1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወቀሳ እና ዶይቼ ቬለ

ረቡዕ፣ የካቲት 6 2005

ዶይቼ ቬለ በሚያቀርባቸዉ ዘገባዎች ከጀርባ የተፅዕኖ እጅ አለበት የሚል መልዕክት ያዘለ ፅሁፍ ሠሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ በሆነዉ ፌስ ቡክ ተሠራጭቷል። ወቀሳዉ በሪያድ ባለፈዉ ሳምንት የተደረገ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በዶይቼ ቨለ አለመዘገቡን ከመግለፅ በተጨማሪ የቴክኒክ እክል ስለገጠመዉ ዘገባም የበኩሉን ድምዳሜ ወስዶ ዶቼ ቬለን ይተቻል።

https://p.dw.com/p/17d2m
ምስል DW

በሳዉዲ አረቢያ የሪያድና አካባቢዉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር ፃፈዉ የተባለዉ ይኸዉ መልዕክት ዶይቼ ቬለ በተለይ ሁለት ጉዳዮችን በትክክል አልዘገበም ወይንም አልፏቸዋል በማለት ይወቅሳል። ከተጠቀሰዉ ዘገባ አንዱ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ ሪያድ ዉስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን የቦድን ሽያጭ ለማካሄድ በሞከሩበት ወቅት እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ያቀረቡትን ጥያቄና ያሰሙትን ተቃዉሞ ዶይቼ ቬለ አልዘገበም የሚል ነዉ። ዶቼ ቬለ ከስፍራዉ ይኽ ተቃዉሞም ይሁን ስብሰባ እንደሚደረግ አስቀድሞ የደረሰዉ ጥቆማ የለም። ስብሰባዉ ወይም ተቃዉሞዉ ከተደረገ በኋላ ግን ጉዳይ የሚገልፅ ተንቀሳቃሽ ምስል በአንዳንድ ድረገፆች ላይ ለመመልከት ተችሏል። ወቀሳዉን በተመለከተ ጄዳ የሚገኘዉ ወኪላችን ነብዩ ሲራክን ጠይቀነዉ፤ በበኩሉ መረጃዉ ቀድሞ ቢደርሰዉም ጉዳዩን የጠቆሙት ወገኖች ግን ስለሁኔታዉ በድምፅ ሊያብራሩለት ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ነዉ የገለፀልን።

Rundfunkstudio bei der Deutschen Welle in Bonn
ምስል DW

ነብዩ ሲራክ ለዶይቼ ቬለ በትርፍ ሰዓት ወኪልነቱ በስዑድ አረብያ ብቻ ሳይሆን በየመን፤ በግብፅ በጥቅሉ በመካከለኛዉ ምስራቅ የሚከናወኑ አካባቢያዊ ዓለም ዓቀፋዊና የኢትዮጵያዉያንን ጉዳይ እየተከታተለ የሚዘግብ ጋዜጠኛ ነዉ። ይህን ተግባሩንም ለማከናወን አስቸጋሪ እንቅፋቶች ከየአቅጣጫዉ እንደሚገጥሙት ይገልፃል። ሌላዉ በዚህ ፅህፍ የተሰነዘረዉ ትችት በዕለተ ዓርብ ከአዲስ አበባ የደረሰንን ዘገባ ይመለከታል። ወኪላችን ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር በላከዉ ዘገባ በርግጥም የድምፅ ጥራት ችግር ገጥሞታል። ያ ቴክኒካዊ እክል መሆኑን አስተዉለን ለዚህም ይቅርታ ጠይቀናል። ነገር ግን መተላለፍ ከሚገባዉ መልዕክት የተዛነፈ እንዳለሌለ መግለጽ እንወዳለን። ወቀሳ ያዘለዉን ፅሁፍ በፌስ ቡክ ገፃቸዉ የለጠፉ ወገኖችን ከጄዳም ከቦንም ለማግኘት ከትናንት ጀምሮ ጥረት አድርገናል።

Deutsche Welle in Bonn
ምስል DW

በኢሜልም ይህን መረጃ ገፃቸዉ ላይ ከለጠፉት አንዱን ግለሰብ ለማግኘት የኢሜይል መልዕክት ላክን እስካሁን ያገኘነዉ ምላሽ የለም። ዙባየር በሚል ስም በፌስ ቡክ የፊታችን ሀሙስም ሳዉዲ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዉን የሰደቃ ድግስ መዘጋጀቱን ያስታዉቁ አንድ ግለሰብ በዚህ ዝግጅት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን የኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊሞች ላይ የሚያደርሰዉን በደል እንዲያቆም ይጠይቃሉ የሚል ማስታወቂያቸዉን ተመልክትን። የስልክ አድራሻቸዉን በመጠየቅ ከዚህ የደወልንላቸዉ እኝህ ሰዉ አቶ ዑመር እንደሚባሉ ገለፁልን እና በሳዉዲ አረቢያ የሪያድና አካባቢዉ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ማኅበርን አድራሻ ጠይቀናቸዉ፤ እሳቸዉም ስለማኅበሩ የሚያዉቁት እንደሌለና እንደዉም እሳቸዉም መጣት እንዳልሆኑ ነዉ የገለፁልን። ሪያድ የሚኖሩ ሌላ አንድ አድማጭን ትብብር ጠየቅን ስለተባለዉ ማኅበር በወሬ ደረጃ እንጂ ስለአባላቱ እንደማያዉቁ ገለፁልን። ዶይቼ ቬለ የሚያቀርባቸዉ ዘገባዎች ተዓማኒነታቸዉ ተረጋግጦ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉም በተቻለ መጠን ተጠይቀዉ እንጂ በዘፈቀደ እንደተገኘ እንዳልሆነ፤ ለሙያ ስነምግባርም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ግልፅ ማድረግ ይወዳል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ