1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎ፣ ግፊት ወይስ ዲፕሎማሲ

ረቡዕ፣ ሰኔ 29 2008

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ በቅርቡ የስልጣን ዘመናቸው በይፋ ያበቃል። እንዲያም ሆኖ ግን ከስልጣን የመሰናበት እቅድ ያላቸው አይመስልም።

https://p.dw.com/p/1JKEq
Joseph Kabila
ምስል AFP/Getty Images/A. Wandimoyi

[No title]

በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ውጥረት ይታያል። የውጭ ሀገራት መንግሥታትም ቢሆኑ በካቢላ ርምጃ ቅር ተሰኝተዋል። ይሁንና፣ በካቢላ ወይም በመንግሥታቸው ላይ ቢያንስ እስከ ጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ ግፊት ከማሳረፍ ተቆጥበዋል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ በቅርቡ የስልጣን ዘመናቸው በይፋ ያበቃል። እንዲያም ሆኖ ግን ከስልጣን የመሰናበት እቅድ ያላቸው አይመስልም። በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ውጥረት ይታያል። የውጭ ሀገራት መንግሥታትም ቢሆኑ በካቢላ ርምጃ ቅር ተሰኝተዋል። ይሁንና፣ በካቢላ ወይም በመንግሥታቸው ላይ ቢያንስ እስከ ጥቂት ጊዜ በፊት ድረስ ግፊት ከማሳረፍ ተቆጥበዋል። ዩኤስ አሜሪካ በዴሞክራቲክ የኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት የቅርብ እና ታማኝ አገልጋይ በሚባሉት የመዲናይቱ ኪንሻሳ የፖሊስ ኃላፊ ሴሌስተ ካንያማ ላይ ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት ማዕቀብ ጥላለች። ማዕቀቡ አንድም አሜሪካዊ ከሴለስተ ካናያማ ጋር የንግድ ግንኙነት እንዳያደርግ ይከለክላል፣ ካያንማ በዩኤስ አሜሪካ ሳይኖራቸው አይቀርም የሚባለው ንብረታቸውም እንዳይንቀሳቀስ ያግዳል። ዩኤስ አሜሪካ በዚሁ የማዕቀብ ውሳኔዋ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክን መንግሥት፣ በተለይም፣ የሴለስተ ካያንማን የኃይል እና የጭቆና አገዛዝ ማውገዟን እንዳሳየ የዩኤስ አሜሪካ የገንዘብ ሚንስቴር አስታውቋል። የፖሊስ ኃላፊው ካያንማ ከሚወቀሱባቸው የመብት ጥሰቶች መካከል በተለይ እጎአ በ2015 ዓም በኪንሻሳ በፕሬዚደንት ካቢላ አንፃር በተካሄዱ ተቃውሞዎች ወቅት በፀጥታ አስከባሪዎች እና በተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ፖሊሶች በኃይል ተግባር የበተኑበት ይጠቀሳል፣ በዚሁ የፖሊስ ርምጃ ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ነበር የተገደሉት።

USA Washington Afrika Gipfel 4.8.2014
ምስል picture-alliance/AP

ይሁን እንጂ፣ ምንም እንኳን የኪንሻሳ ፖሊስ ኃላፊ የዩኤስ አሜሪካ ማዕቀብ ዋነኛ ዒላማ ቢሆኑም፣ አንድ የፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ታማኝን መንካቱ ለራሳቸው ለኮንጎ ርዕሰ ብሔር የተላለፈ ግልጽ መልዕክት ሆኖ ታይቶዋል። በምህፃሩ «ዴ አ ኤስ» በመባል የሚታወቀው የጀርመን እና አፍሪቃ ተቋም ዋና ጸሐፊ እና የኮንጎ አጥኚ ኢንጎ ባዶሬክ እንዳስረዱት፣ ምዕራቡ ዓለም በአንድ ወቅት በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክን መረጋጋት ሊያወርዱ ይችሉ ይሆናል በሚል ተስፋ ጥሎባቸው የነበሩትን ካቢላ በአሁኑ ጊዜ ቀና አመለካከት ነፍጓቸዋል።

« ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ እና መንግሥታቸው የኮንጎ ሕዝብ እና የውጭው ዓለም ከነርሱ የጠበቀውን ተግባር ባለማሟላታቸው ብዙ ሰዎች ቅር የተሰኙ ይመስለኛል። ልክ እንደ ብዙዎቹ አፍሪቃውያን ርዕሳነ ብሔራት ካለፉት ዓመታት ወዲህ ይበልጡን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በመከተል ተቃዋሚዎችን እና የመገናኛ ብዙኃንን ጨቁነዋል። »

የፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን የፊታችን ታህሳስ፣ 2016 ዓም ስለሚበቃ ሕዝቡ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ፣ የቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዕለት እስካሁን ፣ገና አልተወሰነም። ይህ በተቃዋሚ ቡድኖች እይታ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው። ምክንያቱም፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ሕገ መንግሥታዊ ው ፍርድ ቤት ባለፈው ሚያዝያ ወር ባሳለፈው ውሳኔ፣ ፕሬዚደንታዊው ምርጫ እንደተመደበለት የፊታችን ህዳር ወር ካልተካሄደ፣ ፕሬዚደንት ካቢላ ሀገሪቱን በተጠባባቂነት ሊመሩ እንደሚችሉ አስታውቋል። እጎአ በ2012 ዓም ሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት ፕሬዚደንቱ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን የመወዳደር እቅድ ይኑራቸው አይኑራቸው እስካሁን ባይናገሩም፣ ብዙ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ሕዝብ መወዳደራቸው እንደማይቀር መገመቱን ገልጾዋል። በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሰረት፣ አንድ ፕሬዚደንት ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ ሀገሪቱን መምራት አይችልም።

ለወትሮው ክፍፍል የሚታይባቸው 16 የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ተቃዋሚ ቡድኖች አንድ « ጂ ሰባት» የተባለ ህብረት ፈጥረው ፣ በመፀው ወራት ይደረጋል ተብሎ በሚታሰበው ቀጣዩ ምርጫ ላይ የቀድሞ የካታንጋ ግዛት አስተዳዳሪ ሞይዜ ካቱምቢ ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ በስልጣን ላይ በሚገኙት በፕሬዚደንት ካቢላ አንፃር በዕጩነት ቀርበው እንዲወዳደሩ ሰይመዋቸዋል። ይሁንና፣ የሀገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ምርጫውን ለማዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ተናግሮዋል።

Moise Katumbi Chapwe Kongo
ሞይዜ ካቱምቢምስል Getty Images/F. Scoppa

የካቱምቢ ዕጩነት ገና በይፋ ባይረጋገጥም፣ የ51 ዓመቱ ባለተቋም እና የቀድሞው በማዕድን የታደለው የካታንጋ አስተዳዳሪ በምርጫው የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ስላካባቢው በቅርብ የሚከታተሉት በስዊትዘርላንድ የዙሪኽ ዩኒቨርሲቲ መምህር ክሪስቶፍ ፎግል ግምታቸውን ሰጥተዋል።

« ካቱምቢ የካታንጋን ግዛት በተሳካ ሁኑታ በማስተዳደራቸው ብዙ ሞገስ አግኝተዋል። ብዙ ባለወረቶች ወዳካባቢው በመምጣት፣ በተለይ፣ በማዕድን ማውጣቱ ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረጉ ላይ ሰፊ ድርሻ አበርክተዋል። »

ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ መንግሥት ጠቅላላ ገቢ መካከል ከግማሽ የሚበልጠው የሚገኘው በደቡብ ምሥራቃዊ ኮንጎ ካለው የካታንጋ ግዛት ነው፣ ያም ቢሆን ግን፣ ገንዘቡ በአካባቢዎቹ መካከል በሚከፋፈልበት አሰራር ላይ ከማዕከላዩ መንግሥት ጋር ንትርክ መፈጠሩ አልቀረም። በዚህም የተነሳ፣ ማዕከላዩ መንግሥት የሀገሪቱን ግዛቶች እጎአ መስከረም 2015 ዓም ላይ እንዳዲስ በማዋቀር፣ 11 የነበሩትን ግዛቶች ወደ 26 አሳደገ፣ ካታንጋንም በዚሁ ጊዜ በአራት አካባቢዎች በመከፋፈል፣ ሞይትዜ ካቱምቢን ከግዛቱ አስተዳዳሪነት ስልጣናቸው አነሳ። በዚሁ ጊዜ ነበር ካቱምቢ ከገዢው ፓርቲ በመውጣት የተቃዋሚውን ጎራ የተቀላቀሉት።

Kupfermine Kongo
ምስል AFP/Getty Images

ካታንጋግን ቢከፋፈልም፣ በኮንጎ የስልጣን ሽኩቻ ላይ ዛሬም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በዚሁ አካባቢ ወደ 5,000 የሚጠጋ ሕዝብ ባለፈው ሚያዝያ ወር አደባባይ በመውጣት ፕሬዚደንት ካቢላ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንዳይወዳደሩ ባሳሰበበት ጊዜ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን በሚያስለቅስ ጋዝ ነበር የበተነው።

በኮንጎ በመንግሥቱ እና በተቃዋሚዎች መካከል ውጥረቱ እየተካረረ ቢሄድም ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እጎአ በ2006 ዓም ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመረጡበት ጊዜ አንፃር ፣ አሁን ጣልቃ ከመግባት ወደኋላ እንዳለ ይገኛል። በዚያን ጊዜ 2,000 የአውሮጳ ህብረት ወታደሮች ለምርጫው ሂደት ዋስትና ሰጥተዋል። የምርጫውን ወጪ የሸፈነውም የተመድ የልማት መርሀግብር መስሪያ ቤት ነበር። የታወቁ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችም ምርጫውን በቅርብ ነበር የተከታተሉት። አንዳንድ ታዛቢዎች ምዕራቡ ዓለም ይህ ዓይነቱን ትኩረት ቢሰጥ መልካም እንደሆነ ይናገራሉ። የጀርመናውያኑ ዕለታዊ «ታገስሳይቱንግ» የአፍሪቃ ጉዳይ ተከታታይ ጋዜጠኛ ዶሚኒክ ጆንሰን ኮንጎ በጀርመናውያኑ ፖለቲካ ችላ እንደተባለች እንደሚሰማው ገልጾዋል። በጀርመን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ ጌኦርግ ሽሚት ይህን የጆንሰንን አመላካከት የተሳሳተ ሲሉ አጣጥለውታል።

Kongo Steinmeier Joseph Kabila Kabange
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

« በተለይ፣ በኮንጎ የተለያዩትን ቀውሶች ለማብረድ የተሰማራውን ትልቁን የተመድ ተልዕኮ ስመለከት፣ ይህን አስተያየት አልጋራም። ጀርመን ለኮንጎ በያመቱ 260 ሚልዮን ዩሮ የልማት ርዳታ ድጋፍ ታደርጋለች። እና፣ ምንም አታደርጉም፣ አንዳችም ርምጃ ሳትወስዱ ማየት ብቻ ነው መባሉን ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም። »

እርግጥ፣ ጀርመን፣ ልክ እንደ ሌሎቹ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ለዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ ዘዴ መፍትሔ ማፈላለጉን እንደምታስቀድም ጀርመናዊው ዲፕሎማት ጌኦርግ ሽሚት ገልጸዋል። እርግጥ፣ ለኮንጎ ውዝግብ ተጠያቂ በሚባሉት ላይ ማዕቀብ የመጣሉን ጉዳይ በተመለከተ የአውሮጳ ህብረት መወያየቱ አልቀረም፣ ግን፣ የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ ህብረቱ ይህን ዓይነቱን ርምጃ መውሰዱ አብዝቶ ያጠራጥራል።

በኮንጎ ውጥረቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲ ብቻውን በቂ አይደለም የሚሉት ወገኖች በወቅቱ የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ እየቀነሰ እንደመጣ ይሰማቸዋል። የጀርመናውያኑ ሳምንታዊ መጽሔት፣ «ዴር ሽፒግል» ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ፕሬዚደንት ካቢላ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ባለፈው ዓመት 2015 ኮንጎን በጎበኙበት ጊዜ፣ በጀርመን እና በኮንጎ መካከል የቀጠለውን ትብብር እንደሚያደንቁ ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደማይፈልጉ ግልጽ እንዳደረጉላቸው ጽፎዋል። በአሁኑ ጊዜ በተለይ የተፈጥሮ ሀብት ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚፈልጉት ቻይና እና ሩስያ በወቅቱ ዋነኞቹ የአፍሪቃ የንግድ አጋሮች ሆነዋል። እጎአ ከ2006 ዓም ወዲህ አውሮጳውያኑ በአፍሪቃ የሚያደርጉት ታታሪነት እየቀነሰ መምጣቱን «ዴ አ ኤስ» በመባል የሚታወቀው የጀርመን እና አፍሪቃ ተቋም ዋና ጸሐፊ እና የኮንጎ አጥኚ ኢንጎ ባዶሬክ አስረድተዋል።

« በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ የሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ለየት ያለ ነው። ከብዙ አሰርተ ዓመታት ዓለም አቀፍ ርዳታም በኋላ የተወሳሰቡትን የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ችግሮች ማብቃት አልተቻለም። እና አፍሪቃውያኑ ወይም የኮንጎ ዜጎች ለችግሮቻቸው ራሳቸው መፍትሔ ያፈላልጉለት ወደሚለው ደረጃ ላይ ትደርሳለህ። »

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ