1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውርርድ በእግር ኳስ ጨዋታ

ዓርብ፣ ሰኔ 20 2006

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዶቻችን በአሁን ሰዓት በመካሄድ ላይ ያለውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የበለጠ አጓጊ ለማድረግ የወሰኑ ይመስላል።

https://p.dw.com/p/1CQju
Tipp-Kick Figuren
ምስል picture-alliance/dpa

የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር ከመጀመሩ በፊት በቡድን ሊመለከቱ በታደሙ ሰዎች ዘንድ ዛሬ የትኛው ቡድን ያሸንፋል? ስንት ለስንት ይለያያሉ? የሚሉት ጥያቄዎች የተለመዱ ናቸው። ነገር ግን አሁን አሁን ብዙ ሰዎች እነዚህን ጥያቄዎች ሲመልሱ ቢያንስ አንዴ እንኳን ገንዘብ ያስይዙና ይወራረዳሉ። ፍፁም አሰፋ ከእነዚህ አንዱ ነው።

ከፍጹም ሌላ እዚህ ጀርመን ስራዬ ብለው ለመወራረድ የወሰኑ ስድስት ወጣቶች ደግሞ እያንዳንዳቸው 50 ፣ 50 ዮሮ አዋጥተው 300 ዮሮ አሰባሰቡ። ይህንንም ገንዘብ « ቢዊን» በሚል ድር ገፅ ላይ ሂሳባቸውን ሞልተው መወራረድ ጀመሩ። ውርርዱን የሚያካሂዱት ዕርስ በዕርሳቸው ሳይሆን ከ ቢዊን ፅህፈት ቤት ጋር ነው። በዚሁ በቦን ከተማ ነዋሪ የሆነው የስፓኝ ተወላጅ ሀይሜ ካምፖአሞር ከነዚህ ወጣቶች አንዱ ነው። ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ እንዴት እንደሚወራረድ ገልፆልናል።« አንድ ሰው እንደፈለገው መወራረድ ይችላል። ለምሳሌ በዛሬው ጨዋታ አንድ ለአንድ ይለያያሉ ወይም፤ እኩል ለኩል ፣ወይም በመጀመሪያው የጨዋታ አምስት ደቂቃዎች ቀይ ካርድ ይሰጣል አልያም ሚሮስላቭ ክሎዘ 2 ጎል ያስገባል እያልሽ የምትወራረጅባቸው መደበኛ ጥያቄዎች አሉ። አልያም ራስሽ ጥያቄዎቹን ማዛመድ ትችያለች። አንድ የኖርዌይ ዜጋ እንደውም በቀደም የኡሮዋጋዩ ተጫዋች ሉዊዝ ሱዋሬስ አንድ የተቃራኒውን ቡድን ሊነክስ ይችላል የሚለውን ጥያቄ አዎ ብሎ በመመለስ ብዙ ገንዘብ ሊያገኝ ችሏል።»

እርግጡን ለመናገር። 600 ዮሮ ነበር ኖርዌያዊው ያሸነፈው። ነገር ግን ለእንደዚህ አይነት ውርርድ ተሳታፊዎቹ ብዙ እድል ያስፈልጋቸዋል። ሀይሜ እና ጓደኞቹ በዚህ ውርርድ ለመሳተፍ የወሰኑት የግድ ብዙ ገንዘብ እናገኛለን በሚል ምክንያት ብቻ አልነበረም።«አንድ ቀን ሁላችንም አብረን ተሰብስበን ሳለ ለምን ጨዋታውን የበለጠ አናደምቀውም ተባባልን። በርግጥ እንደ ብራዚል እና አርጀንቲና ያሉ ቡድኖች ሲጫወቱ ሁሉም ሰዎች በፍላጎት እንደሚመለከቱ ግልፅ ነው ነገር ግን እንበልና አልጄሪያ ከሩሲያ ጋ ስትጫወት ግጥሚያውን በርካታ ተመልካቾች ላይከታተሉት ይችላሉ። ብዙ ታዋቂ ተጫዋቾች ስለሌሉ ወይም ጨዋታው ስለማይስብ ። ስለዚህ እየተወራረድን ጨዋታውን አጓጊ እናድርገው ብለን ወሰንን።»

Strafe für Luis Suarez
ምስል Reuters

ኢትዮጵያ የሚኖረው ፍፁምም፤ በውርርድ ከሚገኘው ገንዘብ ይልቅ ውርርዱ የሚፈጥረው ስሜት ይበልጣል ብሎ ያምናል። የጀርመኖቹ ወጣቶች በየቀኑ ሲወራረዱ ሳምንት አለፋቸው። እንደ «ቢዊን» ያሉ ግለሰቦች ሊወራረዱባቸው የሚችሉባቸው ድህፈት ቤቶች በዚህ በአውሮጳ በየሀገሩ አሉ። ትርፋማም እንደሆኑ ይነገራል። ታድያ ተወራራጆቹ እነ ሀይሜስ?

«በመጀመሪያው ሳምንት መቶ ዩሮ አግኝተን ነበር። ስንጀምር በ300 ዮሮ ነበር። ከትናንት ወዲያ ግን በፈረንሳይ ቡድን የተነሳ ብዙ ገንዘብ ተሸነፍን። ፈረንሳይ እንደምታሸንፍ ርግጠኛ ነበርን ነገር ግን ከኢኳዶር ጋር እኩል ለኩል ነበር የወጡት። አንዳንዴ ብዙ መድፈር ይጠይቃል። ምክንያቱም ፈረንሳይ፤ ጀርመን ወይም ብራዚል ያሸንፋሉ ብለሽ ስትወራረጅ ለአንድ ዮሮ የምታገኝው ከሁለት ዮሮ ያነሰ ነው። ነገር ግን ብራዚል ከቺሌ ጋር ሲጫወት ቺሌ ካሸነፈች ለ አንድ ዮሮ ስምንት ዮሮ ሊሉ ይችላሉ። ስለዚህ አንድ ሰው ብዙ ገንዘብ ማግኘት ከተፈለገ ብዙ ገንዘብ መድቦ በድፍረት መጫወት ይኖርበታል።»

ሀይሜ እና ጓደኞቹ ያላቸውን የእግር ኳስ እውቀት እና ግምት ተጠቅመው ነው የሚወራረዱት። በተለይ ምርጥ ቡድን በሚባሉ ቡድኖች ላይ ብዙ ገንዘብ ይመድባሉ። ለዚህም ነበር እንደ ስጳኝ ፣ ኢጣሊያ እና ብሪታንያ ባሉ ቡድኖች ከግጥሚያው መሰናበት የተነሳ ገንዘባቸውን ያጡት። በገንዘብ መወራረድ ሱሰኛ ያደርጋል? አይ ይላል ፍፁም ሀይሜስ? «አንዴ ማሸነፍ የጀመረ የበለጠ ማሸነፍ ይፈልጋል። ከተሸነፈ ደግሞ ጥንቁቅ ይሆናል። እኛ ከመጀመሪያውም እያንዳንዱ 50 ዮሮ ይመድባል ነው ያልነው። ይህንን 300 ዮሮ ብንሸነፍ ከዚህ በላይ አንወራረድም። ሎተሪ እና እንደዚህ አይነት ውድድሮች አደገኛ ናቸው። ሰዎች በቃኝ የሚሉበትን ጊዜ አያውቁም። የኛ ግን ግልፅ ነው። የመደብነውን 300 ዮር ካጣን አንወራረድም። ምንም ሳንከስር የበለጠ እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »

Symbolbild Keyboard Tastatur Tippen
ውርርድ በቀላሉ ከቤት እና በኮምፒውተርምስል strixcode/Fotolia

ግን ያልተጠበቀ ነገር ሁሌ ሊከሰት እንደሚችል ሳይገልፅ ያላለፈው ሀይሜ የሀገሩ ብሔራዊ ቡድን እንዲህ በቶሎ ወደ ስጳኝ የተመለሰበት ድርጊት ጥሩ ምሳሌ ነው ይላል። ፍፁምን ግን በውርርድ ብዙ ጊዜ ቀንቶታል።ሀይሜ እና ጓደኞቹ ያገኙትን ትርፍ መልሰው ቢያጡም ገና ሊወራረዱ የሚችሉበት ግጥሚያዎች አሉ። በውርርዳቸው ትርፋማ ከሆኑ እቅዳቸው ምን ይሆን? « አዎ! እሱ ነው አላማችን። ብዙ ገንዘብ ካሸነፍን አንዱን የሳምንት መጨረሻ ሽርሽር እንሄዳለን ብለን ነው ያሰብነው። ምንም ያህል ካላገኘን ደግሞ ተሰብስበን ስጋ እየጠበስን ስለውርርዳችን እንቀልዳለን። ወይም የሆነ የምግብ ቤት እንሄዳለን። ከዛ የሚቀጥለውን የዓለም ዋንጫ እንጠብቃለን።»

ሀይሜ እና ጓደኞቹ 305€ ዮሮ ቀሪ ሂሳብ አላቸው። ምናልባት ቀጣዮቹ ግጥሚያዎች አዲስ እድል ይዘውላቸው ይመጡ ይሆናል።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ