1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፉ ጸረ የባህር ላይ ውንብድና ትግል

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 10 2001

የዓለም ሀገሮች የባህር ላይ ውንብድናን ለመታገል በአንድነት ተባብረው ርምጃ እንዲወስዱ ካለፉት ጊዚያት ወዲህ ጥሪው እየተጠናከረ መሰማት ይዞዋል።

https://p.dw.com/p/HZA0
ምስል picture alliance/dpa

ዩኤስ አሜሪካ ለምሳሌ በባህር ላይ ወንበዴዎች አንጻር የምትወስደውን የራስዋን ርምጃ በውጭ ጉዳይ ሚንስትርዋ፡ ሂለሪ ክሊንተን አማካይነት ሰሞኑን አስተዋውቃለች።
------------

በሶማልያ የባህር ጠረፍ የባህር ላይ ውንብድና እየተባባሰ በመምጣቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዚህ አንጻር ምን ርምጃ መስውሰድ እንደሚቻል ማሰላሰል ይዞዋል። ይሁንና፡ ጠበብት እንደሚሉት፡ በሶማልያ ማዕከላይ መንግስት እስካልተመሰረተ ድረስ፡ የባህር ላይ ውንብድናን ተጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም። ዩኤስ አሜሪካ እአአ በ 1993 ዓም በሶማልያ ያልተሳካ ጣልቃ ገብነት ካካሄደች ወዲህ፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፡ ዩኤስም ሆነች ሌሎች የውጭ ኃይላት በአፍሪቃዊቱ ቀንድ ሀገር ማንኛውንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የሚደረግበትን ሀሳብ ያበረታታሉ ተብሎ አይታሰብም ነበር። ይሁን እንጂ፡ የሶማልያውያኑ የባህር ላይ ወንበዴዎች የተለያዩ ሰንደቃላማዎችን፡ የዩኤስ አሜሪካን ሰንደቃላማን ጭምር እያውለበለቡ በዚሁ የባህር ክልል በሚተላላፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ካጠናከሩ ባኋላ በነዚሁ አጥቂዎች አንጻር ርምጃ የመውሰዱ ሀሳብ ጎልቶ መሰማት ጀምሮዋል። የዩኤስ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂለሪ ክሊንተን ሀገራቸው የባህር ላይ ውንብድናን ለመታገል ባወጣችው አዲስ ፖሊሲ ልትወስደው ባሰበችው ርምጃ መሰረት፡ የባህር ላይ ወንበዴዎቹን ንብረት ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ፡ የባህር ኃይል ትብብርን ማጠናከር እና ከመርከቦች ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ በመስራት አደጋኛ የሆነውን የባህር ክልል አስተማማኝ ለማድረግ መጣር መሆኑን ከጥቂት ቀናት በፊት አስታውቀዋል። ክሊንተን አክለው እንዳስረዱትም፡
« ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከባህር ላይ ወንበዴዎች ጋር አትደራደርም፣ ካሣም አትከፍልም። በመጀመሪያ የምናደርገው፣ አንድ የኛ መልዕክተኛ በብራሰልስ በሚካሄደው በዓለም አቀፉ፣ የሶማልያ የሰላምና የልማት ጉዳይ ጉባዔ እንዲሳተፍ እንልካለን። ለሶማልያው የባህር ላይ ውንብድና፡ ከመፍትሄዎቹ አንዱ፡ ሀገሪቱ፡ ግዛቷን መቆጣጠር የሚያስችል ብቃት እንዲኖራት መርዳት ነው። መልዕከተኛችን፣ ከተጓዳኞች ጋር በመተባበር፣ ሶማልያ፣ የባህር ላይ ወንበዴዎቹን ምሽጎች እንድታፈርስና ወጣት ሶማሌዎች፡ ወደ ውንብድና እንዳያመሩ የሚያደርግ መላ ትሻ ዘንድ ይደግፋሉ።»
ይሁን እንጂ፡ ሂለሪ ክሊንተን የዘረዘሩዋቸው ርምጃዎች ለአርአያነት ያህል ብቻ እንደሚወሰዱ በታዩበት በዚሁ ጊዜ የዓለም ሀገሮች ባለስልጣናት በባህር ውንብድና አንጻር ሌላ ዲፕሎማቲካዊና የጦር ኃይል ርምጃ የሚነቃቃበትን ሀሳብ በመፈተሽ ላይ ይገኛሉ። በበርካታ የዩኤስ የመገናኛ ብዙኃን ምንጮች ዘገባ መሰረት፡ በባህር ውንብድና አንጻር በጦሩ ርምጃ የመውሰዱ ዕቅድ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ተዘጋጅቶ ይገኛል። ዕለታዊው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ለምሳሌ አሜሪካዊውን የቀድሞ የሶማልያ ልዩ ልዑክ ሮበርት ኦክሊን በመጥቀስ እንደጻፈው፡ የዩኤስ ልዩ የጦር ኃይላት በሶማልያ የምድሩ ላይ ጥቃት የመሰንዘር ዕቅድ አዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ፡ መረጋጋት ወደተጓደለባት፡ የጦር ባላባቶች ፍልሚያ ገና ወዳላበቃባትና የአልሸባብ አክራሪ ሙስሊሞችም ጥቃት ወደሚያካሂዱባት ሀገር የጦር ኃይል ለመላክ ማሰብን ጠበብት እንደ ጅልነት ይመለከቱታል። ሶማልያ እአአ ከ 1991 ዓም የቀድሞው የሀገሪቱ ወታደራዊ መሪ ሲያድ ባሬ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ማዕከላይ መንግስት የሌላ የተመሰቃቀለች ሀገር ሆና ትገኛለች። በዚያም ማዕከላይ መንግስት ለማቋቋም እስከዛሬ የተደረጉ ሙከራዎችም ሁሉ አልተሳኩም።
ሶማልያውያኑ የባህር ላይ ወንበዴዎች ሶስት አባሎቻቸው በዩኤስ አሜሪካ ባህር ኃይል አነጣጣሪ ተኳሾች ከተገደሉባቸውና አንደኛውም ከተማረከባቸው በኋላ ባሰሙት ዛቻ መሰረት፡ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ባካባቢው አራት ዓለም አቀፍ መርከቦችን በቁጥጥር አስገብተዋል። እንደሚታወቀው፡ አደገኛ በሚባለው በሶማልያና በአደን የባህር ክልል መካከል የባህር ኃይል ማሰማራት የባህር ላይ ወንበዴዎችን ሊያስፈራራና የውንብድናውን ተግባር ለመታገል እንደሚረዳ ፍቱን ዘዴ የተመለከቱት የዓለም ሀገሮች፡ የአውሮጳ ህብረት ጭምር ባካባቢው ወደ አንድ መቶ ሀያ የሚጠጉ የባህር ኃይል መርከቦችን አሰማርተዋል፤ ይሁን እንጂ፡ ይኸው ስምሪት የታሰበውን የተሳካ ውጤት አላስገኘም። ለዚህም በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፡ ቡንድስታክ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አንጃ የመከላከያ ጉዳይ ጠቢብ ራነር አርኖልት ተከታዩን ምክንያት ሰጥተዋል።
« በዚሁ የባህር ክልል በርግጥ፡ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ የባህር ላይ ውንብድና በጉልህ ቀንሶ ነበር። አሁን በመሀሉ ግን የባህር ላይ ወንበዴዎች ስልታቸውን ቀይረው ከጠረፉ ራቅ ብለው ነው የሚንቀሳቀሱት። በመርከቦች አንጻርም ጠንካራና ፈጣን ርምጃ ይወስዳሉ። ችግሩ በባህር ላይ ወንበዴዎች ቁጥጥር ስር የዋሉት መርከቦች ለባህር ላይ ወንበዴዎች ጥቃት የተጋለጡት ዓለም አቀፉ የባህር ኃይል የከለላ አጀብ ከሚሰጥበት ክልል ውጭ ሲንቀሳቀሱ ነው። እና የንግድ መርከቦቹ ባለቤት ኩባንያዎች እና የመርከቦቹ ካፒቴኖች ምንም እንኳን አጀብ የማግኘቱ ሁኔታ ጥቂት ጊዜ ቢያስጠብቅምና ተጨማሪ ጥቂት ሺህ ዶላር ቢያስወጣቸውም ይህንን ዕድል እንዲጠቀሙበት መገፋፋት ይኖርብናል። »
የጀርመን ነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ «አታላንታ» በተባለው የአውሮጳ ህብረት ጸረ የባህር ላይ ውንብድና ተልዕኮ ስር የአደን ባህረ ሰላጤን የሚቆጣጠሩት ጀርመናውያን ወታደሮች ስምሪት በሚገባ ሊቀነባበርል እንደሚገባ አሳስቦዋል። እስካሁን እንደሚታየው፡ ከሚቆጠጠሩት የባህር ክልል ውጭ የባህር ላይ ወንበዴዎች መርከቦች ላይ ጥቃት ሲጣል ርምጃ ሳይወስዱ ማየት የተገደዱበት ሁኔታ አለ። ይህ ሁኔታ ሊቀየር ይገባል የሚለው ይኸው ፓርቲው የባህር ላይ ወንበዴዎች በፈጣኖቹ ጀልባዎች ለሚያካሂዱት ጥቃት እንደመነሻ በሚጠቀሙባቸው መርከቦች ላይ ወታደራዊ ርምጃ የሚወሰድበትን ሀሳብ አቅርቦዋል። ይሁንና፡ በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፡ ቡንድስታክ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አንጃ የመከላከያ ጉዳይ ጠቢብ ራነር አርኖልት ሀሳቡ ያልተፈለገ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል በሚል አልደገፉትም።
« የጀርመን ብሄራዊ ጦር የሚሰራበትን መመሪያውን እንደጠበቀ መቆየት ይኖርበታል። ተመጣጣኝ የሆነ ርምጃ ነው መወሰድ ያለበት። የባህር ላይ ወንበዴዎች እንደመነሻ የሚጠቀሙበት መርከብ እንደ ማንኛውም የአሳ አስጋሪ መርከብ ሊመስል ስለሚችል ስህተት ሊሰራ ይችላል፤ ልክ ያኔ ህንዳውያኑ የባህር ኃይል አባላት እንደሆኑት። እና እንዲህ ዓይነት ስህተት ሊፈጸም አይገባም። የባህር ላይ ወንበዴዎችን መርከብ ከሰላማዊ የሲቭል መርከብ የመለየቱ ሂደት ቀላል አይደለም። መርከቡ የባህር ላይ ወንበዴዎች መርከብ መሆኑ በርግጥ ከተወቀ ግን ርምጃ መውሰዱ አይከብድም። ይህ ማለት ግን፡መርከቢቱን ወዲያውኑ ማስመጥ ማለት አይደለም። የባህር ኃይሉ በርካታ አማራጮች አሉት። መርከቢቱን እንዳትንቀሳቀስ ማድረግና የባህር ላይ ወንበዴዎቹን ማስራብ ይቻላል። »
የጀርመን ባለስልጣን የባህር ላይ ውንብድናን ለማስቆም ጥረት መጀመራቸውን ሰሞኑን ያስታወቀው የጀርመን መከላከያ ሚንስቴር በባህር ላይ ወንበዴዎች መርከብ ላይ ጥቃት የመሰንዘሩን ርምጃ እንደመጀመሪያው አማራጭ እንደማይመለከት ግልጽ አድርጎዋል። በዚህ ፈንታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ መንስዔ መፍትሄ በማፈላለጉ ረገድ፡ ማለትም፡ የሶማልያን ውዝግብ ለማብቃትና የሽግግሩን መንግስት ለማጠናከር ጠንክሮ እንዲሰራ የመከላከያ ሚንስቴር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ኮሴንዲ ጠይቀዋል። በሶማልያ ሰላምና መረጋጋት ካልወረደ በስተቀር፡ የባህር ላይ ውንብድናን በተሳካ ዘዴ መታገል እንደማይቻል ኮሴንዲ በማሳወቅ፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሶማልያ የሽግግር መንግስት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

DW/DPA/AA/SL