1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ሃገራቸው የሚመለሱ የኮሶቮ ስደተኞች እና ችግራቸው

ሐሙስ፣ ጥቅምት 18 2008

እጅግ ብዙ የኮሶቮ ዜጎች በአሁኑ ጊዜ ሃገራቸውን እየለቀቁ በጀርመን ተገን ይጠይቃሉ። ይሁንና፣ የተገን ማመልከቻቸው ኮሶቮ አስተማማኝ ሃገር ናት በሚል ተቀባይነትን ስለማያገኝላቸው ወደትውልድ ሃገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው። በዚሁ ጀርመን በምትወስደው ርምጃ ተመላሾቹ የኮሶቮ ዜጎች በትውልድ ሃገራቸው ለትልቅ ችግር ተጋልጠዋል።

https://p.dw.com/p/1Gwgo
Bildergalerie Flüchtlingsunterbringung in Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa/D. Endlicher

[No title]

እአአ በ2008 ዓም ነፃነቷን ያገኘችው የንዑሷ ሃገር ኮሶቮ ብዙ ሕዝብ በወቅቱ ሃገር እየለቀቀ ነው። እአአ በ2015 ዓም መጀመሪያ ላይ እስከ 150,000 የኮሶቮ ዜጎች ወደ አውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት የገቡ ሲሆን፣ ባለፈው ጥር ወር ብቻ 3,630 ኮሶቮ ተወላጆች ነበሩ ጀርመን ውስጥ ተገን የጠየቁት። ይሁንና፣ ባለፉት ወራት ከሶርያ የርስበርሱን ጦርነት በመሸሽ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሶርያ ዜጎች በገቡበት ምክንያት በተፈጠረው ግዙፍ ችግር የኮሶቮ ዜጎች የተገን ማመልከቻ ማስገባት እንኳን እንዳልቻሉ፣ የቻሉትም ኮሶቮ አስተማማኝ ሃገር ተብላ በምትታይበት ሁኔታ የተነሳ ማመልከቻቸው ውድቅ መሆኑን አንዱ ተገን ጠያቂ የሆነው ኔቅሜዲን አስረድቶዋል።

« ኮሶቮ ውስጥ ጦርነት የለም በሚል ምክንያት ተገን እንደማይሰጠን ነው የነገሩን። ባጭሩ ሃገር አላችሁ ነው ያሉን።»

Karte Von Deutschland als sicher eingestufte Herkunftsländer Englisch

ባለፉት ወራት ብቻ ወደ 15,000 የሚጠጉ የኮሶቮ ዜጎች ከአውሮጳ ህብረት አብል ሃገራት ተባረዋል። ኔቅሜዲን የመሳሰሉ ተመላሾች ትልቅ ችግር ላይ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት፣ በተለይ መሸት ሲል ብርዳማ በሆነው ተራራማው የሰሜን ኮሶቮ አካባቢ የሚገኘው ኔቅሜዲን ለመኖር ያህል ካልሆነ በስተቀር ለቤት ማሞቂያ የሚያስፈልገውን ከሰል መግዣ እንኳን እንደሌለው ገልጾዋል።

« የምኖረው ወንድሜ ቤት ነው። ሁለት ልጆች አሉኝ፣ ወንድሜ ነው ምግባችንን እና ለኑሮ የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚችለን ወንድሜ ነው፣ እኔ ምንም ነገር የለኝም። »

የኮሶቮ መንግሥት ለተመላሾቹ መዲናይቱ ፕሪሽቲና መዳረሻ ላይ አንድ የማቆያ ማዕከል ከፍቶዋል፣ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ወደ ህብረቱ ሃገራት ላደረጉት የጉዞ ወጪ መሸፈኛ ሲሉ ቤታቸውን ሸጠዋል። ፋሪየ ቴርናቫ ሼሬሜንዲ በሃገር አስተዳደር ሚንስቴር ውስጥ ተመላሾቹን የኮሶቮ ዜጎች እንደገና በህብረተሰቡ ውስጥ መልሶ ለማዋኃድ የተከፈተው ክፍል ኃላፊ ናቸው።

« ማዕከሉ እስከ 25 ሰዎች መቀበል ይችላል፣ ሆኖም ግን፣ ይህን ያህል ሰው እስካሁን ወደ ማዕከሉ አልመጣም፣ ምክንያቱም፣ እኛ አገልግሎት የምንሰጠው ረዘመ ከተባለ ለሰባት ቀናት ብቻ ነው። ሰራተኞቻችን ተመላሾቹ ለገጠማቸው የመኖሪያ ቤት ችግራቸው ቀድሞ ይኖሩበት በነበረው አካባቢ ወደሚገኘው የከተሞች አስተዳደር በመሄድ መፍትሔ ያፈላልጋሉ። »

Flüchtlinge Kosovo Balkan Deutschland Hamburg
ምስል picture-alliance/dpa/Daniel Reinhardt

የኮሶቮ መንግሥት በአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ያቀረቡት የተገን ማመልከቻቸው ውድቅ ሆኖ ወደ ትውልድ ሃገራቸው የተመለሱ ዜጎቹን ለመርጃ ባሁኑ ጊዜ 3,2 ሚልዮን ዩሮ መድቦዋል። ይሁን እንጂ፣ ጀርመን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኮሶቮ ዜጎችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ዕቅድ እንዳላት ማስታወቋ ሲታሰብ ይኸው የተመደበው ገንዘብ በጣም ንዑስ እና እዚህ ግብ የማይባል ሆኖ ነው የተገኘው። ቴሬዛ እና ሁለት ልጆችዋ ከስዊድን ነው የተባረሩት።

« ከተመለስን አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ሆኖናል። እስካሁን አንዳችም ርዳታ አላገኘንም። ምንም ገንዘብ የለንም። ኮሬንቲ ፣ ምን አለፋህ፣ ለኑሮ የሚያስፈልገው ሁሉ የለንም። »

የኮሶቮ ዜጎች ሃገራቸው አስተማማኝ ብትባልም ፣ ሰርተው ሕይወታቸውን መምራት የሚችሉበት ብሩሕ የወደፊት ዕድል በማጣታቸው ፣ ወደበለፀጉት የምዕራብ አውሮጳ ሃገራት መሰደዳቸውን አሁንም እንደቀጠሉ ነው፣ ምንም እንኳን በዚያ የመቆየት ዕድላቸው ንዑስ ቢሆንም።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ