1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዋሚዎች ተጓዦችን አስወርደው አራት አውቶቡሶችን ደብድበዋል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19 2010

ዓመታዊዉን የቅዱስ ገብርኤል በዓል የሚከብሩ ምዕመናንን አሳፍረው ከአዲስ አበባ ወደ ቁልቢ ይጓዙ የነበሩ አራት አዉቶብሶች ትናንት አሰበተፈሪ አጠገብ አርበረከቴ ሲደርሱ በአካባቢዉ ነዋሪዎች መደብደባቸውን የተመድ አስታወቀ። ድርጅቱ ለሰራተኞቹ በሚያሰራጨዉ የደሕንነት ማስጠንቀቂያ እንዳለዉ አደጋዉ የደረሰባቸው አዉቶብሶች የሠላም ባስ ኩባንያ ነበሩ።

https://p.dw.com/p/2q4OY
Karte Äthiopien englisch

አዉቶቡሶች በድብደባ መስታወታቸዉ ተሰባብሯል፤

የቁልቢ ገብርኤልን አመታዊ በዓል የሚከብሩ ምዕመናን አሳፍረዉ ከአዲስ አበባ ወደ ቁልቢ በመጓዝ ላይ በነበሩ አውቶቡሶች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል ተባለ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሰራተኞቹ ባሰራጨው የጸጥታ ማስጠንቀቂያ ማስታወሻ እንደገለጠው አውቶቡሶቹ በተቃዋሚዎች ጥቃት የተፈጸመባቸው ጭሮ አቅራቢያ በምትገኘው አርባረከቴ ከተማ አዉራ መንገድ ላይ ነው።

ተቃዋሚዎቹ መንገደኞቹን በማስወረድ አራቱን አውቶቡሶች በድንጋይ መደብደባቸውን እና የአብዛኞቹ መስታወቶች መውደማቸውን ማስታወሻው ገልጧል። በመረጃው መሰረት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ተቃዋሚዎቹ አውቶቡሶቹን በእሳት ከማጋየታቸው በፊት ወታደራዊ ኃይል ደርሶ እንደበተናቸውም አትቷል።

አውቶቡሶቹ በወታደራዊው ኃይል ታጅበው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል ተብሏል።ሰላም ፤ ስካይ እና ኢትዮ ባስ ከተባሉት ውጪ ሌሎች በነፃነት ይጓዙ እንደነበር ይኸው ማስታወሻ አትቷል። ሶስቱ የሕዝብ ማመላለሻ ኩባንዮች የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት ንብረቶች ናቸው በሚል ለጥቃት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሰራጨው ማስታወሻ የመረጃ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ አትቷል። 

ቁልቢ ደርሶ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰዉ ባልደረባችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር እንደሚለዉ ደግሞ አዲስ አበባን ከሐረር እና ድሬዳዋ ጋር የሚያገናኘዉ መንገድ ዛሬም ዉጥረት እና ሥጋት እንደሰፈነበት ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ዮሐንስን ዛሬ ከቀትር በኋላ በስልክ አነጋግሮት ነበር።

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ነጋሽ መሐመድ