1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የታዳሽ ኃይልምንጮች ጉባኤና የመራሔመንግሥት ሽረደር ንግግር

ሐሙስ፣ ግንቦት 26 1996

ባለፈው ማክሰኞ ቦን ውስጥ የተከፈተው የታዳሽ ኃይልምንጮች ዓለምአቀፍ ጉባኤ በሦሥተኛው ቀን ዛሬ ብዙ ሚኒስትሮችና ጠቅላይ ሚኒስትሮችም የተሳተፉበት በመሆኑ፣ የተለየ ድምቀት ነበር የታየበት። ከተሳታፊዎቹና ከዓለም ጋዜጠኞች ብዛት የተነሳ ወደ ጉባኤው አዳራሽ ለመዝለቅ ረዥም ጊዜ የፈጀ ረዥም የወረፋ ሰልፍ ነበር አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው። ለዛሬው የጉባኤ መድረክ የተለየውን ትርጓሜና ክብደት የሰጠው፣ የጉባኤው ጋባዥ--ማለት የጀርመን መራሔመንግሥት ጌርሃር

https://p.dw.com/p/E0fe

�� ሽረደር እዚያው በአካል ተገኝተው ያሰሙት ዲስኩር ነበር።

በመስከረም፣ ፲፱፻፺፭ ስለ ዛላቂው ልማት በጆሃንስበርግ/ደቡብ አፍሪቃ ዓለምአቀፍ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት ስለ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ጠቀሜታና ልማት አንድ ዓለምአቀፍ ጉባኤ ቦን ውስጥ እንደሚያስተናግዱ የገቡትን ቃል ይኸው እውን ያደረጉት መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር በንግግራቸው መግቢያ ላይ እንዳሉት፣ ብዙ ዓለምአቀፍ ተቋማት የሚገኙባት ከተማ ቦን የተባ መ ያየር ደኅንነት ጥበቃ ጽ/ቤት የሚገኝባት ማዕከል እንደመሆኗ መጠን፣ ስለ አማራጭ የኃይል ምንጮች አቅርቦት መንገዱ የሚጠቆምባት ትክክለኛ መካን ሆና ነው የምትታየው።

አለቅጥ እየናረ የሄደው የተለምዶው ኃይልምንጭ--በተለይም የምድርዘይት--ዋጋ በመላው ዓለም ውስጥ የኤኮኖሚያዊ ዕድገቱን ዕድል ይዘጋዋል፣ በደረጁት ሀገሮች ውስጥ የኤኮኖሚውን ግስጋሴ ይገታዋል፣ በሚደረጁትም ሀገሮች ውስጥ በድህነትና በረሃብ አንፃር የሚደረገውን ትግል ያሰናክለዋል፥ ሽረደር እንዳስሩት። በእርሳቸው አመለካከት መሠረት፣ አሁን በኢራቅና በሳኡዲት ዓረብያ የሚፈፀሙት ኣቃዋሽ ድርጊቶች የኃይል ምንጭ አቅርቦት ምኑን ያህል ብዙ ወጥ መሆን እንዳለበት በግልጽ ነው የሚያሳዩት። እርሳቸው የጠበብቱን ግምገማ መሠረት በማድረግ እንዳስረዱት፣ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንረት የሚደረጁት ሀገሮች በስድሳ ሚሊያርድ ዶላር የሚታሰብ ተጨማሪ ወጭ ነው የሚቆልልባቸው፤ ይህም በያመቱ የሚሰጠው የልማት ርዳታ እኩያ ነው የሚሆነው፤ ዛሬም ቢሆን በአፍሪቃ ያሉት እጅግ ድሆቹ ሀገሮች ከውጭው ንግድ ገቢያቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ከፊል ነው ለነዳጅ ማስመጫ የሚከሰክሱት።

ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ አንድ/አራተኛ ያህሉ--ወይም ሁለት ሚሊያርዱ--ይላሉ ሽረደር፣ ለማናቸውም የኃይል ምንጭ አቅርቦት አንዳች ዕድል አያገኙም፣ ንፁሕ ውሃ፣ የኮሬንቲ ብርሃን የሚያቀርቡበት ኣቅም የላቸውም፣ ኤኮኖሚያቸው አይንቀሳቀስም። ስለዚህ፣ ሽረደር እንደሚያስገነዝቡት፣ ድህነትን ለመታገልና ልማትን ለማረመድ የሚፈልግ ሰው በየአካባቢው ለሚከፈቱ፣ ለታዳሽና ለርካሽ የኃይል ምንጮች አስፈላጊውን ውዒሎተንዋይ መመደብ ይገባዋል።

መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር ያተኮሩበት ሌላው ዓቢይ ጉዳይ ሽብርተኞች በምድርዘይት ተቋማትና በሰውም ላይ የሚጥሉትን አደጋ ያስመለከተ ነበር። አሁን እነዚያኑ ሽብርተኞችና ግብረአበሮቻቸውን ተከታትሎ መያዝና ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን መረባቸውን ማሰስና መደምሰስ፣ የፊናንስ ምንጫቸውንም ማድረቅ የጊዜው ዓለምአቀፍ ጥሪ ነው ይላሉ ሽረደር። የዓለም ኤኮኖሚ በምድርዘይት ላይ ያለበትን ጥገኝነት እየቀነሱ የታዳሽ ኃይልምንጮችን ጠቀሜታ ማጠናከር ለፀጥታ አጠባበቅም ጥንካሬ የሚረዳ ሆኖ ነው እርሳቸው የሚያዩት።

አሁንና ወደፊት አማራጭ የኃይል ምንጮች በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሚወሰዱት ርምጃዎች እጎአ በ1992 በሪዮ/ብራዚል፣ በ2002 ደግሞ በጆሃንስበርግ/ደቡብ አፍሪቃ ስለ ዘላቂ ልማት በተካሄዱት የዓለም ጉባኤዎች ላይ የተጀመረው ሥራ ዓይነተኛ መሠረት እንደሚሆን ያስረዱት ሽረደር፣ ያየር ብክለት ለሚቀነስበት ለኪዮቶው ሠነድም ነበር ትኩረት የሰጡት። ይኸውም፣ በእርሳቸው ማስገንዘቢያ፣ የኪዮቶውን ሠነድ መላው መንግሥታት እስኪያፀድቁት ድረስ በመጠበቅ ፈንታ አሁኑኑ ወደ ትክክለኛው ርምጃ መንቀሳቀስ ይኖርብናል፥ ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ በዓለም ውስጥ ብርሃን የተነሳው አንድ ሚሊያርድ ሕዝብ እጎአ እስከ 2015 ድረስ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የኮሬንቲውን ብርሃንና መቀት አቅርቦት እንዲያገኝ የተተለመው ግብ እውን ሊሆን የሚበቃው።

ሽረደር እንደገለፁት፣ ዛሬ የፀሐይ ሙቀትና ነፋስ ወደ ኃይልምንጭነት የሚለውጡበት ቴክኒክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰባት ጀርመን፣ ፩፻፳ሺ የሚደርሱ ሠራተኞች ናቸው በዚሁ መስክ በኩል የሥራ ዕድል ያገኙት። ጀርመን ውስጥ በያመቱ ስድስት ሚሊያርድ ኦይሮ ነው ለታዳሽ ኃይልምንጮች ልማት የሚውለው። የአውሮጳውም ኅብረት እጎአ እስከ 2010 ድረስ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ከጠቅላላው የኮሬንቲ አቅርቦት የሚይዙትን ድርሻ ወደ ሃያ በመቶ ከፍ ለማድረግ ማቀዱም ነው የተገለፀው። ጀርመን ካሁን ቀደም በጆሃንስበርጉ ጉባኤ ላይ በገባችው ቃል መሠረት፣ በልማት ትብብሩ መርሐግብር ሥር በአምስት ዓመታት ውስጥ ፭፻ ሚሊዮን ኦይሮ ለታዳሽ ኃይልምንጮች ልማት፣ ሌላ ፭፻ ሚሊዮን ኦይሮ ደግሞ ለዚሁ ዘርፍ የእርባታ ኃይል ማጠናከሪያ ለማዋል ዝግጁ ናት። ይኸው የልማት ትብብር አሁን ፍሬ ማሳየት እንደጀመረ ያስረዱት ሽረደር፣ ሀገራቸው አሁን በአፍሪቃና በእስያ ብዙ ሀገሮች ታዳሽ የኃይል ምንጮችን አቅርቦት እንዲያስፋፉት፣ አመራረቱንና ፍጆታውንም እንዲያቀላጥፉት በመርዳት ላይ መሆኗንም ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ በተለይም ምሥራቅ አፍሪቃንና ግብጽን ነበር ምሳሌ አድርገው ያቀረቡት።