1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ መከፈት

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2003

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ከፖለቲካ፡ ከኤኮኖሚው እና ከስነ ጥበቡ ዘርፍ የተውጣጡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ልዑካን በተገኙበት ዛሬ በቦን ከተማ በሚገኘው ዶይቸ ቬለ ተከፈተ።

https://p.dw.com/p/RUlI
ምስል DW

በዚሁ ሶስት ቀናት በሚቆየው « የሰብዓዊ መብት እና ግሎባላይዜሽን - የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ፈተና » በሚል ርዕስ የሚካሄደውን የውይይት መድረክ የከፈቱት የዶይቸ ቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ኤሪክ ቤተርማን የዐረቡ ዓለም ህዝብ ለነጻነት እና ለሰብዓዊ መብቱ ያካሄደውን ዓብዮት አሞግሰዋል።

« የመገናኛ ብዙኃን የሰብዓዊ መብት በማስጠበቁ ጠንካራ መሳሪያ ሊሆን ይችላል። እንደ መረጃ ድልድይ እና እንደ ገለጻ ሰጪ መሳሪያ። ማህበራዊው መገናኛ ብዙኃን፡ በተለይ፡ ፌስቡክ፡ ትዊተር እና ድረ መጽሄት አዲስ ተጽዕኖ አሳርፈዋል። አገናኚ ሞተሮች እና የተቃውሞ ንቅናቄዎች አራማጆችም ናቸው። »

የኢንተርኔቱ የመገናኛ ብዙኃን አዎንታዊ ሚና እንዳለው ሁሉ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ሚስተር ቤተርማን በማስረዳት፡ የመገናኛ ብዙኃን የተሸከሙትን ኃላፊነት በሚገባ ለሚወጡበት ድርጊት ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚሁ አጋጣሚ አንዲት ቱኒዝያዊት የዩኒቨርሲቲ መምህር በኢንተርኔት መረጃ በማዳረስ በቱኒዝያ ለተቀሰቀሰው የህዝብ ዓመጽ ድፍረት የተላበሰ አስተዋጽዖ በማበርከትዋ ዛሬ በዚሁ ዝግጅት ሽልማት ሰጥተዋል።

አርያም ተክሌ