1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የልማት ገንዘብ ማፈላለጊያ ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7 2007

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት በብራዚሏ የሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ ባደረጉት ጉባኤ የምዕተ-ዓመቱን የልማት ግቦች በዘላቂ የልማት ግቦች ለመተካት መወሰናቸው ይታወሳል። አዲሱ ዘላቂ የልማት ግቦች ጽንሰ ሃሳብ በጥልቀት ተተንትኖ ባይቀርብም የተለጠጠ እቅድና ከፍተኛ ገንዘብ ይጠይቃል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1FyXg
Äthiopien International Conference on Financing for Development in Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

[No title]

የተለያዩ አገራት መሪዎች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ፖሊሲ አውጪዎች፤ ባለወረቶች፤ የመዋዕለንዋይ ተንታኞች እና አደራዳሪዎች ለሶስተኛው የልማት ማፈላለጊያ ጉባኤ አዲስ አበባ ከከተሙ ዛሬ ሁለተኛ ቀናቸው ነው። ጉባኤው በዚህ ዓመት የሚጠናቀቀውን የምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች ለሚተካው ዘላቂ የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals) ማሳኪያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማስገኘት በሚቻልበት ፤ በተደቀኑበት ፈተናዎች እና በትግበራቸው ላይ ይመክራል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሪዮ ዲ ጄኔሮ ጉባኤ ቀርቦ ተቀባይነት ያገኘው አዲሱ ዘላቂ የልማት ግቦች ካሁን ቀደም ከነበሩት ሁሉ ውድ እና የማይሳካ የሚመስል የተለጠጠ እቅድ ይዞ መጥቷል። ስለእቅዱ በጉባኤው ከተሳተፉት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቆንስጠንጢኖስ በርኸ «ድህነትን እስከናካቴው ለማጥፋት እቅድ ተይዟል። ይህንንም ለማድረግ 25 ትሪሊየን ዶላር ያስፈልጋል ነው የሚባለው።» ሲሉ ስለ እቅዱ ያብራራሉ።

Äthiopien International Conference on Financing for Development in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/dpa/M. Wondimu Hailu

ለመጪዎቹ አስራ አምስት አመታት የታለመው የአዲሱ ዘላቂ የልማት ግቦች እቅዶች ገና በዝርዝር ባይቀመጡም በዋናነት ሶስት ዓላማዎች አሉት። አካታች ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማበረታታት፤ተፈጥሮን መጠበቅና ማህበራዊ ተሳትፎን ማበረታታት የሚሉ ጠቅለል ያሉ እቅዶች ሰንቋል። በምዕተ-ዓመቱ የልማት ግቦች ትግበራ ትኩረት አግኝተው የነበሩት እርዳታ እና የእዳ ስረዛ ውይይቶች ተቀይረዋል። በአሁኑ የዘላቂ ልማት ግቦች በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች የራሳቸውን አስተዋጽዖ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። ገንዘቡ ከየት ይመጣል? «ከአፍሪካ እየተሰረቀ የሚሄደውን ገንዘብ ማስቀረትና መቆጣጠር፤ ነዳጅና ሃብት ያላቸው የአፍሪካ አገሮች ከአፍሪካ ልማት ባንክ ቦንድ እየገዙ ገንዘብ እየተሰበሰበ ወደ ልማት ማዋልና ከውጭ በሚመጣ መዋዕለ ንዋይ( Foreign Direct Investment)» የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በገንዘብ ምንጭነት እንዲያገለግሉ መታሰቡን ዶ/ር ቆንስጠንጢኖስ በርኸ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባው የልማት ገንዘብ ፍለጋ ጉባኤ በፊት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ያደረገው የዘላቂ ልማት እቅዶች የውይይት መርሃ-ግብር አዲሱ እቅድ ለሰብዓዊ መብት እና የጾታ እኩልነት ቦታ እንዳለው ይፋ አድርጓል።

ከጉባኤው ቀደም ብሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና ማህበረሰብ አቀፍ ተቋማት በታደሙበት የውይይት መድረክ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማነት የሚኖራቸውን ከፍተኛ ሚና ተናግረዋል። «አሁን ዓለም ከሌላው ጊዜ በተለየ የእናንተን የማግባባት ስራ፤ሙያ እና ችግሮችን በአዳዲስ ፈጠራ የመፍታት ብልሃት ይፈልጋል።» ሲሉ ለሰብዓዊ መብት ተሟጋችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተናገሩት ባንኪ ሙን ተቋማቱ ለሰው ልጆች ደህንነትና የዓለም ጤና የሚያደርጉትን ተጋድሎ ከጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. በኋላም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። የባንኪ ሙን ሃሳብ ግን እንደ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ባሉ አገሮች መንግስታት የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ሚና የሚገድቡ አዋጆች በማውጣታቸው ተግባራዊነቱ አዳጋች ይመስላል። ዶ/ር ቆንስጠንጢኖስ በርኸ እንደሚሉትም፣ ይኸው ጉባኤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚገጥሟቸው ፈተናዎችም ላይ እየመከረ ነው።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ