1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ ሐይል ሰጪ ንጥረ-ነገር በኢትዮጵያ

እሑድ፣ መጋቢት 4 2008
https://p.dw.com/p/1IBuD
Meldonium Doping
ምስል picture-alliance/dpa/D. Sorokin

ዉይይት፤ ሐይል ሰጪ ንጥረ-ነገር በኢትዮጵያ

«የኢትዮጵያ አትሌቲክስና ሐይል ሰጪ መድሐኒት» ወይም ዶፒንግ የሚል ርዕሥ ሠጥተነዋል። ሐይል ሰጪ ዕፅ መጠቀም ከስፖርት እኩል ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ ነዉ።ጥንታዉያኑ የግሪክ፤ የሮማና የቤዛንታኒያን ስፖርተኞች በተለይም የሩጫ፤ የፈረስ ግልቢያ እና የትግል ስፖርተኞችን አንዳቸዉን ከሌላቸዉ ለመብለጥ ሐይል ሰጪ ቅጠላቅጠል እና ሥራሥር ይወስዱ እንደነበር በሰፊዉ ተዘግቧል።

ሥፖርቱ ዓይነቱ እየበዛ፤ እየሰፋ፤ ዉድድሩ እየረቀቀና እየጠነከረ በመጣ ቁጥር ከቅጠላቅጠል፤ ወይም ሥራሥር የሚገኘዉ ንጥረ ነገር በእንክብል፤ በፈሳሽ፤ በምግብ መልክም እየተዘጋጀ የአዉሮጳ ስፖርተኞች በሰፊዉ ይጠቀሙበት ነበር።ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዓለምን እሁለት ገምሶ በየሥፍራዉ በሚያሻኩት፤በሚያጋጭና በሚያወዛግበብት ወቅት ስፖርትም የካፒታሊስት-ኮሚኒስቶች ፍትጊያ መድረክ ሆኖ አትሌቶች አዉቀዉም፤ ሳያዉቅም፤ ተገድደዉም ሐይል ሰጪ መድሐኒት በተደጋጋሚ ይወስዱ አልፎ አልፎ ይጋለጡም ነበር።

ካናዳዊዉ የአጭር ርቀት ሯጭ ቤን ጆንሰን በ1998ቱ (እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) የሶል ኦሎምፒክ ሐይል ሰጪ መድሐኒት መዉሰዱ ሲጋለጥ ብዙ አነጋግሮ ነበር።የምሥራቅ ጀርመንዋ አትሌት ሬናተ ኖየን ፍልድ ከሐገሯ ከከበለለች በኋላ ሐይል ሰጪ መድሐኒት ትወስድ እንደነበር ማጋለጥዋም በዘመኑ ትልቅ ርዕሥ ነበር።ኢትዮጵያ እንደ ሶሻሊስት ሐገር ከወታደራዊ-ፖለቲካዊ ባሕላዊ እስከ ስፖርት በደረሰዉ ሽኩቻም በተለይ በአትሌትክሱ ዉድድር በሰፊዉ ተሳታፊ ብትሆንም አንድም ጊዜ አንድም አትሌት ሐይል ሰጪ መድሐኒት ወስዶባት ወይም ተጋልጦባት አያዉቅም።

Olympische Spiele Sydney 2000 Haile Gebrselassie
አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሲድኒ ላይ ሲያሸንፍምስል Getty Images/Bongarts/H. Szwarc

በቅርቡ ዘመንም አሜሪካዊቷ የሩጫ፤ የዝላይና የዱላ ቅብብል ዕዉቅ አትሌት ማሪዮን ሉዊስ ጆንስ፤ አሜሪካዊያኑ ብስክሌተኞ ላንስ አርም ስትሮንግ እና ፍሎይድ ላንዲስ ሐይል ሰጪ መድሐኒት መዉሰዳቸዉ በመጋለጡ ያገኙትን በየዉድድሩ ያገኙትን ሽልማት፤ ክብርና ማዕረግ ተገፈዋል።

ኢትዮጵያዉያን ግን ከአበበ ቢቂላ እስከ ምሩፅ ይፈጥር፤ ከሐይለ ገብረ ሥላሴ እስከ ገንዘቤ ዲባባ በአትሌትክሲ መደረግ ዓለምን ጉድ ያሰኘ ዉጤት ሲያመዘግቡ አንድም አትሌት አንድም ጊዜ አሳፋራዉ ቅሌት አጋጥሞት አያዉቅም።

በቅርቡ ግን ከጥንት ጀምሮ የነበረዉ የኢትዮጵያዉያን አትሌቶች ድል፤ የኢትዮጵያዉያን ኩራትና ክብር በነበረበት የሚቀጥል አልመሠለም።አለም አቀፉ የፀረ-ሐይል ሰጪ መድሐኒት ተቆጣጣሪ ተቋም WADA፤ ቢያንስ ዘጠኝ ኢትዮጵያዉን አትሌቶች ሐይል ሰጪ መድሐኒት ወስደዋል ተብለዉ እንደሚጠረጠሩ አስታዉቋል።

ከዘጠኙ ቢያንስ ሰወስቱ ከአትሌቲክስ መታገዳቸዉም እየተነገረ ነዉ።ሰሞኑን በደረሰን ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያዊቷ-ስዊድናዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ መድሐኒቱን መዉሰዷ ተረጋግጧል።እሷም ይቅርታ ጠይቃለች።አትሌቶቻችን በዚሕ ቅሌት የመነከራቸዉ ምክንያት፤ ምርመራዉ የደረሰበት ደረጃ፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የሚያሳድረዉ ተፅዕኖና መፍትሔዉ የዛሬዉ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ልደት አበበ