1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውትድርና እና ፖሊስነት ምን ያህል ተወዳጅ ስራ ነው?

ዓርብ፣ ኅዳር 1 2010

ለበርካታ ወጣት ጀርመናውያን ከዚህ ቀደም ተመራጭ ነበር። እንደእየ ሀገሩ ሁኔታ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ይለያይ እንጂ ጀርመንም ይሁን ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የውትድርናን እና የፖሊስነትን ስራ ብዙም አርኪ ሆኖ ያላገኙት ይመስላል።

https://p.dw.com/p/2nPQT
Deutschland Berlin - Tag der offenen Tür der Polizei
ምስል Imago/S. Zeitz

ውትድርና እና ፖሊስነት ምን ያህል ተወዳጅ ስራ ነው?

ጀርመን ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ፖሊስ ለመሆን ለሚፈልግ ወጣት እድሉ ከመቼውም በላይ ሰፊ ነው። በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው ጎርጎሮሲያዊ 2017 ዓም ብቻ የጀርመን ፖሊስ መስሪያ ቤት 15 000 ፖሊሶችን መቅጠር ይፈልጋል። ይሁንና መስፈርቱን የሚያሟሉ ተመዝጋቢዎች ለማግኘት የመስሪያ ቤቱ ባለስልጣናት ቀላል ሆኖ አላገኙትም። የዶይቸ ቬለው ዳንኤል ፔልስ የወጣቶቹ ፍላጎት የቀነሰበትን ሁኔታ ወደ ፖሊስ ማሰልጠኛ ጎራ በማለት አጠያይቋል።

ጊዜው በበርሊን የፖሊስ ማሰልጠኛ ጣቢያ ልምምድ የሚደረግበት ሰዓት  ነው። ጥቁር ሰማያዊ የወታደር መለያ ልብስ የለበሱ 30 ተለማማጆች ኮስተር ያለው የአዛዣቸውን ትዕዛዝ እየተከተሉ ጠመንጃቸውን ይከፍታሉ ይዘጋሉ። ወዲያውም መሬት ላይ ተኝተው የማይታየው ጠላታቸው ላይ ያነጣጥራሉ።

አብዛኞቹ ሰልጣኞች እድሜያቸው በ20ኛዎቹ መጀመሪያ ላይ ይገኛል።  የ22 ዓመቱ ኡገር ዘንድሮ የሁለተኛ ዓመት ስልጠናቸውን ከሚወስዱ የወደፊት ፖሊሶች አንዱ ነው።«ፖሊስ መሆን በጣም ጥሩ እንደሆነ ሁሌም የማስበው ነበር። ቤተሰቦቼ ለዚህ ስራ ብዙ ክብር አላቸው እና ማሰልጠኛ ጣቢያው ሲቀበለኝ በጣም ነው የኮሩብኝ። ፖሊስ ሲኮን በማህበረሰቡ ዘንድ የሆነ ገፅታ አለው እና የግዳጅ ኃላፊነት።»

የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ልክ እንደ ኡገር ያሉ ለስራቸው ልዩ ፍቅር ያላቸው ወጣቶችን እያፈላለገ ይገኛል።ድንበር የሚጠብቁ ፣ በየባቡር ጣቢያው እና አይሮፕራን ማረፊያዎች ሰላም የሚያስከብሩ ፖሊሶች። ጥያቄው ግን ጀርመን ለምን ይህን ያህል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት አዲስ ፖሊሶች በአንድ ጊዜ አስፈለጋት?  ነው። አንድሪያ ዚፈርት የጀርመን የፖሊስ ኃይል ማሰልጠኛ ጣቢያ ኃላፊ ናቸው። « ያለውን የባጀት ክፍተት ለመሙላት ሲባል በርሊን ለአመታት ጠንካራ ርመጃዎች ስትወስድ ቆይታለች። የፖሊሱም አካል የዚህ ተጎጂ ሆናል።  ሰዎች ከስራ ባይፈናቀሉም አዲስ ፖሊሶች ግን አልተቀጠሩም። በአሁን ሰዓት ብዙ ሰዎች ወደ በርሊን ለመኖር እየመጡ ነው። ስለዚህ ነዋሪዎቹን የሚጠብቅ የበለጠ የፖሊስ ኃይል ያስፈልገናል። »

ሌላም ምክንያት አለ። የጀርመን ፖሊሶች እድሜያቸው የገፋ ነው። የጀርመን መዲና በርሊንን እንደ አብነት ብንወስድ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ 38 ከመቶ ያህሉ ፖሊሶች ጡረታ ይወጣሉ። ስለሆነም የበርሊን ፖሊስ መስሪያ ቤት  በመዋኛ ቦታዎች ሳይቀር ማስታወቂያ በትኗል። ማመልከቻ ማስገባት የሚያበቃበትንም የጊዜ ገደብ  ለሁለተኛ ጊዜ አራዝሟል። የጀርመን የፖሊስ ኃይል ማሰልጠኛ ጣቢያ ኃላፊ አንድሪያ ዚፈርት ይህ የስራ ዘርፍ አሁንም ዝና እንዳለው እና በርካታ አመልካቾች እንዳሉም ይናገራሉ። ይሁንና ብዙዎቹ አመልካቾች ከአንድ አዲስ ፖሊስ መኮንን የሚጠበቀውን መስፈርት አያሟሉም። 

« ፖሊሶች በየዕለቱ የተለያዩ ከባድ ችግሮች ከሚገጥሟቸው ሰዎች ጋር ይጋፈጣሉ። ፍርሃት ያደረበት ፣ ግራ የተጋባ ወይም የተደናገጠ ይኖራል። ስለዚህ በጣም ጥንቁቅ እና መላ ፈጣሪ መሆን ይገባቸዋል። በሌላ አጋጣሚዎች ደግሞ የበላይነታቸውን ማረጋገጥ እና ጠንካራ ርምጃ መውሰድ አለባቸው። ስራው ኃላፊነት የተሞላው እና አልፎ አልፎም ከታቀደው ጊዜ በላይ የሚወስድ ስራ ነው። »ተመዝጋቢዎቹ ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ብዙ ናቸው። ፖሊስ መሆን አመልካቾቹ  የጀርመን ዜጋ ወይም የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ዜጎች መሆን አለባቸው። የአካል ጥንካሬ እና ብቃታቸውም ወሳኝ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለተፈለገው ስራ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ሊኖራቸው ይገባል። እነዚህን አይነት ሰዎች ለማግኘት ለምን ከባድ እንደሆነ የጀርመን ፖሊስ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር ዩርግ ራዴክ ፍንጭ አላቸው።

« ለዓመታት የጀርመን ፖሊስ ስራ ላይ ቅነሳ ነበር። አሁን አዲስ ሰዎች እየፈለግን ነው ነገር ግን እነሱን ማግኘት ከባድ ሆኗል። ምክንያቱም የጀርመን ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ነው። ከኢንዱስትሪው፣ ከንግድ ዘርፉ እና ሌሎች ዘርፎች ጋር እየተፎካከርን ነው። ስለዚህ የፖሊስ ዘርፍን ተመራጭ ለማድረግ የበለጠ መስራት ይኖርብናል።»

እያንዳንዱ የፖሊስ ተቋም በተለያዩ ቦታዎች ለተሰማሩ ተቀጣሪዎች የሚከፍለው ደሞዝ ይለያያል። ሌላው የስራ ሰዓቱም ቋሚ አይደለም። ሌሊት ፣ቅዳሜ እና እሁድ፣ በበዓላት ቀናት መስራት ግድ ይላል። በአንዳንድ የጀርመን አካባቢዎችም ከሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ፖሊሶች ከወትሮው ሰዓት በላይ እንዲሰሩ ተገደዋል። የጀርመን ፖሊሶች ባለፈው ዓመት መስራት ከሚገባቸው ሰዓታት 22 ሚሊዮን ሰዓታት በላይ ሰርተዋል። ይህም አልበቃ ብሎ በፖሊሶች ላይ የሚጣሉት የኃይል ጥቃቶች ጨምረዋል። ዩርግ ራዴክ ቀደም ሲል ለአንድ ፖሊስ የነበረው ክብር ቀንሷል ይላሉ። 

« የፖሊሶችን ስራ የሚያመሰግኑ በርካቶች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለፖሊስ ያለው ከበሬታ እየቀነሰ ሲሄድ ይታያል። በስድብ ጀምሮ አንዳንድ ባልደረቦቻችን እንደውም ግፊያ፣ ምት፣እና አካላዊ ጥቃቶችን መቅመስ እና ማለፍ ነበረባቸው።»

ምንም እንኳን ስለ ጀርመን ፖሊስ የማያስደስቱ ወሬዎች ቢናፈሱም እንደ ኡገር ያሉ ሰልጣኞች ልበ ሙሉ ናቸው። ወጣቱ ስልጠናውን ጨርሶ ወደ ስራው አለም እስኪገባ መጠበቅ አቅቶታል። ግን ገና  18 ወራት ይቀሩታል። ወደፊት ሊገጥሙት የሚችሉት ፈተናዎች ብዙም አያሳስቡትም።

ከበደ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ወጣት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባልደረባ ነበር። ያኔ ፖሊስ ለመሆን የወሰነው በ10 ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጥሩ  ውጤት ባለማምጣቱ እና በአቅራቢያውም የሚያውቀው ስራ  ውትድርና ብቻ ስለነበረ ነው።ከበደ ላለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ ከተሞች በፌደራል ፖሊስነት አገልግሏል። ዛሬ 28 ዓመቱ ነው። ለስራው ፍቅር ቢኖረውም በቃኝ ብሎ የስራ መልቀቂያውን አስገብቷል። የለቀቀው በግል ምክንያት ነው። ሀገሬን የውጭ ሀይል ቢወራት ግን አስታጥቁኝ ብዬ መልሼ ልመዘገብ  እችላለሁ ይላል ዛሬ ላይም።

ምንጃሬው ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ሌላው ወጣት በበኩሉ በሚኖርበት አካባቢ በተለይ የ 10ኛ  ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤታቸው ጥሩ ያልሆነላቸው ወጣቶች ለውትድርና እየተገፋፉ እንደሆነ ገልፆልናል። በእሱ አመለካከት ይህ ትክክል አይደለም። ምንጃሬው ወንድሙን ጨምሮ ስድስት የሰፈሩ ወጣቶች በምዝገባው ሊሳተፉ ሲሉ ወንዱሙን ከውትድርና እንዲቀር ማሳመን ችሏል።

እንደእየ ሀገሩ ሁኔታ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ይለያይ እንጂ ጀርመንም ይሁን ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች የውትድርናን እና የፖሊስነትን ስራ ብዙም አርኪ ሆኖ ያላገኙት ይመስላል።

ልደት አበበ