1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፉ የአክሲዮን ገበያ ውዥምብርና ተጽዕኖው

ሐሙስ፣ ጥር 15 2000

የአሜሪካ የቤት ባለቤቶች ብድርና ብድር መልሶ ለመክፈል ያለመቻል ችግር ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። ይሄው ቀውስ ሰሞኑን በዓለምአቀፉ የአክሢዮን ገበያ ላይም ብርቱ ውዥምብርን አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/E0cS
ምስል AP

ከኒውዮርክ እስከ ሻንግሃይና እስከ ሆንግ ኮንግ የምንዛሪው ተመን ክፉኛ ሲያቆለቁል ሁኔታው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋት መፍጠሩ አልቀረም። የአሜሪካ ኤኮኖሚ ሲነካ መዘዙ ለተቀረው ዓለም እንደሚተርፍ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። እንድ የአውሮፓ የባንክ ባለሙያ “አሜሪካ ስታነጥስ አውሮፓን ጉንፋን ይይዛታል” ሲሉ ነበር ተጽዕኖው አትላንቲክን ተሻጎሮ ሊከሰት እንደሚችል ያስገነዘቡት። በእርግጥም የቤት ባለቤቶች ብድርና ብድርን መልሶ መክፈል አለመቻል በአሜሪካ ባንኮች ዘንድ ያስከተለው በሚሊያርድ የሚቆጠር ኪሣራ፤ የዓለም ንግድ ዋነኛ መለዋወጫ የሆነው የዶላርም ዋጋ መውደቅ ከአውሮፓ እስከ ሩቅ ምሥራቅ እሢያ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት መሰንበቱ ብዙም አያደንቅም።

የአሜሪካ የምንዛሪ ባንክ ትናንት ከታሰበው ጊዜ አንድ ሣምንት ቀደም ብሎ ወለዱን በመቀነስ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሞክሯል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ሄንሪ ፓውልሰን እንዳሉት ውሣኔው ዓመኔታን የሚያዳብር ነው። “ይህ ማዕከላዊ ባንካችን ችግር ሲፈጠር በፍጥነት ዕርምጃ ለመውሰድ ብቁ መሆኑን ለዓለም ያሣየበት ገንቢ ውሣኔ ነው። ዕርምጃው በኤኮኖሚው መድረክ ላይ አመኔታን መልሶ እንደሚያስፍንም አያጠራጠርም” ሆኖም የአሜሪካ ኤኮኖሚ ከለየለት ቀውስ ላይ ወድቋል ለማለት ገና በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም የማዕከላዊው ባንክ ዕርምጃ ብቻውን ለፈውስ መንገድ ከፋች ይሆናል ብሎ ማመኑ ያዳግታል። በአሜሪካው ብሄራዊ ሸንጎ የኤኮኖሚ ኮሚቴ ውስጥ የፊናንስ ባለሙያ የሆኑት ዴሞክራቱ እንደራሴ ቻርልስ ሻመር እንዳሳሰቡት ፈጣን ዕርምጃዎች መከተል አለባቸው።
“የወለዱ ቅነሣና ከዚሁ ተያይዞ ለተጠቃሚውና ለቤት ባለቤቶች ርካሽ ብድር ለማቅረብ የተደረገው ውሣኔ ታላቁን የአሜሪካን ብሄራዊ ኤኮኖሚ ከቀውስ ለማዳን ብቻውን በቂ አይሆንም። ይልቁንም ኤኮኖሚውን ለማሳደግ የሚረዳ አንድ የለውጥ ፓኬት በተቻለ ፍጥነት ሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል። እኛ ዴሞክራቶች የፖለቲካ ልዩነት ሳያግደን በዚህ ጉዳይ ከሬፑብሊካኖችና ከፕሬዚደንት ቡሽ ጋር ለመተባበር ቁርጠኛ ነን” ብለዋል። ሻመር የተባለው የለውጥ ሃሣብ በሚቀጥሉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ ለተግባር ተጠናቆ እንደሚቀርብ ተሥፋ ያደርጋሉ። ፕሬዚደንት ቡሽም ትናንት 145 ሚሊያርድ ዶላር በተመደበለት የለውጥ ፓኬት ላይ ከኮንግሬስ መሪዎች ተገናኝተው መክረዋል። እንደ ዴሞክራቱ እንደራሴ እንደ ቻርልስ ሻመር በወቅቱ እየናረ ከሚሄደው የኤነርጂ ዋጋ አንጻር ተጠቃሚው ህዝብ በኪሱ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲኖረው ማድረጉ ወሣኝ ነው። ምክንያቱም የአሜሪካ ኤኮኖሚ መንኮራኩር የግል ፍጆቱ ነውና!

የፊናንስ ሚኒስትሩ ሄንሪ ፓውልሰንም ቢሆን ሁሉም ነገር በአሜሪካ ተጠቃሚዎች’ ዝንባሌ ላይ ጥገኛ መሆኑን አልሳቱትም። ስለዚህም የግብር ቅነሣው ይጠቅማል ባይ ናቸው። ጥያቄው በአሜሪካ ላይ የሚያንዣብበውን የኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ለመግታት በጊዜው ተገቢው ዕርምጃ ተወስዷል ወይ ነው። በኒውዮርክ የአክሢዮን ገበያ እንደተሰማው ከሆነ የማዕከላዊው ባንክ አስተዳዳሪ በወለድ ቅነሣ ውሣኔያቸው ዘግይተዋል። በሌላ በኩል በዚህ አውሮፓ የሕብረቱ የፊናንስ ሚኒስትሮች የእክሢዮኑን ገበያ ውዥምብር ለዘብ አድርገው ለመያዝ ነው የሞከሩት። የ 15ቱ የኤውሮ ምንዛሪ ተገልጋይ አገሮች ሊቀ-መንበር ዣን-ክላውድ-ዩንከር ሁኔታው በከፊል ድንጋጤ የቀሰቀሰው ነው ባይ ናቸው።
እናም አውሮፓ ውስጥ የኤኮኖሚው ዕድገት በተረጋጋ መሠረት ላይ የቆመ ነው የሚሉት ዩንከር የከፋ ሁኔታ አይጠብቁም። ይሁንና አሜሪካ ከቀውስ ለማምለጧ ደግሞ እርግጠኛ አይደሉም። በዚህ በጀርመንም የፊናንስ ጠበብትና ፖለቲከኞች በአውሮፓ የኤኮኖሚ ጽኑነት እንደማይጠራጠሩ በየፊናቸው ገልጸዋል። ቻንስለር አንጌላ ሜርክል እንዲህ ይላሉ። “የኤኮኖሚ ቀውስን የሚጠቁም አንድም ምልክት አይታይም። በዓመቱ የኤኮኖሚ ዘገባችን ካለፈው ዘመን ሲነጻጸር የዕድገት ትንበያችንን ዝቅ አድርገን አርመናል። ግን የአውሮፓም ሆነ የጀርመን ኤኮኖሚ በጽኑ መረጃዎች ላይ አልቆመም ማለት አይደለም። ከዚህ በተረፈ በአሜሪካ ገበዮች ላይ ከነበረን ጥገኝነት ጥቂት ነጻ ለመሆን ችለናል”

የሕብረቱ የምንዛሪና የኤኮኖሚ ኮሜሣር ዮአኪም አልሙኒያ በበኩላቸው የአሜሪካ መንግሥት በፊናንሱ ቀውስ ረገድ በአብዛኛው ተጠያቂ እንደመሆኑ መጠን የበጀት ኪሣራውን እንዲያለዝብ ነው የጠየቁት። አልሙኒያ እንደሚያምኑት የአውሮፓ ሕብረት በጉዳዩ በቀጥታ ጣልቃ መግባት የለበትም፤ በለውጥ መርሁና ጥብቅ በሆነ የበጀት ፖሊሲው መቀጠል አለበት። “የተጠቀምንባቸውና ወደፊትም የምንጠቀምባቸው በርካታ መሣሪያዎች አሉን። አላጋነንን እንደሆን እንጂ ምንም ነገር አላደረጋችሁም ልንባል አንችልም። በአክሢዮኑና በፊናንሱ ገበዮች የሶሥት ቀናት ውዥምብር ስለተፈጠረ ብቻ!” በሆንግ ኮንግና በሻንግሃይ ጭምር የአክሢዮኑ ገበያ በሰፊው ማቆልቆሉና ቀጣይ አዝማሚያ ማሣየቱም ለቻይና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ገቺ እንዳይሆን ስጋት መፍጠሩ አልቀረም። ማዕበሉ ያለ ብዙ ጉዳት ሊያልፍ ይችል ይሆን” ጠብቆ መታዘቡ የሚመረጥ ነው።