1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወጣቷ ተዋናይት በፊልም፣ ሬዲዮና መድረክ

ዓርብ፣ ግንቦት 23 2005

በርካታ ወጣቶች ዕድሉንና አጋጣሚውን ባለማግኘታቸው ብቻ ከእነችሎታቸው ተደብቀው ይገኛሉ ትላለች የዛሬዋ የወጣቶች ዓለም እንግዳ። በመድረክ፣ ፊልምና ሬዲዮ ትወና በስፋት በመንቀሳቀስ ላይም ትገኛለች።

https://p.dw.com/p/18i39
ምስል picture-alliance/dpa

አንዳንድ ጊዜ አንዳንዶችን ዕድል አለያም አጋጣሚ ያልጠበቁት ቦታ ላይ በቀላሉ ስታንደረድራቸው ይስተዋላል። በአንጻሩ ደግሞ ዕምቅ ችሎታና ብቃት እያላቸው እንኳን አጋጣሚ የሠማይ መቀነት ሆኖባቸው ዓመታትን የሚገፉ ወጣቶች እዚህም እዚያም ተደብቀው ይገኛሉ። የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ወጣት አርቲስት መቅደስ ፀጋው ትባላለች። ወጣቷ በርካቶች መድረክ አጥተው ችሎታቸው እንደተደበቀ መቅረቱ ሁልጊዜም የሚያሳስባት ነገር እንደሆነ ትገልፃለች። መቅደስ በተለያዩ የመድረክ ቴአትሮች፣ ፊልሞችና የዶቸቬለ የበማድመጥ መማር የሬዲዮ ድራማን ጨምሮ ለአራት ዓመት በዘለቀ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ላይ በመሳተፍም ትታወቃለች።

ወጣት መቅደስ ፀጋው ትወናን የጀመረችው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የቤተሰብ መምሪያ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ነው። አ.አ. ቂርቆስ ተወልዳ ያደገችው መቅደስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት የተከታተለች ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ  በሽመልስ ሀብቴ አጠናቃለች። መቅደስ ወደ ትወናው ዓለም ሙሉ ለሙሉ እንዴት እንደተቀላቀለች በእዚህ መልኩ ትገልፃለች።

Symbolbild Drama und Masken
ምስል Fotolia/Eduard Härkönen

እርግጥም ወጣት አርቲስት መቅደስ ፀጋው  ጥሩ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። መቅደስ በተለያዩ ፊልሞች ውስጥ ዘመናዊነት የሚንፀባረቅባቸው ገፀባህሪያትን ወክላ ነው የምትጫወተው። ታዲያ «ጓደኛሞቹ» የተሰኘው ኮሜዲ የመድረክ ቴአትር ላይ እንዲያ ምንም የማታውቅ ገጠሬ ልጅ ሆና ላያት መቅደስ መሆኗን በቀላሉ ለመለየት ይከብዳል።

መቅደስ ከፊልሙም ሆነ ከመድረክ ተውኔት አድናቂዎቿ የምታገኘው ማበረታታት የበለጠ ጥንካሬ ይሰጣታል። ድንገት በቃለ መጠይቁ መሀከል መቅደስን «ታዘብኩሽ ግን» አልኳት፤ «ምነው፣ ለምን?» አለች ደንገጥ ባለ ድምፀት። መቅደስ፦ ዶቸቬለ ሬዲዮ ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ላይ ባዘጋጀው የበማድመጥ መማር ድራማ ላይም ተሳታፊ ነበረች።

«የተስፋይቱ ምድር» በተሰኘውና ወደ አውሮጳ የሚሰደዱ ወጣቶችን ህይወት በሚዳስሰው የዶቸ ቬለ የበማድመጥ መማር ድራማ ላይ መቅደስ ወጣቷ ሊንዳን ሆና ነው የተጫወተችው። አደገኛውን የባሕር ላይ የስደት ጉዞ የጀመረውን ዕጮኛዋን የትምህርት ዕድል አግኝታ በሄደችበት የአውሮጳ ምድር ታገኘ አታገኘው እንደሆነም ያጠይቃል ድራማው። ወጣቷ አርቲስት በጥበቡ ዓለም ውድድሩ ከባድ እንደሆነ ትገልፃለች።

ከወጣቷ አርቲስት መቅደስ ፀጋው ጋር ያደረግነው ቃለመጠይቅ በእዚህ ይጠናቀቃል። ችሎታውና አቅሙ ኖሯቸው ዕድል አለያም አጋጣሚ አልሰምር ብሎ የተደበቁ የጥበብ ሰዎች አጋጣሚውና ዕድሉ እንዲሰምርላቸው እንመኛለን። በጥበቡ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎች አይናቸውን በእነዚህ ወጣቶች ላይም እንዲያሳርፉ በመጠቆም የዛሬውን የወጣቶች ማኅደር ጥንቅር በእዚሁ እንቋጫለን።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ ከታች ያለውን የድምፅ ማጫወቻ ይጫኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ