1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ 3 ሚሊዮን የጀርመን ወጣቶች ይሳተፋሉ

ዓርብ፣ መስከረም 12 2010

በመጪው እሁድ ጀርመን ውስጥ ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ጥሪ ከደረሳቸው ጀርመናውያን መካከል ሶስት ሚሊዮን ያህሉ ወጣት አዲስ መራጮች ናቸው።ለመሆኑ እነዚህ ወጣቶች ድምፅ ለመስጠት ይወጡ ይሆን ወይስ ምርጫውን ለትላልቆቹ ወይም ለወላጆቻቸው ይተውታል?

https://p.dw.com/p/2kSAr
Junge Menschen vor dem Reichstag in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/W.Kumm

የክርስትያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ«CDU»  በጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን ከተማ በሚገኝ አንድ ጥንታዊ አዳራሽ ውስጥ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የምርጫ ዘመቻውን ያካሂዳል።  በጣም ዘመናዊ እና ሁሉም ነገር ግልፅ ነው ትላለች ቺየኔ ቱርነር። በወረቀት የተሞላውን ክፍል ፍላጎት አድሮባት በትኩረት የምትመለከተው የበርሊን ከተማ ተማሪዋ ቱርነር ከጥቂት ወራት በፊት ነው 18 ዓመት የሞላት። እንደ ሌሎች ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች ዘንድሮ  ከሁለት ቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትመርጥ የምርጫ መጥሪያ ደርሷታል።  ጥያቄው ማንን ነው የምትመርጠው የሚለው ነው። ወጣቷ እንደምትለው በግልም ይሁን በትምህርት ቤት የፖለቲካ ነገር ከዚህ በፊት አሳስቧት አያውቅም። « በ 17 እና 18 ዓመት ምርጫ መሄድ መቻል ከባድ ይመስለኛል።  በአካባቢ ካሉት ለምሳሌ ወላጆች ፣ጓደኞች ወይም ቤተሰብ አስተያየት ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ እዛ ሄዶ ቆሞ ማንን እንደሚመርጥ ማወቁ ከባድ ነው።

Bundestagswahl - Cheyenne Turner, Erstwählerin,
ቺየኔ ቱርነርምስል DW/N. Werkhäuser

እንደ ወጣቷ የሚያስቡት በርካታ ናቸው። ስለሆነም በመጨረሻ ወደ ምርጫ ጣቢያ ከመሄድ ይቆጠባሉ። የጀርመንን ፖለቲካ የሚያራምዱት እድሜያቸው በ 50 እና 70ዎቹ መካከል የሚገኙት ሰዎች ናቸው ይላሉ ፕሮፌሰር ክላውስ ሁሬልማን። በወጣቶች ላይ ጥናት ከሚያደርጉ ታዋቂ ምሁሮች አንዱ ናቸው። « ፖለቲካው በአግባቡ እየተራመደ ነው ብለው ያምናሉ።  ከርቀት ሆነውም ቢሆን የሚመለከቷቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች  ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ያያሉ። ሀገር ያስተዳድራሉ።  ፓርቲዎቹ ውስጥ ያሉት በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች እንደሆኑ ይታዘባሉ። ይህም ሀቅ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አባላት አማካይ እድሜ በ 6o ዎቹ ውስጥ ይገኛል።»ይህም በምርጫ ላይ ይስተዋላል። በ50ዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙት ጀርመናውያን ምርጫ ሲሄዱ ወጣት መራጮች ግን ራሳቸውን ያገላሉ። ይህም የሚሆነው እንደ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ሁሬልማን ማብራሪያ ወጣቱ በአግባቡ ያለውን ሚና ባለማወቁ ነው። ብዙውን ጊዜ ወጣት መራጮች በድምፃቸው ምን ያህል የፖለቲካ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ አያውቁም። ለዚህም ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት ትውጣ አትውጣ ሲባል የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል። 

Klaus Hurrelmann
የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሁሬልማንምስል Hertie School/Peter Himsel

ብሪታንያ የአውሮጳ ህብረት አባል ሆና እንድትቆይ ይፈልግ የነበረው አብዛናው ወጣት ድምፁን ባለመስጠቱ የትላልቆቹ ውሳኔ ፀድቋል። ይህ ውሳኔም ጀርመናውያኑ ወጣቶች ጉዳዩን በጥሞና እንዲያስቡበት በር ከፍቷል ይላሉ ሁሬልማን።« ምንም ቢሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ናቸው።  ለኔ ይሄ አስገራሚ ነው ምክንያቱም ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ስለሆነ፤ ዘላቂነት ይኑረው ወይስ እንደ ማዕበል መቶ ይመለሳል ወደፊት የሚታይ ይሆናል። »

ለበርካታ አዲስ መራጮች፣ ጥያቄው ጨርሶ ምርጫ እሄዳለሁ ወይ? የሚለው ሳይሆን የትኛውን ፓርቲ እና መሪ ልምረጥ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካውንም ዓለም አስቀድመው የተቀላቀሉ ጥቂት ወጣቶች አልጠፉም። ምንም እንኳን አማካዩ የፖለቲካ አባላት እድሜ በ60ዎቹ ውስጥ ቢገኝም የ 19 ዓመቷ ሉዊዘ ሀትንዶርፍ ካለፈው ዓመት አንስቶ ለአረንጓዴው ፓርቲ ተሳትፋለች። ከዚህ ዓመት አንስቶም የፓርቲው አባል ሆናለች። ለሌሎች ወጣቶች አሰልች የሆነው ፖለቲካን እሷ እንደ እድል ነው የምታየው። « ምክር ቤታዊ ዲሞክራሲ ያለበት ሀገር ነው የምንኖረው።  የተለያዩ ፓርቲዎች አሉን። ስለዚህ የፓርቲው አካል ሆኖ መገኘቱን መርጫለሁ። ምክንያቱም አባልነት ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር ቀጥተኛው መንገድ ስለሆነ።»

ሉውዘ በእድሜዋ የሚገኙ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ምንም ለውጥ አያምጣም የሚል አስተያየት ቢሰነዝሩም በአጠቃላይ የኔ ትውልድ ፖለቲካው ያሳስበዋል ትላለች። በከፍተኛ ተቋም የህግ ተማሪም የሆነችው ወጣት ለመጀመሪያ ጊዜ እሁድ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ድምጿን ትሰጣለች።

ከሰላሳ እድሜ በታች ያሉ ወጣቶች የፖለቲካውን ዓለም መቀላቀላቸውን የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ሁሬልማን ይደግፋሉ፣ ያበረታታሉም። እንደሳቸው ከሆነ ብዙ አማራጮች ክፍት ሆነው ለሚገኝለት ወጣት ምን ይጠቅመኛል? የሚለውን ጥያቄ እያንዳንዱ ፓርቲ  በአግባቡ መግለፅ አለባቸው። ምክንያቱም ወጣቱ ለዚህ ጥያቄ  ቆዳው ስስ ነው ይላሉ።

Bundestagswahl - Louisa Hattendorff, Erstwählerin
ሉዊዘ ሀትንዶርፍምስል DW/N. Werkäuser

በእሁዱ አጠቃላይ ምርጫ የጀርመን የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ መሪ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ  ማርቲን ሹልስ በእጩ መራሄ መንግሥትነት ቀርበዋል። ሁለቱም እጩዎች በቴሌቪዥን ፊት ለፊት ባካሄዱት ክርክር፤ ሥልጣን ላይ ያሉት ሜርክል ክርክሩን በጥሩ እና አሳማኝ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውን ከክርክሩ በኋላ የተደረገው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ያመለክታል። ለመሆኑ ሜርክልን ብቻ በመራሄ መንግሥትነት ለሚያውቀው አዲስ መራጭ ትውልድ ምርጫው ምን አይነት ሚና ይጫወታል? የ19 ዓመቷ ሉዊዘ ከምንም በላይ የሚረብሻት ሜርክል ፖለቲካቸውን ሲያራምዱ ምንም ሌላ አማራጭ እንደሌለ ማድረጋቸው ነው ትላለች። ይህም እንደሷ አስተሳሰብ ዲሞክራሲያዊውን ፉክክር ይጎዷል። ወጣቱ ሆነም ቀረ ምንም አንቀይርም የሚል አስተሳሰብ እንዲያድርበት ያደረገውም የሜርክል ለረዥም አመታት ሥልጣን ላይ መቆየት ነው ትላለች።

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሁሬልማንም እዚህ ጋር ጭጋግ ይታያቸዋል። «ወጣቱ ፖለቲካዊውን መረጋጋት እና የጀርመንን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ያወድሳል፣ መሪዋም ጥሩ ስራ እንደሰሩ ያምናል፣ስለሆነም ባለው መዋቅር ላይ ብዙ አይከራከርም፤ ግፋ ቢል ወጣቱ ራሱን ከፖለቲካው አለም ያሸሻል፤  ከዲሞክራሲያዊው ገፅታ ሲታይ ግን ይህ ዘላቂነት አይኖረውም። ምክንያቱም ፓርቲዎቹ እንዲያንቀላፉ ያደርጋል» ይላሉ ሁሬልማን።

የጀርመን ፓርቲዎች ታድያ አዲስ እና ወጣት መራጮችን ለማሳመን አሁንም ቸግሯቸዋል። የአረንጓዴ ፓርቲ አባሏ ሊዊዘ ለስልጣን እጩ ሆኜ እንድወዳደር አምስት ዙር የምርጫ ዘመቻ መፈክር መለጠፍ አልፈልግም ትላለች።  ለመጀመሪያ ጊዜ የምትመርጠው ቺየኔ ቱርነርም ብትሆን እሷ እና መሰሎቿን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ትኩረት እንዳልሰጧቸው ይሰማታል። ቢሆንም እሁድ ለመሰላት ፓርቲ ድምጸን ትሰጣለች። ቺየኔ ስለፖርቲዎቹ የበለጠ ለመረዳት CDU እንዳዘጋጀው እና የተገኘችበት የምርጫ ዘመቻ ጣቢያ በየቦታው ሌሎቹም ቢዘጋጁ ጥሩ ነው የሚል እምነት አላት።ይህም እሷ እና ሌሎች ወጣቶች በሌሎች ተመርተው ሳይሆን በራሳቸው እና በአመኑበት ፓርቲ ላይ ገለልተኛ ሆነው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ይረዳል ብላ ስለምታምን ነው።

 

ኒና ቬርክሆይዘር / ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ