1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

በጋምቤላ ለእርሻ ሥራ 100,000 ሔክታር መሬት የወሰደው የህንዱ ካራቱሪ ጥሎ ወጥቷል

ረቡዕ፣ መስከረም 17 2010

በጋምቤላ በሰፋፊ መሬት ላይ የሚካሔደው የእርሻ ሥራ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳቀደው አልሰመረም። በክልሉ በእርሻ ሥራ ከተሰማሩ መካከል የወሰዱትን መሬት ሙሉ በሙሉ በሰብል የሸፈኑት ከአንድ በመቶ በታች መሆናቸውን አንዲት ኢትዮጵያዊት የሰሩት ጥናት ይጠቁማል። የሕንዱ አበባ አብቃይ ካራቱሪ ኩባንያ ደግሞ ለእርሻ መሬት የወሰደውን መሬት ጥሎ ወጥቷል። 

https://p.dw.com/p/2kpnA
Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien
ምስል DW

የጋምቤላ እርሻ ዉስብዉስብ ችግሮች

በስተመጨረሻ የሕንዱ ካራቱሪ የእርሻ ኩባንያ እጅ ሰጠ። በአመት አንድ ሚሊዮን ቶን በቆሎ፤ ሩዝ፤የፓልም ተክልና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ሊያመርት ያቀደው ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ባሻገር ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲን በኃላፊነት ይመሩ የነበሩት አቶ አበራ ሙላት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር። 

የኩባንያው መስራች እና ባለቤትም እጆቹን ዘርግቶ ከተቀበላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከመቃቃራቸው በፊት ሥራቸውን "የመሬት ቅርምት" ብለው ለተቹባቸው ምላሽ ነበራቸው። ራም ካራቱሪ በኢትዮጵያ የእርሻ ሥራቸውን በጀመሩ ሰሞን ለውጭ መገኛኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ እርሳቸው እና ኩባንያቸው ለአፍሪቃ ያደረጉትን ሌላ ማንም አላደረገውም ሲሉ ተናግረው ነበር።
"ካራቱሪ እያደረገ ያለው አፍሪቃ የምትፈልገውን እና የሚገባትን ነው።  እያደረግን ያለንው ሌላ ማንም ያላደረገውን ነው። የአረንጓዴው አብዮት አፍሪቃን ያለፈው ከ20 አመት በፊት ነው። በዚህ አገር በግለሰቦች ዘንድ ከአንድ ሺህ በላይ ትራክተሮች የሉም።  ከ80 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት እና ከ120 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ለምትሰፋ አገር ይሕ አሳዛኝ ሑኔታ ነው።"

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab
ምስል DW/Schadomsky

ኃላፊው እንዳሉት ግን ቃላቸው አልሰመረም። እቅዳቸው አልተሳካም። ባለፈው ሳምንት የካራቱሪ ግሎባል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ራም ካራቱሪ በጻፉት ደብዳቤ "ደክሞናል፤ ተሸንፈናልም" ብለዋል። ኃላፊው በቢዝነስ ዘገባዎቹ ለሚታወቀው የብሎምበርግ ድረ-ገፅ ባጋሩት ደብዳቤ ኩባንያው የእርሻ መሳሪያዎቹን መልሶ ወደ አገሩ ለመጫን እንዲፈቀድለት "ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መዋዕለ-ንዋያችንን እና የንግድ ፈቃዳችንን ሰርዟል" ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ጠይቋል።  በሁለት ምዕራፎች እስከ 300,000 ሔክታር መሬት የማልማት እቅድ የነበረው ኩባንያ የሥራ ፈቃድ በኢትዮጵያ መንግሥት ከተሰረዘ ግን ሁለት አመት አልፎታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃዱን ሲሰርዝ ካራቱሪ ከተሰጠው 100,000 ሔክታር መሬት ያለማው 1,340 ሔክታር ብቻ ነበር። 
ካራቱሪ የጋምቤላ እርሻውን ጥሎ ሲወጣ ሊያለማ የወሰደው መሬት እንደ ድሮው አይደለም። የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ መንደራቸው እንዳይመለሱ ሆነው ተፈናቅለዋል።  ደን ተመንጥሯል፤ ብዝኃ-ሕይወት እንዳይመለስ ሆኖ ተቃውሷል። የዱር እንስሳት የመኖሪያ ቀያቸውን፤ተነጥቀዋል  ተሰደዋል። 
 የኢትዮጵያ መንግሥት የእድገት እና የለውጥ ሁለተኛ እቅድ እንደሚጠቁመው ክልሎች እና የፌድራል መንግሥቱ 2.3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለባለ ወረቶች ቢሰጡም የለማው ግን 840 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ የውጭ ባለወረቶችን ቀልብ በሳበው የጋምቤላ ክልል ሰፋፊ መሬት ለእርሻ የወሰዱት ባለወረቶች ሥራ እጅጉን ዘገምተኛ ነው። 
በሉድቪግ ማክሲሚላን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሙኒክ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ ወርቁ የሰሩት ጥናት እንደሚጠቁመው በጋምቤላ ክልል የሰፋፊ የእርሻ ሥራ ላይ ሊሰማሩ ፈቃድ ከወሰዱ 93 ከመቶ በላይ ያቀዱትን አልጀመሩም። ወ/ሮ አዜብ ወርቁ ሰፋፊ የእርሻ ሥራ በጋምቤላ ያሳደረውን ማኅበራዊ፤ኤኮኖሚያዊ እና የተፈጥሮ ሐብት ጫና ያጠኑ ባለሙያ ናቸው። ባለሙያዋ የሰፋፊ እርሻ ሥራው በውስብስብ ችግሮች የተበተበ እንደሆነ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በሚከተለው ሥልት ከሞላ ጎደል እቅዶቹን አሳክቷል የሚሉት ወ/ሮ አዜብ የአካባቢው ነዋሪዎች ከውጭ ባለወረቶቹ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሻከረ መሆኑን ያስረዳሉ።

Karte von Äthiopien
ምስል DW/E.B. Tekle

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ከዚህ ቀደም ባወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ለበእርሻ ሥራ ሰበብ ከምዕራባዊ ጋምቤላ 70,000 ሰዎችን ወደ አዳዲስ መንደሮች ማስፈሩን ገልጦ ነበር። ዘገባው "የሰፈራ ፕሮግራሙ ያለሰፋሪዎቹ ፈቃድ የሚካሄድ መሆኑን፣ ሰፋሪዎቹን መተዳደሪያና የኑሮ መሠረት ማሳጣቱን" አትቷል። ወ/ሮ አዜብ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ከሚቆጠረው የመዋዕለ ንዋይ ሥራ ጥቅም ካጡት የአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መኖሩን ታዝበዋል። ተመራማሪዋ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የባለወረቶቹ ግንኙነትም ጤናማ አይደለም ይላሉ። 
እስከ 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ሊመራበት የታቀደው የእድገት እና የለውጥ ውጥን (GTP II) እንደሚለው በባለ ወረቶች በሰፋፊ መሬት ላይ የሚከወነው እርሻ ሥራ ውጤታማ አልነበረም። ሰነዱ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ፤ የባለሐብቶች ምልመላ፤ድጋፍ እና ቁጥጥር ሊጠናከሩ እንደሚገባ ይጠቁማል።   ወ/ሮ አዜብ በሰፋፊ መሬቶች ላይ በእርሻ ሥራ የተሰማሩት የውጭ ባለወረቶች ቀዳሚ ትኩረት የሐገሪቱን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ በሆነ ነበር የሚል አቋም አላቸው።  
ወ/ሮ አዜብ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርሻ መሬት ለባለወረቶች ሲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎችን ፈቃድ ሊያገኝ ይገባል ባይ ናቸው። ጥልቅ የምርታማነት ጥናት ሊደረግ ያሻል የሚሉት ባለሙያዋ በእርሻ ሥራ ላይ የኬሚካል እና የውሐ አጠቃቀምም ትኩረት እንደሚያሻው ተናግረዋል። 

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien
ምስል DW

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ