1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ሰኞ፣ ነሐሴ 28 2004

ባለፈው ሣምንት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ ዓበይት የስፖርት ውድድሮች አንዱ ስዊትዘርላንድ ዙሪክ ላይ የተካሄደው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ነበር።

https://p.dw.com/p/162lP
ምስል AP

ባለፈው ሣምንት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተካሄዱ ዓበይት የስፖርት ውድድሮች አንዱ ስዊትዘርላንድ ዙሪክ ላይ የተካሄደው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ነበር። በትናንትናው ዕለትም በርሊን ላይ ሌላ ዓለምአቀፍ አትሌቲክስ ውድድር ተካሂዷል። በሁለቱም ውድድሮች ደግሞ አስደናቂው ነገር በተለይ ኢትዮጵያዊው ወጣት አትሌት መሐመድ አማን በ 800 ሜትር ሩጫ በቅርቡ የለንደን ኦሎምፒክ በዚህ ርቀት አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግቦ የነበረውን ኬንያዊ በማሸነፍ የተለየ ጥንካሬ ለማሳየት መብቃቱ ነበር።

ባለፈው ሐሙስ የዙሪክ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ጃማይካዊው የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ዩሤይን ቦልት በ 200 ሜትር ሶሥት የአገሩን ልጆች በማስከተል ሲያሸንፍ በአንድ መቶ ሜትርም የጃማይካው የኦሎምፒክ ብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ዮሃን ብሌክ ባለድል ሆኗል። በ800 ሜትር ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ኢትዮጵያዊው መሐመድ አማን ኬንያዊውን ዴቪድ ሩዲሻን ቀድሞ ሲያሸንፍ በ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያውያን አንደኛና ሁለተኛ ሆነዋል።

ከኢትዮጵያ በኩል ደጀን ገ/መስቀል አራተኛ ሲወጣ ታሪኩ በቀለ ስድሥተኛ፣ ይግረም ደመላሽ ሰባተኛ፣ ኢማነ መርጋ ስምንተኛ፣ የኔው አላምረው አሥረኛ፤ እንዲሁም ይታያል አጥናፉ 15ኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሴቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች እንደገና ተሥፋ ሰጭ ውጤቶችን ነበር ያስመዘገቡት። በ 1,500 ሜትር አበባ አረጋዊ ኬንያዊቱን ሜርሢይ ቼሬኖን ቀድማ ስታሸንፍ በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ ደግሞ እቴነሽ ዲሮና ሕይወት አያሌው በቀደምትነት ተከታትለው ገብተዋል።

በትናንቱ የበርሊን ዓለምአቀፍ ውድድር መሐመድ አማን በ 800 ሜትር ኬንያዊውን ኤድዊን ኪፕላጋትን ቀድሞ ሲያሸንፍ በ 1,500 ሜትር ኬንያውያን ከአንድ አሰከ ሶሥት በመከታተል ብርቱ ጥንካሬ አሳይተዋል። በሴቶች 100 ሜትር ሩጫ የትሪኒዳድና ተባጎ ተወዳዳሪ ኬሊይ-አን-ባፕቲስት ስታሸንፍ በ800 ሜትር ኬንያዎቱ ፓሜላ ጀሊሞ አንደኛ፣ ፍራንሢን ኒዮንሣባ ሁለተኛ፣ እንዲሁም አበባ አረጋዊ ሶሥተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽመዋል። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ደግሞ ሶፊያ አሰፋ አሸንፋለች።

FC Bayern München - VfB Stuttgart
ምስል Getty Images/AFP

እግር ኳስ

በአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ግራናዳን 3-0 በመርታት ለመጀመሪያ ድሉ ሲበቃ ባለፈው አርብ በአውሮፓ ሱፐር-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ በአትሌቲኮ ማድሪድ 4-1 ተቀጥቶ የነበረው ቼልሢይ በእንግሊዝ ሻምፒዮና ቀደምቱ እንደሆነ ነው። በስፓኝ ላ-ሊጋ ባርሤሎና ቫሌንሢያን 1-0 በማሸነፍ በድል ጉዞው ሲቀጥል ከሶሥት ግጥሚያዎች በኋላ ሙሉ ዘጠን ነጥብ ይዞ ይመራል። ማዮርካ፣ ማላጋና ራዮ ቬሊካኖ በሰባት ነጥብ ተከታዮቹ ሲሆኑ ሬያል ማድሪድ አሁን ከፍ በማለት ዘጠነኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ሁኔታው ከስፓኙ ይመሳሰላል። ቼልሢይ ሪዲንግን 4-2 ሲረታ በሙሉ ዘጠን ነጥብ ቁንጮነቱን እንደያዘ ቀጥሏል። ስዋንሢ ሲቲይ፣ አልቢዮንና ማንቼስተር ሢቲይ በሰባት ነጥብ የሚከተሉ ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሉ አምሥተኛ ነው። ሊቨርፑል በገዛ ሜዳው በአርሰናል 2-0 ሲሸነፍ ይብስ በማቆልቆል በአንዲት ነጥብ 18 ሆኗል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ሽቱትጋርትን 6-1 ቀጥቶ በመሸኘት አመራሩን እንደያዘ ሲቀጥል ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣው ፍራንክፉርት በሁለተኛ ግጥሚያውም በማሸነፍ በእኩል ነጥብ ተከታይ ነው። ሶሥተኛው ሃኖቨርም ቮልፍስቡርግን 4-0 አሸንፎ በመመለስ ያሳየው ጥንካሬ ችላ የሚባል አልነበረም። እርግጥ ውድድሩ ገና በጅምሩ ላይ ሲሆን በልምድ የሚታወቁት ጠንካራ ክለቦች እያደር ከፍ እያሉ ቅደም ተከተሉን የሚለውጡ ለመሆናቸው አንድና ሁለት የለውም።

በተቀረ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ አራት ክለቦች ሁለተኛ ግጥሚያቸውንም በድል ሲወጡ ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ጁቬንቱስ ሊጋውን በጎል ብልጫ ይመራል። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ኦላምፒክ ማርሢይ በአራተኛ ግጥሚያውም ሬንስን 3-1 በመርታት በ 12 ነጥቦች መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ኦላምፒክ ሊዮን በአሥር ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን በዘንድሮው ውድድር ሊልን 2-1 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ድሉ የበቃው ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ደግሞ ወደ ስምንተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። ከዚሁ ሌላ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ትዌንቴና በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ቤንፊካ ሊዝበን ይመራሉ።

Großbritannien Paralympics Brasilien Südafrika Alan Oliveira und Oscar Pistorius
ምስል dapd

ፓራሊምፒክስ

ለንደን ላይ የሚካሄደው የበጋ ፓራሊምፒክስ በአስደናቂ ሁኔታ እንደቀጠለ ሲሆን በሜዳሊያ ብዛት ቻይና የማይደረስባት ሆና መምራቷን እንደቀጠለች ነው። ሕዝባዊት ቻይና እስካሁን 35 ወርቅ፣ 24 ብርና 28 ናስ፤ በጠቅላላው 87 ሜዳሊያዎችን ስታገኝ አስተናጋጇ ብሪታኒያ በ 16 ወርቅ ሁለተኛ፤ እንዲሁም አውስትራሊያ በ 14 ወርቅ ሶሥተኛ ናት። ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ሂደትና በተለይም ስለ ኢትዮጵያ ተሳታፊዎች ሁኔታ በስፍራው የምትገኘውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን አሁን በቅርቡ በስልክ አነጋግሬ ነበር።

Formel 1 Spa Große Preis von Belgien
ምስል AP

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት ቤልጂግ ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው የማካላረን ዘዋሪ ጄሰን ባተን አሸናፊ ሆኗል። ከመጀመሪያው ተርታ የጀመረው ባተን የተረጋጋ እሽቅድድም ሲያሳልፍ ሉዊስ ሃሚልተንና ፌርናንዶ አሎንሶ በአንጻሩ ገና ከጅምሩ በደረሰ ግጭት ከጠበቁት ውጤት ሊደርሱ አልቻሉም። የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ሶሥተኛ ሲወጣ የጀርመኑ ኒኮ ሁልከንበርግም አራተኛ ሆኗል።

የዕለቱ ድንቅ ተወዳዳሪ ምናልባትም ከአሥረኛው ቦታ ተነስቶ ውድድሩን በሁለተኝነት ለመፈጸም የበቃው ጀርመናዊው የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ነበር። ፌትል በአጠቃላይ ነጥብም አሎንሶን ተከትሎ ሁለተኛ ሲሆን ከአንደኛው የሚለየው በ 26 ነጥቦች ብቻ ነው። ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ያለውን ዕድል እንደያዘ ይቀጥላል። ሌላው ጀርመናዊ የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ በ 30ኛ ውድድሩ ሰባተኛ ሊሆን በቅቷል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ