1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐበይት የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ «ክንውኖች» በ 2011

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18 2004

ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ፣ ለዘመናዊ ሥልጣኔ መስፋፋት፣ ለኤኮኖሚ ዕድገትና በተናጠልም ሆነ በኅብረት ለአህጉራዊ መደርጀት፣ መሰላልነቱ ባያጠራጥርም፤ እስካሁን አስተዋይ ልቡና ያለው ሰውን የመሰለ ፍጡር፤

https://p.dw.com/p/13b3l
ምስል picture-alliance/ dpa

  በብቸኝነት የሚገኝባትን ፕላኔታችንን (ምድራችንን)ለመንከባከብ ይበልጥ ከመጣር ይልቅ፤ በ 2011 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመትም፣ እጅግ ሰፋ ያለው ወጪ የተደረገው፤ ለልማት ሳይሆን፤ ለአዳዲስ ጦር መሣሪያ ምርትና    በሺ፣ ሚሊዮንም ሆነ  ቢሊዮን  የብርሃን ዓመታት ርቀት ስላላቸው፣እንዲሁም በእኛዋ ፀሐይና ተጫፋሪ ፕላኔቶች፣  ጨረቃዋች ፤ ሥብርባሪ ከዋክብትና በመሳሰሉ ላይ ምርምር ለማድረግ ነው። ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፤መልሰ ብለን  ባለፉት 12 ወራት በምርምሩ ዘርፍ ትኩረት ያገኙ ትን ከሞላ ጎደል ዋና-ዋና ጉዳዮችን  እንዳስሳለን። 

ፍጥረተ ዓለምና ሀድ በሌለው መጠኑ የታላላቅ ከዋክብት ፍንዳታ ጠቋሚነት፣

ሲያስቡት ህልም  እንጂ ፣ እውን አይመስልም። ከቅርባችን ያለው፣  ተጣርቶ  ሳይመረምር ፣ የህልም ዓለም ስለሚመስለው፤ ለማወቅ መጣሩ ፤ የሰውን ልጅ የማወቅ ጉጉነት ከማመላከት አልፎ፣   ምን ዓይነት ፋይዳ  ያስገኝ ይሆን?!

እስካሁን ድረስ፣ ከብርሃን የሚፈጥን ምንም እንደሌለ ነው የሚታወቀው። እርግጥ ነው፣ በቅርቡ  የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ጣቢያ(CERN)፣ ኢምንት የአቶም ቅንጣቶች «ኒውትሪኖስ» ከብርሃን ፍንጠቃ ፤ በ 60 ቢሊዮንኛ ሴኮንድ  ፈጥነው ሳይንቀሳቀሱ እንዳልቀሩ መጠቆሙ የሚታወስ ነው። በእርግጥ ምንም በሌለበት ባዶ ቦታ (አየር ጭምር)  ብርሃን ፣ ከሞላ ጎደል፣  በሴኮንድ 300,000 ኪሎሜትር  ነው የሚፈነጥቀው።

የሥነ ፈለክ ጠበብት፣  21 ሚሊዮን  የብርሃን ዓመት ገደማ ርቀት ስላላቸው ከዋክብት ሲያወሱ ፤ ከተዘረጋ 13,75 ቢሊዮን  ዓመታት እንደሆኑት ስለሚገመተው ኅዋ ምንነት አስቡ!

የዓእማቱ ታላቅ ሳይንቲስት አልበርት አይንሽታይን ከብርሃን የሚፈጥን አለመኖሩን በምርምር ተመርኩዞ የቀመረው የፊዚክስ ነባቤ ቃል የሚሻር ከሆነ፤ በኅዋ ርቀትን ለማመላከት እንደመለኪያ የተወሰደውና «የብርሃን ዓመት» እየተባለ የሚጠቀሰውንም መለወጥ ግድ ይሆናል ማለት ነው።

በፊዚክስ የዘንድሮ ሽልማት አሸናፊዎች የሆኑት ጠበብት፤ ከ 50 በላይ የሚሆኑ እጅግ ራቅ ብለው የሚገኙ ግዙፍ ከዋክብት(ሱፐርኖቫዎች)(ከእኛዋ ፀሐይ ፤ ቢያንስ 8 እጥፍ የላቀ ግዝፈት ያላቸው መሆናቸው ነው፤ )የሚፈነጥቁት  ብርሃን ከተጠበቀው በላይ ደካማ ሆኖ መገኘቱን በምርምራቸው ላይ ደርሰውበታል። ይህ ደግሞ ፣ እንደተባለው ፍጥረተ ዓለም መጠኑ እጅግ እየሰፋና ፍጥነቱም እጅግ እየናረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው የሚያስረዳው።

የፍጥረተ ዓለም መጠን እጅግ እየሰፋና ፈጥነቱም እየናረ መሄዱ ከቀጠለ፤ ፍጻሜው ወደ በረዶ መለወጥ  ይሆናል ነው የሚባለው። ፍጥረተ ዓለምን  የሚያከንፈው «ጽልመታዊ ኀይል (Dark Energy) የሚሰኘው ነው ።  ይህ ደግሞ ከፍጥረተ ዓለም በበይት ምሥጢራት አንዱ መሆኑ ነው የሚነገርለት። ፍጥረተ ዓለም ፣  መገመት በሚያዳግት ፍጥነት  በሚጓዝበት የማያልቅ ጉዞ፣ ፕላኔታችን፤ ምድርና በውስጥዋና በላይዋ  የሚኖረው ፍጡር ፤ ጸሐይና አጫፋሪዎቿ ፕላኔቶች፤ ጨረቃዎች፤ ስብርባሪ ከዋክብት ፤ በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ የሚገኙበት የኅዋ ቀጣና ፤ ፍኖተ ኀሊብ (MILKY WAY)በሰዓት 2,1 ሚሊዮን ኪሎሜትር ነው የሚከንፈው።

ስለኅዋ ፤ ስለ ጽልመታዊ የኃይል ምንጭም ሆነ ፤ ጽልመታዊ ቁስ አካል ስለሚባለው የሚታወቅ ነገር የለም። ታዲያ እምብዛም በማይታወቅ ጉዳይ፣ ተማራማሪዎች እጅግ ከፍተኛው ሽልማት ሲሰጣቸው ማስገረሙ አልቀረም። በሙዑንሸን ፤ ጀርመን ፣ የማክስ ፕላንክ የምርምር  ተቋም፤ የሥነ-ፈለክ  ምሁር፣  ሃንስ ቶማስ ያንካ፤---

«እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ሽልማቱ አስገርሞኛል፤ እርግጥ ነው ግኝቱ፤ ሥር ነቀል ሊሰኝ የሚችል ነው። የፍጥረተ-ዓለም ተመራማሪውን ዓለም፣ መሠረታዊ አመለካከትም አጠያያቂ ነው የሚያደርገው።

በሌላ በኩል እነዚህ እጅግ ግዙፍ የሩቅ ከዋክብት (SUPERNOVAE)ምነነታቸውና ባህርያቸው መቶ በመቶ የሚታወቅ አይደለም። እንዲሁም ጽልመታዊው የኃይል ምንጭ የሚሰኘው ከዋክብቱን የሚያከንፈው ኃይል ምንነት በትክክል አይታወቅም። ታዲያ ለአንዲህ ዓይነቱ «ሾላ በድፍን» ዓይነት የምርምር ውጤት የኖቤል ሽልማት መስጠቱ አያስደምም አይባልም።»

Flash-Galerie NASA Mars
ማርስምስል NASA/Lunar and Planetary Institute

በተፈጥሮ የሳይንስ ዘርፎች፤ ከፊዚክስ ሌላ ፤  በሥነ -ህይወት (BIOLOGY ) ሆነ የህክምና ምርምር(MEDICINE )

የዘንድሮዎቹ  የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ፣

አሜሪካዊው ብሩስ ቦይትለርና የሉክሰምቡርኹ ተወላጅ ዩልስ ሆፍማን፤ እንዲሁም፣ የሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ሲታወጅ ፣ በ 68 ዓመታቸው በካንሠር ሳቢያ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተነገረላቸው ፤ ካናዳዊው የህክምና ተመራማሪ ራልፍ  እስቴይንማን ነበሩ። በሥነ ቅመማ (CHEMISTRY)በአንፀባራቂ ቁስ አካላት ባሕርይ  ላይ ሰፊ ምርምር ያደረጉት እስራኤላዊው  ሳይንቲስት Dan Shechtman ናቸው።

እ ጎ አ ሚያዝያ 12 ቀን 1961 ዓ ም፤ በዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ጠፈርተኛ ፣ ሩሲያዊው ኮስሞኖት ዩሪ ጋጋሪን ፣ በኅዋ የአንድ ሰዓት ከ 48 ደቂቃ በራራ አጠናቆ ወደ ምድር ከተመለሰ በኋላ ፤ በያኔዋ ሶብየት ኅብረትና ዩናይትድ እስቴትስ ፤ ስነ ፈለኩ ፣ የሳይንስ ብቻ ሳይሆን የርዑዮት ፉክክር ቢታይበትም ፤ ባለፉት 20 ዓመታት በዓለም አቀፍና በጋራ ሁለቱም መንግሥታት በኅዋ ምርምር ረገድ ትብብራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ከጨረቃ አልፎ ማርስ ደርሶ ለመመለስ 520 ቀናት ስለሚያስፈልግ ፤ ይህን ፤ የሩሲያ ፤ የፈረንሳይ፤ የቻይናና የኢታሎ ኮሎምቢያ ተወላጆች የሆኑ 6 ጠፈርተኞች ምድር ላይ እንዲለማመዱ ተደርጎ ፣ ሙከራው ተሳክቶ፣ ባለፈው ወር ተደምድሟል ። ከአውሮፓው የኅዋ ድርጅት የተወከሉት የኢጣልያና የኮሎምቢያው ተወላጅ ዲዬጎ ዑርቢና!

በአፍሪቃ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ትብብር፣

ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ለኤኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፤ ውድድር፤ የተፈጥሮ ግዳጅ በመሰለበት ዓለም፤ ለኅልውና ጭምር አለኝታም ነው። ዕውቁ ናይጀሪያዊ የኮምፒዩተር ሳይንስ ሊቅ ፊሊፕ ኤሜጋዋሊ፤ አፍሪቃ በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ በተለይ በሥነ ቴክኒክ ጠንክሮ ለመራመድ ካልጣረ ለዳግም ቅኝ አገዛዝ ቢዳረግ ላያስደንቅ እንደሚችል ነው የሚናገሩት።  የአፍሪቃ ፤ የእስያና የላቲን አሜሪካ ነባር ህዝብ፣ የሰሜን አሜሪካም ቢሆን፤ በመካከለኛው ክፍለ-ዘመን ፤ በተለይ  አፍሪቃውያን በባርነት እስከመጋዝ የደረሱት፤ በኋላም በ 19ኛው ምዕተ -ዓመት በቅኝ ግዛት ሥር የዋሉት፣ ከኋላ ተነስተው በጥቂቱም ቢሆን በሥነ ቴክኒክ ቀድመው በተገኙ አገሮች መሆኑ የሚታበል አይደለም።   ስለሆነም በየጊዜው እመርታ በሚያሳዬው የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ምርምር አፍሪቃውያን ተግተው ካልሠሩ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰል ለማንም የሚያዳግት አይደለም። 

በአፍሪቃው ክፍለ ዓለም፣ እጅግ ብሩኅ አእምሮ ያላቸውን ወጣቶች በማስተርስ ዲግሪ የሚያስመርቅ በተለይ ፣ በኬፕታውን ፣ ደቡብ አፍሪቃ ፣ የአፍሪቃ የሂሳብ ተቋም፣ African Institute of Mathematics(AIMS) ከ 8 ዓመት በፊት ከተቋቋመ ወዲህ፤ በክፍለ ዓለሙ በአጠቃላይ ከ 20 የማያንሱ የሂሳብና የተፈጥሮ ሳይንስ ተቋማት እንዲገነቡ እቅድ አለ። ሴኔጋል እምቡር በተባለችው ከተማ 2ኛውን በማቋቋም  የኬፕታውን ተከታይ ሆናለች። በእንዲህ ዓይነቶቹ ተቋማት አፍሪቃዊ አይንሽታይንን ማፍራት እንደሚቻል ነው ተስፋ የሚደረገው።

Micheal Katerregga
ማይክል ካቴሬጋ የ AIMS ምሩቅምስል AIMS

በዚሁ የጎርጎሪዮሳውያን ዓመት መገባደጃም በሆነው  ወር ፤በታኅሳስ ፣ መጀመሪያ ሳምንት ላይ አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪቃ አቀፍ ዩኒቨርስቲ የሰው ኃይል ፤ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ክፍል፤ የአፍሪቃን ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ደረጃና ጥራት ከፍ ማድረግ፤ ክፍለ ዓለሙንም በኤኮኖሚ እንዲያንሠራራ የሚያስችልበትን ፕሮጀክት በይፋ አስተዋውቋል።

የጥንት ሥልጣኔ መገለጫ ቅርሶችን ጠብቆ፣ በዘመናዊ ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ  ምርምር ፣ አመርቂ ዕድገት ለማስመዝገብ መጣር ከሳይንስ ምሁራን የሚጠበቅ ነው። ዕድገቱ እንዲገኝ  ከተፈለገ፣ አመቺ ሁኔታን መፍጠር የግድ የሚል ነገር ነው።

 ከተቋቋመ ፣ በመጪው ሚያዝያ 2 ዓመት የሚሆነው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካደሚ፤ የመጀመሪያውን የ 2 ቀናት ዐቢይ ጉባዔ በቅርቡ አዲስ አበባ  ውስጥ አካሂዷል።

አዘጋጂዎቹ እንዳሉት ፣ የአገሪቱን የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ግሥጋሤ ይዞታና ደረጃ  ለመመርመር በማለም ፣ «ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ-የአንድ አገር ኅልውና » በሚል መፈክር በተካሄደው ጉባዔ፤ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአካደሚ ምሁራን ጭምር ተሳትፈውበታል። 

ህዝቧ ፤ ዴሞክራሲ ለማምጣት ሰላማዊ ትግል አካሂዶ አምባገነን  አገዛዝ ባስወገደላት ግብፅ፤ ታኅሳስ 7 እና 8 ፤ ሰላማዊ ሰልፈኞች ካይሮ ውስጥ ከጦር ሠራዊቱ ጋር በታህሪር አደባባይ እንደተጋጩ፤ ከሰልፈኞቹ ዓላማ ያፈነገጠ ፈለግ የተከተሉ ጋጠ ወጦች፤ የብዙ ሺ ዓመታት የጥንት ግብጻውያን  ሥልጣኔ መገለጫ ቅርሶች የተከማቹበትን የግብፅ የሳይንስ ተቋም በአሳት ለኩሰው ጣራው መደርመሱና ወለሉ መፈርከሱ ተነግሯል። እ ጎ አ በ 1798 የያኔው የፈረናሳይ መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት ወደ ግብጽ በዘመተበት ወቅት ባደረገው ተቋም፣ በገንዘብ የማይተመኑ መጽሐፍት ታቃጥለዋል። እሳቱን ለማጥፋት የተረጨው ውሃም፤ ቃጠሎውን ማጥፋት ቢችልም መጽሐፍቱን ከብልሽት አላዳነም። ከግብፅ የጥንት ቅርሳ ጥበቃ ሚንስቴር ፤ ሞህዜን ሰዒድ ዓሊ፣---

«እዚህ የሆነው ነገር ፍጹም የሚያሳዝን ነው። በቃጠሎው የግብፅ ታሪክ ነው ለሞት የተዳረገው። በተቋሙ ውስጥ ከ 200,000 በላይ ታሪካዊ ሰነዶች በናፖሊዮን ዘመቻ ወቅት የተሰበሰቡ፤ ስለምሥር (ግብፅ) ጥንታዊ ጽሑፍ የሚገልፁ፣ በምንም ዓይነት፣ በዋጋ  የማይተመኑ ቅርሶች ናቸው ለጥፋት የተዳረጉት»።

በዓለም ውስጥ የመጀመሪያው አውቶሞቢል ጀርመን ውስጥ የተሠራበት 125 ዓመት  ባለፉት 12 ወራት ሲታሰብ ፤አትላንቲክ ማዶ ፤ በአትላንታ የሚገኘው ሥነ ቅመማን (ኬምስትሪን)መሠረት ያደረገው ፤ በዓለም ዙሪያ የታወቀው የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካው፣ ኮካ ኮላም፣  125ኛ ዓመት ልደቱን በ 2011 ነበረ ያከበረው። 

2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፤ በተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ፤ የሥነ ቅመማ (CHEMISTRY) ዓመት ተብሎ  ዓመቱን ሙሉ ታስቧል።  2012 የኅብረት ሥራ ማኅበራት መታሰቢያ ዘመን ተብሏል። የፊታችን እሁድ የሚያብተው አዲሱ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት  2012 ፤ የእኛው 2004 ፤ መልካም የኅብረት ሥራ ዘመን ይሁንልን! ተክሌ የኋላ ነኝ ፣ ቸር ለመስማትና ለማየት ያብቃን!

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ