1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓመታዊዉ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዘገባ

ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2006

«አፍሪቃ የምትፈልገዉ ተግባር ነዉ፤ አፍሪቃ ወደ ተግባር እንድትገባ ከተፈለገ፤ አፍሪቃ የራስዋን ወይም ደግሞ ሀገሮች፤ የራሳቸዉን ፍላጎት፤ ሌሎችን በመጠበቅ ሳይሆን፤ በራሳቸዉን መወሰን መቻል አለባቸዉ» የኤኮነሚ ጉዳይ ምሁሩ ደምስ ጫንያለዉ፤ የአፍሪቃን ዓመታዊ የኤኮነሚ ዘገባን በተመለከተ የተናገሩት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1BzWE
ECA Wirtschaftskommission Afrika Addis Abeba Äthiopien
ምስል DW

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ የተመ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ለአፍሪቃ በእንግሊዘኛ ምህፃሩ በኢሲኤና በአፍሪቃ ኅብረት የተዘጋጀ ዓመታዊ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዘገባ ቀርቦአል። ይህ በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ የሚያተኩረዉ ዓመታዊ ዘገባ የተባበሩት መንግሥታት የዓመዓቱ የልማት ግቦች ካስቀመጣቸዉ የአፍሪቃ ልማት እና ኤኮኖሚ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማጤን በየዓመቱ የሚዘጋጅ እንደሆነ ተመልክቶአል። የዘንድሮዉ ስብሰባ « ፈጣን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአፍሪቃ» በሚል የተዘጋጀና በተለይ በአፍሪቃ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነበር። በኢስኤ በተዘጋጀዉ ስነ-ስርዓት ላይ ከአፍሪቃ ኅብረት፤ ከተመ የአፍሪቃ ጉዳይ ኮሚሽን፤ የኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁራን እና ባለሞያዎች፤ እንዲሁም በኤኮኖሚ የግል ዘርፎችን ያካተተ ከ 500 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ነበር። በለቱ ዝግጅታችን በወቅታዊ የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ማብራርያ የሚሰጡንን የኤኮኖሚ ባለሞያ ዶክተር ደምስ ጫን ጋብዘናል ።
በአፍሪቃ ገበያ የማጣትን ችግር ለማስወገድ ከተፈለገ በኢንዱስትሪ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ግዴታ አስፈላጊ መሆኑ ባለፈዉ ሰኞ አዲስ አበባ በተመ የኤኮኖሚ ኮሚሽን ለአፍሪቃ «ኢሲኤ» ዉስጥ በተዘጋጀዉ ስብሰባ ላይ ተነግሮአል። ስብሰባዉን በንግግር የከፈቱት የECA ም/ተጠሪ አብደላ ሃሞክ ፤ የአፍሪቃ የወቅቱ የምጣኔ ሃብት እድገት አስተማማኝ መሆኑን ገልፀዋል። በአፍሪቃ አህጉር የሚታየዉ የማይክሮ ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አረጋግጠናል ሲሉ የኢሲኤ ም/ ተጠሪ በሥነ- ስርዓቱ መክፈቻ ተናግረዋል። አፍሪቃ የተሻለ ኤኮኖሚ ደረጃን እንድትይዝ የኢንዱስትሪዉን ዘርፍ ማጠናከር እንደሚገባም ተመልክቶአል። ለሶስት አስርተ ዓመታት በኤኮኖሚዉ ዘርፍ በማገልገልና ምክር የሚሰጡት የግብርና ኤኮኖሚ ባለሞያ ዶክተር ደምስ ጫንያለዉ እንደሚሉት በአፍሪቃ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማጠናከር አለብን ከማለታችን በፊት አፍሪቃ ያለችበት ቦታ የት ነዉ ብለን ልንጠይቅ ይገባናል ባይ ናቸዉ። ኢሲኤ በተዘጋጀዉ ሥነ-ስርዓት ላይ የወቅቱ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ እድገት አመርቂ መሆኑ ተነግሮአል። በተለይም የማይክሮ ኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ማደጉ ነዉ የተገለፀዉ። ይህ እድገት እንዴት ይታያል፤ ማይክሮ ኤኮኖሚስ ስንልስ ምን ማለታችን ይሆን፤ የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለሞያዉ ዶክተር ደምስ ጫንያለዉ፤ ሰፊ ማብራርያ ሰተዉናል።
በአፍሪቃ የተመ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦችን በተመለከተ በየዓመቱ በሚዘጋጀዉ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ሪፖርት እንደሚያመለክተዉ « የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት እድገት አስተማማኝ ነዉ» የግብርና ኤኮኖሚ ባለሞያዉ ዶክተር ደምስ ጫንያለዉ እንደሚሉት፤ ሁላችንም ለአፍሪቃ በጎን ነገርን ብንመኝም አባባሎች እና ተግባር የተለያዩ መሆናቸዉን መዘንጋት የለብንም። በአፍሪቃ ሃገራት ዉስጥ አንዱ ሀገር ከሌላዉ ጋር የሚያደርገዉ የንግድ ልዉዉጥ፤ ለሀገራቱ እድገት የሚያስገኝና፤ የአንዱን ሀገር ሸቀጥ ከሌላዉ የተለየ በመሆኑ ለኢንዱስትሪዉም አመች መሆኑም ተገልፆአል። በዚህ አንጻር ዩጋንዳ የኬንያ ዋንኛ የንግድ አጋር መሆናቸዉ የ«ኢሲኤ»የማይክሮ ኤኮኖሚ ክፍል ተጠሪ አዳም ኤልሪአካ፤ በስነ ሥርዓቱ ላይ ገልፀዋል። በሀገራት መካከል የሚደረገዉ የንግድ ልዉዉጥ በጠነክር ለኤኮኖሚዉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ የሚገልፁት የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለሞያዉ ዶክተር ደምስ ጫንያለዉ ቢሆንም፤ የአፍሪቃ በሀገራት በንግድ ልዉዉጡ ገና ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከትናንት በስታያ አዲስ አበባ «ኢሲኤ» ዉስጥ በተካሄደዉ ሥብሰባ በአፍሪቃ የግል ንግድ ዘርፎች ከመንግሥት ጋር አብረዉ መራመድ እንዳለባቸዉ፤ በዚህ አኳያ ግን እስካሁን እንደተፈለገዉ ለማጣመር አልተቻለም ተነግሮአል። የኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁሩ ዶክተር ደምስ ጫንያለዉ፤ በበኩላቸዉ መንግስትና የግሉ ዘርፍ አልተጣመረም ማለት እንደማይቻል፤ በመግለፅ በአፍሪቃ በተለይ በግብርናዉ ዘርፍ መንግሥት እኩል ሊራመድ ይገባዋል ብለዋል። የአፍሪቃ ዓመታዊ የኤኮኖሚ ሪፖርትን ይዘን በተለያዩ ነጥቦች ላይ ማብራርያ ከሰጡን ከኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁሩ ከዶክተር ደምስ ጫንያለዉ ጋር፤ ያደረግነዉን ሙሉ ዉይይት የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ!
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

ECA Wirtschaftskommission Afrika Addis Abeba Äthiopien
ምስል DW
ECA Wirtschaftskommission Afrika Addis Abeba Äthiopien
ምስል DW