1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም በ2015 ክፍል II

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18 2008

አሜሪካኖች፤ አዉሮጶች፤ አዉስትሬሊያኖች፤ ፋርሶች፤ አረቦች፤ ቱርኮች፤ በጥቅሉ የ22 ሐያል፤ ሐብታም መንግስታት ጦር ከአየር-ከምድር ቢቀጠቀጡትም ISIS ማሸበሩን አላስቆሙትም።

https://p.dw.com/p/1HUm5
ምስል Reuters/L. Jackson

ዓለም በ2015 ክፍል II

ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ በድል መጠናቀቁ የተነገረለት ጦርነት ዳግም ጦር ያስዘመተበት፤በዩክሬን ሰበብ ጦር የተማዘዙ ጠላቶች እንደ ጥሩ ወዳጅ በጋራ ሶሪያ የዘመቱበት፤ ሕዝብ የሚፈጅ የሚያሰድደዉን ጦርነት የሚያግፈጠፍጠዉ ሐያል ዓለም ለዛፍ፤ዕፅዋት፤ ለአየር ደሕነት በጋራ ሊሰራ ቃል የገባባበት የጎሪጎሪያኑ ዘንድሮ-አምና ሊሆን አራት ቀን ቀረዉ። ጊዜዉ ይሮጣል።ሕይወት አጭር ናት።ግን ቅጥቧ እስኪደርስ ትቀጥላለች።በጎርጎሮሳዊዉ 2015 የመጀመሪያ መንፈቅ ከአፍሪቃና አዉሮጳ ዉጪ ባለዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት ፖለቲካዊ እዉነተቾን ባለፈዉ ሳምንት ቃኝተን ነበር።ሁለተናዉን ዛሬ እንቀጥል።

                               የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ዳብሊዉ ቡሽ ግንቦት 2 2003 ያወጁት «ድል» ዉሸትን መደበቂያ ሌላ ዉሸት ባይሆን ኖሮ ዘንድሮ ግንቦት የድል፤ ገድሉ ዝክር አስራ-ሁለተኛ ዓመት የትልቂቱን ሐገር ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ስርጭትን ባጨናነቀ ነበር።ቡሽ ኢራቅ ላይ የከፈቱት የወረራ ዋና ጦርነት ዋና ዉጊያ በድል መጠናቀቁን ለማወጅ ቤተ-መንግሥታቸዉ፤ ርዕሠ-ከተማቸዉም አልበቃቸዉም ነበር።

የአሜሪካኖችን የርስ በርስ ጦርነት በድል አድራጊነት በማጠናቀቃቸዉ በአሜሪካኖች ዘንድ እስካሁን በሚደነቁ፤ በሚወደሱ፤ በሚከበሩት በፕሬዝደንት አብረሐም ሊከን ሥም በተሰየመችዉ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ላይ ወጡ።አስጨበጨቡ፤ አዉራ ጣታቸዉን ሽቅብ ቀስሩ፤ አሉም።-

                                       «ኢራቅ ዉስጥ ዋናዉ ጦርነት አብቅቷል።በኢራቁ ዉጊያ፤ ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቻችን የበላይነት ተቀዳጅተናል።»

Saudi-Arabien hunderte Tote bei Massenpanik in Mekka
ምስል Reuters/A. Masood

የቡሽ-ብሌር የእብሪት ወረራ ግን ኢራቅን ከድል ፌስታ ምድርነት ይልቅ ወደ የአሜሪካ ወታደሮች መሞቻነት፤ የኢራቅ ሰላማዊ ዜጎች ማለቀቂነትያ፤  የሸባሪዎች መፈልፈያነት ነበር የቀየራት።የአሜሪካ መገናኛ ዘዴዎችም የቡሽ የድል አዋጅ የተነገረበት አስራ-ሁለተኛ ዓመትን አዳፍነዉ ወደ ኢራቅ ዳግም ስለሚዘምተዉ ጦራቸዉና ዉጊያዉ እያነሱ ሲጥሉ ዓመቱ ተገባደደ።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማም ለቡድን 7 ጉባኤ ወደ ኤልማዉ- ጀርመን የመጡት የዛሬ 3 ዓመት ከኢራቅ ያሰወጡት ጦር ዳግም ወደ ኢራቅ እንዲዘምት ለሁለተኛ ጊዜ በወሰኑ በሰወስተኛዉ ሳምንት ነበር።ኦባማ ከቅርብ ተባባሪዎቻቸዉ ጋር የመከሩ፤የወሰኑት ግን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት ዳአሽ፤ ወይም ISIS (በምሕጻሩ) የተሰኘዉን ቡድን ከሚወጉበት ሥልት ይልቅ ሩሲያን ስለሚቀጡበት እርምጃ ነበር።

                               «ሥራ እና ዕድል የሚፈጥር የዓለም ምጣኔ ሐብት መፍጠር፤በአትላንቲክ ማዶ-ለማዶ አዲስ የንግድ ስምምነት ማድረግ፤ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችዉን ወረራ በጋራ መቋቋም፤ የፅንፈኞችን አመፅ እና የዓየር ንብረት ለዉጥን መቋቋም ዋና ትኩረታችን ነዉ።»

አሜሪካኖች፤ አዉሮጶች፤ አዉስትሬሊያኖች፤ ፋርሶች፤ አረቦች፤ ቱርኮች፤ በጥቅሉ የ22 ሐያል፤ ሐብታም መንግስታት ጦር ከየር-ከምድር ቢቀጠቀጡትም ISIS ማሸበሩን አላስቆሙትም።ሙስሊማዊ የሚባለዉ ቡድን በሙስሊሞቹ ቅዱስ ወር ረመዳን ኮባኒን፤ኩዌትን እና ኤል ካንቶኒን በተከታታይ አሸበረ።

Ägypten Untersuchung nach Absturz russischer Passagiermaschine
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

የቡድኑ አባላት ሰኔ ሃያ-አምስትና ሐያ-ስድስት ኮባኒን-ሶሪያ እና የኩዌት መስጊድ ዉስጥ ባፈነዱት ቦምብ መቶ ሰማንያ ሰዉ ገደሉ። የቡድኑ አባል ነዉ የተባለ አንድ ወጣት ደግሞ ካንቶኒ በተባለች የቱኒዚያ መዝናኛ ሥፍራ ላይ  አርባ ሰዎችን ረሸነ።አብዛኞቹ የብሪታንያ ሐገር ጎብኚዎች ነበሩ።

ሐምሌ፤ ለፓኪስታኖች የሙቀት እልቂት ዓመት ነበር።አለቅጥ የናረዉ ሙቀት ከ2000 በላይ ሰዉ ገደለ።ለቴሕራን ዋሽግተን-ብራስልሶች ግን ወሩ ከቸር ወሬ ጋር ነበር የባተዉ።በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ሰበብ ለበርካታ አመታት ሲወዛገቡ ደግሞ በተቃራኒዉ ሲደራደሩ የነበሩት ኢራን፤ ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራቸዉ የምዕራባ አዉሮጳ መግስታት ዉዝግብ፤ ድርድር በአግባቢ ዉል ተቋጨ።ሐምሌ 14

ዓመቱ ለኩባ ገደኛ ብጤ ነዉ።ሶሻሊስታዊቷ ዉብ ደሴት እና ትልቅ፤ጉልበታም፤ ሐብታም ጎረቤት ጠላትዋ ዩናይትድ ስቴትስ 54 ዘመናት ያስቆጠረ ፤ ግጭት፤ ቁርቁስ ዉዝግባቸዉን አስወግደዉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጀመሩ።በሐቫና የዩናይትድ ስቴትስን ኤምባሲን ዳግም የከፈቱት የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ነበሩ።

                           «የዲፕሎማሲ ግንኙነት መመሥረት አንድ መንግሥት ለሌላዉ የሚዉለዉ ዉለታ አይደለም። ሁለት መንግሥታት፤ የሁለቱም ሐገራት ሕዝቦች እንዲጠቀሙ የሚያደርጉት እንጂ።»

የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት የሚባለዉን ቡድን፤ የምዕራብ ተባባሪዎችዋን ወይም የአረብ ወዳጆችዋን ያክል አልወጋችም ተብለ በተደጋጋሚ ስትወቀስ የነበረችዉ ቱርክ ጎረቤቶችዋን ከሚያተራምሰዉ ጦርነት ተሞጀረችበት።አንካራ፤ ባንድ በኩል ISISን በሚወጉት የኢራቅና የሶሪያ ኩርዶች በሚደገፉት በኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ (PKK) ሽማቂዎች፤በሌላ በኩል በISIS ላይ የከፈተችዉ መንታ የአዉሮፕላን ድብደባ የምሥቅልቅሉን ጦርነት ግራ አጋቢ ገፅታ ያፈጋ ነበር።

G7 Gipfel Schloss Elmau Outreach Konferenz Gruppenfoto
ምስል Getty Images/AFP/R. Michael

ኩርዶች ISISን ይወጋሉ፤ ምዕራባዉያን መንግሥታት ኩርዶችን ያስታጥቃሉ፤ቱርክ የምዕራባዉያን መንግሥታት የሚበዙበት የሰሜን አትላቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል በመሆንዋ የምዕራባዉያኑ ተሻራኪ ናት።ግን በተሻራኪዎችዋ የሚረዱትን ኩርዶችንም፤ተሻራኪዎችዋ የሚወጉትን ISISንም እኩል ትወጋለች።

በግራ-አጋቢዉ የሐይል አሰላለፍ የሚዘወረዉ ጦርነት አላባራም።ቱርክ መሸበሯም አልቆመም።የዘመን ዑደትም ቀጠለና ሐምሌ በነሐሴ ተተካ።ዓለም የ2014ቱን የዓለም ሴቶች ቀን በሚያከብርበት መጋቢት 8  227 መንገደኞችና 12 ሠራተኞቹን አሳፍሮ ከኩዋላላፑር-ማሌዢያ ወደ ቤጂንግ-ቻይና መብረር እንደጀመረ ድንገት የተሠወረዉ የማሌዢያ የመንገደኞች አዉሮፕላን የገባበት መጥፋቱ ዓለምን እንዳስደመመ ነበር።

ነሐሴ 5 ሬዩኒየን በተባለችዉ የፈረንሳይ ቅኝ ደሴት አጠገብ የተገኘዉ የአዉሮፕላኑ ጉማጅ ግን የዓመት ከሰወስት ወሩን የሚስጥር ቋጠሮ ዉልን ያመለከተ ነዉ።መስከረም መካና መዲና ለሐይማኖታዊ ተልዕኮ፤ኒዮርክ ለፖለቲካ-ዲፕሎማሲያዊ ጉባኤ አመቱን ሙሉ የባተሉበትን ዝግጅት ያስተናገዱበት ወር ነዉ።

የኒዮርኩ ከዓመታዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ዓለም አቀፋዊነቱም በላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባኛ ዓመት ዝክርም ነበር።የሰባ-ዐመቱን አንጋፋ ድርጅት የሚመሩት የ71 ዓመቱ አዛዉንት ፓን ጊ ሙን በርግጥም ዲፕሎማት ናቸዉ።ጦርነት፤ ሽብር፤እልቂት፤ ስደት ዉዝግብ የነገሰበትን 2015ን እንደማንኛዉም ዓመት ጥሩም መጥፎም የተከወነበት ነዉ አሉት።

«2015 የበጎ ግኝትም፤ የዘግናኝ ድርጊትም ዓመት ነዉ።»መስከረም 24 ሚና-ሳዑዲ አረቢያ፤ ዓመታዊዉ የሙስሊሞች ሐይማኖታዊ ጉዞ በዘግናኝ እልቂት ተጨናጎለ።

Symbolbild - Flagge ISIS
ምስል picture-alliance/dpa

በሐጃጆች መካከል በተፈጠረ ትርምስና መረጋገጥ ከ2200 በላይ ሐጃጆች አለቁ።የኒዮርኩ ጉባኤ በሐዘን መግለጫ ቢታጅብም እንደቀጠለ ነበር።ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ጥሩ ያሉት የዓመቱ ክንዉን የዓመአቱ ግብ ይባል የነበረዉን ዕቅድ የሚተካ አዲስ አቅድ መፅደቁን ነዉ።SDG

«የአጠቃላይ ጉባኤዉ ሰባኛ ስብሰባ የተጀመረዉ፤ አስራ-ሰባት የዘላቂ ልማት ግቦችን (SDG) ያካተተዉን 2030 የልማት አጀንዳዎችን ባፀደቀ አንፀባራቂ ዉጤት ነዉ።»

መጥፎ ወይም ዘግናኝ ካሉት የዓመቱ የአመቱ ክስተት ዋነኛዉ ደግሞ የሶሪያ ጦርነትና የሟች ስደተኛዉ ቁጥር መበርከት ነዉ።«ግጭቱ ለሶሪያ ታላቅ ድቀት፤ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መከፋፈል ደግሞ አሳፋሪ ምሳሌ ነዉ።ታሪክና ፍትሕ ምሕረት አይኖራቸዉም።»

የጦርነቱ ዘግናኝ ዉጤት ኒዮርክ ላይ ሲዘረዘር የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ትደግፋለች የምትባለዉ ሩሲያ፤ ሶሪያ የሚገኙ የISIS ይዞታን በአዉሮፕላን መደብደብ ጀመረች።መስከረም ሠላሳ።ምዕራባዉያንን የምትቃወመዉ ሩሲያ ISISን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ሸማቂዎችን ትደበድባለች ከሚል ወቀሳ አላመለመለጠችም።

ከባዱ ብቀላ የደረሰባት ግን ከISIS ወይም ከተባባሪዎቹ ነበር።ሩሲያ ISISን መደብደብ በጀመረች በወሩ 224 መንገደኞችንና ሰራተኞችን አሳፍሮ ከሻርም አል-ሼክ ግብፅ ወደ ፒተርስቡርግ-ሩሲያ ይበር የነበረ አዉሮፕላኗ ሲና-ግብፅ በረሐ ጋየ።ተሳፋራዊቹ በሙሉ አለቁ።አዉሮፕላኑ የጋየዉ አሸባሪዎች ከመንገደኞች ጋር ባሳፈሩት ቦምብ መሆኑ ተረጋገጠ።

ከሩሲያ ቀድማ፤ ከሌሎቹ ዘግይታ ከሶሪያ ዉጊያ የተዘፈቀችዉ ቱርክ ዘንድሮ ካስተናገደቻቸዉ ጥቃቶች አንዱ-አንካራን ያሸበረዉ ቦምብ ነበር።ጥቅምት 10። ሠላም እንዲሰፍን ለመጠየቅ አደባባይ በወጣ ሠልፈኛ መሐል የፈነዳ ቦምብ ከመቶ በላይ ሰዉ ገደለ።አራት መቶ አቆሰለ።

Frankreich Cafe A La Bonne Biere Trauer nach den Anschlägen von Paris
ምስል Getty Images/AFP/K. Tribouillard

አፍቃኒስታን ዉስጥ ከ2001 ጀምሮ ከታሊባን እና ከአል-ቃኢዳ ሸማቂዎች ጋር የሚዋጋዉ አሜሪካ መራሽ ጦር በ2014 ጠቅልሎ እንደሚወጣ ሲነገር 13 ዓመት ያስቆጠረዉ ዉጊያ ትርፍ-ኪሳራ እንዳነጋገረ ነበር።ዘንድሮ በአስራ-አራተኛ ዓመቱ ደግሞ ጦሩ እዚያዉ እንዲቆይ፤ የወጣዉም በሌላ እንዲተካ ተወሰነ።«ተሸነፍን፤ ወይም ፈራን » ለማለት የደፈረ ግን አልነበም።

ጥቅም 26 ሕንድ፤ ፓኪስታን እና አፍቃኒስታንን የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰወስት መቶ በላይ ሰዉ ገደለ። በሬክተር መመዘኛ 7,5 የተለካዉ መሬት መንቀጥቀጥ የጠናዉ ሒንዱ ኩሽ በተባለዉ የፓኪስታን ግዛት ነበር።

የቻይና እና የታይዋን የረጅም ዘመናት ጠብ የሠላም ጭላንጭል የፈነጠቀዉ ዘንድሮ ነበር።ሕዳር ሰባት የቻይናዉ ፕሬዝደንት ዢ ቺፒንግ እና የታይዋኑ አቻቸዉ ማ ይንግ-ጄዉስ ሲንጋፑር ዉስጥ ፊት ለፊት ተገናኝተዉ ተነጋገሩ።የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ፊትለፊት ተገናኝተዉ ሲነጋገሩ ከ1949 ወዲሕ የሕዳሩ የመጀመሪያዉ ነዉ።

ሕዳር 12 የሊባኖስዋ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት በተከታታይ የቦምብ ፍንዳታ ተናወጠች።43 ሰዉ ተገደለ።ከ230 በላይ ቆሰለ።በማግስቱ ተረኛዋ ፓሪስ ነበረች።የፓሪስ ምግብ ቤት፤የሙዚቃ አዳራሽ እና የኳስ ሜዳ መግቢያን በቦምብ እና ጥይት ያሸበሩት ታጣቂዎች 113-ሰዉ ገደሉ።

ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ «እኔም ሻርሊ ኤብዶነኝ» ሲል የነበረዉ ዓለም በሌላ ሐዘን እየቆዘመ-ለብቀላ ይዝት ገባ።

ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ።ቤይሩትንም፤ ፓሪስንም ያሸበሩት የISIS አባላት ናቸዉ ተብሏል።ፈረንሳይ ሶሪያ በሸመቀዉ አሸባሪ ቡድን ላይ የከፈተችዉን የአዉሮፕላን ድብደባ ማጠናከሯ ከፓሪስ ሲዘገብ፤ የቱርክ ጦር የISISን ይዞታ ይደበድብ ነበር የተባለ የሩሲያ ተዋጊ ጄትን መትታ ጣለች።ቱርክን ለመቅጣት የሩሲያ ሁለንተናዊ አፃፋ ቀጠለ።

ዘመኑን በጎርጎሪያዊዉ ቀመር የሚያሰላዉ የክርስትና እምነት ተከታይ ለገና በዓል ሲዘጋጅ የታሊባን ታጣቂዎች ባግራም-አፍቃኒስታን ዉስጥ ስድስት የአሜሪካ ወታደሮችን ገደለ።ታሕሳስ 23።በማግስቱ-እኩለ ሌት፣-

ይባል ገባ።ከነገ-ወዲያ ዉድቅት ደግሞ አዲዮስ-2015 ይባላል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።በዘመኑ ለምትቆጥሩ መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ