1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮዮጵያውያን ችግር

ማክሰኞ፣ መጋቢት 4 2010

የመከላከያ ሰራዊት በሞያሌ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ተፈናቃዮች ቁጥር መጨመሩ ተነገረ :: በኬንያ ሰባት የተለያዩ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች የሰፈሩት ተፈናቃዮችም በተለይም ሕጻናት ከፍተኛ የመጠለያ የአልሚ ምግብ እና የህክምና አገልግሎት ችግር እንደገጠማቸው አስታውቀዋል ::

https://p.dw.com/p/2uGcD
Mitarbeiter des Roten Kreuzes transportieren die Leichen der bei dem Anschlag im Paradise Hotel in Kikambala ums Leben gekommenen Personen ab
ምስል AP

ወደ ኬንያ የተሰደዱ ኢትዮዮጵያውያን ችግር

 

የኬንያ የቀይ መስቀል ማህበር ጽህፈት ቤት በበኩሉ የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የሚፈልሱ ተፈናቃዮች በተለያዩ የኬንያ ቀበሌዎች ተሰበጣጠረው መገኘታቸው ማህበሩ በሚሰጠው የግብረሰናይ አገልግሎት ላይ ተጽእኖ አሳድሮብኛል ብሏል :: የማህበሩ ጸሃፊ ሚስተር አባስ ጉሌት የተፈናቃዮቹን ጉዳይ እና አያያዝ በተመለከተም የኬንያ መንግስትን ውሳኔ እየጠበቅን ነው ሲሉ ለዶቼቨለ ገልጸዋል ::

በደቡብ ኦሮምያ ክልል በቦረ ዞን ሞያሌ ከተማ ባለፈው ቅዳሜ የመከላከያ ሰራዊት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አካባቢው እስካሁን መረጋጋት አልቻለም :: የኮማንድ ፖስት አካባቢውን ለማረጋጋት በሚል ሰበብ በርካታ ሰዎችን ማሰር መጀመሩም እየተነገረ ነው :: ጥቃቱን እና በመንግስት ኃይላት እየተወሰደ ያለውን የማሰር እርምጃ ተከትሎ የከተማዋ እንቅስቃሴ የስራ እና የንግድ አገልግሎቱ መቀዝቀዙንም የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ :: ቀደም ሲል ለደህንነታቸው ስጋት ያደረባቸው በሞያሌ የጫሙቅ ሸዋ በር እና አርበሌ ነዋሪዎች በብዛት ድንበር አቋርጠው መፍለሳቸው ሲታወቅ ስጋቱ ወደ ሌሎችም ቀበሌዎች ተዛምቶ ወደ ኬንያ የሚፈልሱ ነዋሪዎችን ቁጥር እንዳሻቀበው ታውቋል ::  በመከላከያ ሰራዊት የፈጸመውን ጥቃት ሸሽተው ከሞያሌ ሸዋ በር ኬንያ ከገቡት እና ማህሙድ ኢሊ በሚባል የግለሰብ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል ያነጋገርናቸው በተለይም ህጻናት በመጠለያ ህክምናና እና አልሚ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ነው የገለጹልን ::

በኬንያ የቀይ መስቀል ማህበር ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አባስ ጉሌት የኢትዮጵያ ሞያሌን ድንበር አቋርጠው ወደተለያዩ የኬንያ መንደሮች በመግባት ላይ የሚገኙት ነዋሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ይናገራሉ :: ከኢትዮጵያ በመፍለስ ላይ የሚገኙት ሰዎች ኬንያ ውስጥ በተለያዩ ቀበሌዎች ተበታትነው የመስፈራቸው ጉዳይም ማህበሩ በሚሰጠውን የግብረሰናይ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ሃላፊው ለዶቸቨለ ገልጸዋል ::

Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

" ዛሬ ያደረግነው ጊዜያዊ ጥናት እንደሚያመለክተው የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከአምስት ሺህ በላይ ሆኗል :: ተፈናቃዮቹ ድንበር አቋርጠው ወደተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ኬንያ ሞያሌ መርሳቤት ሶሎሎ እና ሌሎች አምስት የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ተሰበጣጥረው የፈለሱበት ሁኔታ ማህበራችን በሚሰጠው ግብረ ሰናይ የተቀናጀ አገልግሎት ላይ እንቅፋት ፈጥሮበታል :: ያም ቢሆን በተቻለን አቅም ጊዜያዊ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የምግብ የውሃ እና የቁሳቁስ አገልግሎት ለተፈናቃዮቹ እየሰጠን ነው :: "

የኬንያ የቀይ መስቀል ማህበር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሚስተር ጉሌት ለኢትዮጵያውያኑ ተፈናቃዮች ማህበሩ ከሚሰጠው የግብረሰናይ አገልግሎት ጎን ለጎንም የስደተኞቹን ጉዳይ አያያዝ በተመለከተ የኬንያን መንግስት ውሳኔ እየጠበቅን ነው ብለዋል ::

" የተፈናቃዮቹን ጉዳይ አያያዝ እና መጻኢ ሁኔታ በተመለከተ ችግሩ እስኪረጋጋ በአካባቢው ይቆዩ አልያም ወደመጡበት አካባቢ ይመለሱ የሚለውን መወሰን የሚችለው የኬንያ መንግስት ነው :: በእኛ በኩል በተለይም ከመርሳቤት አስተዳደር ሃላፊዎች እና የስደተኞችን ጉዳይ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር ተነጋግረናል ውሳኔ እየጠበቅን ነው "

በሞያሌ የመከላከያ ሰራዊት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በከፈተው የተኩስ ጥቃት 10 ሰዎች ተገድለው 12 መቁሰላቸው ይታወሳል :: ንጹሃን ዜጎችን የገደሉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ቢገልጽም ኢሰብአዊነት የጎደለው ወንጀል ፈጻሚዎቹ ድርጊቱ በተፈጸመበት ኦሮምያ ክልል መደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እንዲታይ የኦሮምያ ክልል የከተማ እና ዞን አስተዳደር መጠየቁ ታውቋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ

ሸዋዬ ለገሠ