgewinnung
ምስል picture-alliance/AP Phtoo/A. Sundaram

ጥልቅ በቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ኾነው ወጣቶቹ ወንዶች በያዙት መዶሻና አነስተኛ አካፋ አለታማዉ ግድግዳ ላይ ተጠምደዋል። 50 ሜትር ጥልቀት ባለው ዋሻ ውስጥ ጽልመት ነግሷል። አነስተኛ መብራት ከዋሻው መግቢያ ላይ ተንጠልጥላ ጭልጭል የሚል ብርሃን ታመነጫለች። ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ውስጥ በሚገኘው በዚህ ጠባብ ዋሻ የወርቅ ማዕድን ቆፋሪዎቹ በቀን ውስጥ እስከ ስምንት ሰአት ድረስ ለማሳለፍ ይገደዳሉ።

አንዲት ግራም የወርቅ ፍልቃቂ ለማግኘት 200 ኪሎ ግራም የአፈር ቁልል ዝቀው ማውጣት ይጠበቅባቸዋል። ታዲያ ጠባቡ ጉድጓድ በየጊዜው እየተደረመሰ ወጣት ቆፋሪዎቹን መቅበሩም የተለመደ ነው። በቀን ጥቂት ዶላሮችን ለማግኘት ሲሉ ወጣቶቹ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ያለመታከት ይቆፍራሉ። «የደቡባዊ አፍሪቃ ተፈጥሮ ሐብት ተመልካች» የተሰኘው ድርጅት ኃላፊ ክላውድ ካቤምባ «ተጠቃሚዎቹ ግን ሌሎች ናቸው» ይላሉ።

«የኮንጎ ወታደራዊ መኮንኖች እና ጀነራሎች፤ ሌላው ቀርቶ የጎረቤት ሃገራት ወታደሮች እና ጦር ሠራዊት አዛዦች ተሳታፊ መሆናቸው ለማንም ግልጽ ነው። የማይሳተፍ ማን አለ? ሌላው ቀርቶ የኮንጎ ፖለቲከኞች እና ሚንሥትሮች ሳይቀሩ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ጉድጓዶች አሏቸው። ምንም ሊያስደንቀን አይገባም።» 

Afrika Kongo Goldgewinnung Tagebau
ምስል GettyImages/R. Olson

የወርቅ ማዕድኑ ሽሚያ ላይ የተሠማሩት የኮንጎ ጦር ሠራዊት እና የአማጺያን አባላት በአካባቢው የሚፈጽሟቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለማጣራት ካሳይ ወደተባለው  አውራጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  ሁለት ባለሞያዎች አቅንተው ነበር። እንደ ባለሞያዎቹ ግኝት ከሆነ የወርቅ ቁፋሮው በደራበት አካባቢ ሰዎች ይታፈናሉ፣ በስውር ይገደላሉ በአጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቱ ልኩን ያጣ ነው። ከዚህ ሁሉ ግፍና በደል ጀርባ ግን እጁ ማን እንዳለበት ዛሬም ድረስ ለማንም ግልጽ አይደለም። ብቻ በወርቅ ማዕድን ቁፋሮ የማፊያ መሰል ተግባር ውስጥ መሳተፍ የማይሻ የለም።

«ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም፤ ሌላው ቀርቶ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችም በዚህ የማዕድን ማውጣት ንግድ መሰማራት ይሻሉ። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብ ማግኛ ብቸኛው የገቢ ምንጭ ይህ የወርቅ የማዕድን ማውጣት ተግባር ነው። ሁሉም በዚህ ተግባር መሳተፍ ይሻል። ሌላ የገቢ ምንጭ ሊያስገኝ የሚችል ነገር የለም።»

ቁጥጥሩ በላላበት የኮንጎ የወርቅ ማዕድን ንግድ 98 በመቶው ወደ ውጭ ሀገር የሚላከው ወርቅ ዝውውሩ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 በተደረገ ጥናት ከወርቅ ንግድ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን 345 ሚሊዮን ዩሮ አጥታለች። እንደው በሕገወጥ መንገድ ከተሰወረው ከዚያ ሁሉ ሚሊዮን ዩሮ ለአመል ያህል ተነስቶለት 6,7 ሚሊዮን ለመንግሥት ቢገባ ኖሮ ኅብረተሰቡ ትምህርት ቤቶች፣ ሐኪም ቤቶች እና መንገዶች በተገነቡለት ነበር።  

Afrika Kongo Goldgewinnung Tagebau
ምስል GettyImages/R. Olson

የእርስ በእርስ ጦርነት እና ግጭት ለዘመናት በነገሰበት የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሁሉም ከውጥንቅጡ አትርፎ መውጣትን ይሻል። ሙስና እንዲሁም ድህነት ነዋሪውን ይገዘግዛል፤ ጦሩና ባለሥልጣናቱ ደግሞ ከወርቅ ቁፋሮው ጀርባ ጎስቋላውን ነዋሪ ይደቁሳሉ።  ለህዝቡ የሚሠራ መሪ ጠፋ ይላሉ ክላውድ ካቤምባ።

«ለኮንጎ ሕዝብ የሚባልትል ጠንካራ መሪ ያስፈልጋል። የሕዝቡን ፍላጎት የሚረዳ፣ ለለውጥ የተጋ መሪ ያስፈልጋል። አዲስ አስተሳሰብን ይዞ ብቅ የሚል መሪ፤ በፖለቲካውም በወታደሩም ሰፈር ያሻል።»

ዛሬም ግን በብዙዎቹ አፍሪቃ ሃገራት እንደሚታየው ሁሉ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክም ጥቂቶች በሕገወጥ መንገድ በቀላሉ በብልጽግና ይመነደጋሉ። አብዛኛው ነዋሪ ግን የእለት ጉርሱን ለማግኘት መሪር ሕይወትን ይገፋል።

ግዌንዶሊን ሒልሰ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ