1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘመናዊ የእርሻ ልማት ቴክኖሎጂ

ሐሙስ፣ ኅዳር 10 2002

በዓለም ላይ እየተስፋፋ መሄዱን የቀጠለውን ረሃብ ለመቋቋም የምግብ ምርትን ማሳደጉ የማይቀር ግድ ነው።

https://p.dw.com/p/KZD9
አግሪ-ቴክኒካ፤ የዘመናዊ የእርሻ ልማት ቴክኖሎጂ ትዕይንት በጀርመን-ሃኖቨር
አግሪ-ቴክኒካ፤ የዘመናዊ የእርሻ ልማት ቴክኖሎጂ ትዕይንት በጀርመን-ሃኖቨርምስል DLG-Pressestelle

ዛሬ በዓለም ገበያ ላይ የሚቀርበው የእርሻ ምርት የአያሌ ድሆችን አንጀት በማስታገስ ፈንታ ለበለጸገው ዓለም የከብት ቀለብና የባዮ-ኤነርጂ ምንጭ እየሆነ መሄዱም ጨምሯል። እናም በወቅቱ የዓለም ረሃብተኛ ቁጥር እየናረ ከአንድ ሚሊያርድ በላይ ዘልቆ ነው የሚገኘው። ለዚሁ ምክንያቱና መፍትሄውም እርግጥ ዘርፈ-ብዙ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የዓለም ሕዝብ ቁጥር በሰፊው እየጨመረ መሄድ ችግሩን ይበልጥ የሚያከብደው ሲሆን የእርሻ ልማትን በዘመናዊ መልክ ብቁ ማድረጉ አንዱ መንገድ ሆኖ ነው የሚታየው። በዚህ በጀርመን ሃኖቨር ከተማ ላይ ባለፈው ሣምንት ይህንኑ ማተኮሪያው ያደረገ አምሥት ቀናት የፈጀ “አግሪ-ቴክኒካ” በመባል የሚታወቅ ዓለምአቀፍ ትዕይንት-ኤግዚቢሽን ተካሂዶ ነበር። በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ጥበብ የሚካሄድ የእርሻ ልማት የወደፊቱ ፍቱን መፍትሄ እንደሚሆን ተሥፋ የሚያደርጉት የዘርፉ ጠበብት ብዙዎች ናቸው።

እርግጥ ጥቂት የሚያሳዝነው የሃኖቨሩ አግሪ-ቴክኒካ ትዕይንት በባለሙያዎች ወይም በዘርፉ የንግድ ሰዎች ብቻ የሚጎበኝ መሆኑ ነው። ትዕይንቱ ለተራው ሕዝብ ክፍት ቢሆን ኖሮ የዘመናዊ እርሻ መኪናዎቹ ርቀት ምናልባት ከሕጻን እስከ ሽማግሌ የሁሉንም ቀልብ ሊስብ በቻለ ነበር። ለማንኛውም በተለያዩት የትዕይንት አዳራሾች ውስጥ ከትንሽ እስከ ግዙፍ አዳዲስ ሃይ-ቴክ የእርሻ መኪናዎች ተደርድረው ሲደነቁና ሲስተዋሉ ሰንብተዋል። አንዳንዶቹ ለምሳሌ መውቃትን፣ መፈልፈልን ወይም ጭኖ ማመላለስን በተቀላጠፈ ሁኔታና ብዙ ኤነርጂ ሳይጠይቁ ለማከናወን ይችላሉ። የአውስትሪያው ኩባንያ ባልደረባ ካርል ማይቦክ ከቦታው እንዳስረዱት አዳዲሶቹ መኪናዎች በአጠቃቀም ረገድም በቀላሉ ሥራ ላይ እንዲውሉ ሆነው የታነጹ ናቸው።

“ይህ የሚመለከቱት አልትራ-ላይት 800 የተሰኘ ተሸላሚ መቆራረጫ መኪና ነው። ዛሬ በአግሮ-ቴክኒካ ትዕይንት ላይ የብር ሜዳሊያ ተሽላሚ ሆኗል። ከእህል እስከ ጥራጥሬ የተለያዩ ዘሮችን ለመውቃት የሚያስችል ሁል-ገብ መቆራረጫ ይዘት አለው። ከአሉሚኒየም፤ ማለት ክብደት ከሌለው ብረት የተሰራ ሲሆን አስተናነጹ ቀላልና እስከ 14 ሜትር ተፈትቶ ሊረዝም የሚችልም ነው”

ከዚሁ መሣሪያ ጥቂት ሜትሮች ፈንጥር ብሎ ደግሞ ጎማዎቹ ከሰው ቁመት የማይተናነሱ ይበልጥ ግዙፍ የሆነ መኪና ቆሟል። የዘዋሪው መቀመጫ አምሥት ሜትር ያህል ከፍ ብሎ የተሰቀለ ነው። ስፋቱ አሥር ሜትር ገደማ ይጠጋል። ከጀርመን የእርሻ ልማት ኩባንያዎች ባልደረቦች አንዱ እንደሆኑት እንደ አልፍሬድ ካስማን አገላለጽ ይህ ፍራንስ በተሰኘው ኩባንያ የቀረበው መኪናም ኤኮኖሚያዊ ለሆነ አመራረት እጅግ የሚስማማ ነው።

“ይህ መኪና ፕሮፌሺናል በሆነ መንገድ ስኳር ድንችን ለመጫን የሚያገለግል ነው። እሥር ሜትር ስፋት አለው። በጥቂት የናፍጣ ፍጆት በስድሥት ደቂቃዎች ውስጥ ሰላሣ ቶን ስኳር ድንች ለመጫን ያስችላል። በ 2 ሊትር ያህል ናፍጣ ማለት ነው። ከዚህ የረከሰ ነገር ሊኖር አይችልም”

የእርሻ ቴክኖሎጂው ትዕይንት አግሪ-ቴክኒካ በአጠቃላይ ተሳታፊውን በጣሙን የማረከ ሆኖ ነው ያለፈው። የብዙዎቹን ኩባንያዎች የወደፊት ተሥፋ ያዳበረ ነበር ለማለት ይቻላል። በትዕይንቱ ላይ 46 አገሮችን የሚጠቀልሉ 2,300 የኤግዚቪሽን ምርት አቅራቢዎች ሲሳተፉ ከነዚሁ 1,100 የሚሆኑት ደግሞ ከውጭ የመጡ ነበሩ። ይህም ከአራት ዓመታት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር እጥፍ መሆኑ ነው። በተረፈ በትዕይንቱ ላይ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖ ብዙም ጎልቶ አልታየም። ከሞላ-ጎደል ስር ሳይሰድ ያለፈው ነው የሚመስለው። ለዚህም የጀርመን የእርሻ ልማት ማሕበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ራይንሃርድ ግራንድከ እንደሚሉት ምክንያት አልጠፋም።

“የእርሻ ልማት ቁልፍ የሆነው የልማት መስክ ብቻ አይደለም። የወደፊቱም ዕድገት ዘርፍ እንጂ! በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ስሌት ሁሉም ሂደት በእርሻ ልማት ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው”

ሂደቱ በዕውነትም ግልጽ ነው። በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በፋኦ ግምት መሠረት በ 2050 ዓ.ም. ገደማ በምድራችን ላይ የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ዘጠኝ ሚሊዮን እንደሚደርስ ይታመናል። እንግዲህ ዓለም ይህን ያህል ሕዝብ መቀለብ ይኖርበታል ማለት ነው። በሌላ በኩል ይሁንና ለእርሻ ልማት የሚሆነው መሬት እንደሰዉ ቁጥር ሊባዛ ወይም ሊሰፋ የሚችል አይደለም። ይልቁንም በአካባቢ አየር ለውጥ የተነሣ በዓለም ዙሪያ ብዙ መሬት እየደረቀና የዝናቡም ሁኔታ ይበልጥ ሚዛን ያልጠበቀ እየሆነ፤ ጎርፍ እያየለ ሲሄድ ነው ከወዲሁ የሚታየው። በፋኦና በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት እስከ 2050 ዓ.ም. ለእያንዳንዱ ሰው ለእርሻ የሚቀረው መሬት ከሁለት ካሪ-ሜትር የሚበልጥ አይሆንም። ለግንዛቤ ይህል ከስልሣ ዓመታት ገደማ በፊት ይሄው አምሥት ካሪ-ሜትር ገደማ ነበር።

ሁለተኛው ምክንያት በጣሙን እያደገ የሚሄደው የባዮ-ኤነርጂ ፍላጎትና ፍጆት ነው። በዚሁ የተነሣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደጊዜ ይበልጥ መሬት ለዚሁ ምንጭ የሚሆኑ ተክሎችን ለማምረት ጥቅም ላይ ሲውል ነው የሚታየው። ይህም ለምግብ ምርት የሚሆነውን መሬት ክፉኛ እየተሻማ ይሄዳል ማለት ነው። ከዚህ አንጻር ችግሩን ለመቋቋም ከዓለም የፖለቲካ ተሃድሶ ባሻገር ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ ለማስፈለጉ አንድና ሁለት የለውም። የዚሁ ዘመናዊ የእርሻ ልማት ቴክኖሎጂ ገበያ መጠን ባለፈው 2008 ዓ.ም. በዓለምአቀፍ ደረጃ 67 ሚሊያርድ ኤውሮ ደርሶ ነበር። እርግጥ የጀርመን የእርሻ መሬት ቴክኒክ የሙያ ማሕበር ሥራ አስኪያጅ በርንድ ሼረር እንደሚያስረዱት ዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሂደቱን ብዙ ባያውክም በጥቂቱም ቢሆን ሳይጎትተው አይቀርም።

“በዚህ ዓመት በጀርመን የመሬት ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 25 በመቶ ገደማ የምርት ማቆልቆል ይኖራል ብለን እንጠብቃለን። በዚሁ በ 2006 እና በ 2007 መካከል በነበረው መጠን እንወሰናለን ማለት ነው። በዓለምአቀፍ ደረጃም ምርቱ በዓመቱ ሂደት ተመሳሳይ ማቆልቆል ያሳያል ባይ ነኝ”

ይህም ሆኖ ግን በዚህ በጀርመን ሰላሣ ሺህ ሰዎችን በሥራ ያሰማራውና 7,5 ሚሊያርድ ኤውሮ በጀት ያለው ዘርፍ ቋሚ ተቀጣሪዎቹን እንደያዘ ለመቀጠል ነው የሚያስበው። ምክንያቱም መልሶ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ እንደማይቀር ጽኑ ዕምነት አለ። ለነገሩ በእርሻው ልማት ዘርፍ ውዥቀት በየጊዜው መፈራረቁ ያልተለመደ ነገር አይደለም። በሌላ በኩል ግን የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ፍላጎት ማቆልቆል ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።

“በመካከለኛና በምሥራቅ አውሮፓ ገበዮች የዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ በተለይም እነዚህ አገሮች የእርሻ ልማት ቴክኖሊጂ መሣሪያዎችን በአብዛኛው በውጭ ገንዘብ ያስገቡ ስለነበር በፍጥነት ተጽዕኖ ማሳደሩ የሚታይ ነው። እርግጥ በተመሳሳይ ጊዜ ብዙ የአካባቢው ገበዮች ለጀርመን ምርቶች ሰፊ ተቀባዮች እየሆኑ ሄደዋል። ጀርመን በአንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች እንዲያውም ዛሬም ቢሆን ዋነኛዋ የእርሻ ልማት ቴክኖሎጂ አቅራቢ ናት”

በሌላ በኩል ዘርፉ ቀውሱን በመጠቀም የነጻ ገበያ እገዳን መሣሪያ አድርጋ በምትጠቀመው በሩሢያ ላይ ቅሬታ ማሰማቱ አልቀረም። ሩሢያ ወደ አገር በሚገቡ የእርሻ ቴክኒክ መሣሪያዎች ላይ የምታስከፍለውን ቀረጥ በ 15 ከመቶ ከፍ አድርጋለች። ዕርምጃው ትራክተሮችንና ጎታች መኪናዎችን በተመለከተ በኪሎዋት አቅም ተጨማሪ 120 ኤውሮ ወጪ መሆኑ ነው። ይህ የሚደረገው ደግሞ ብዙም ያልተስፋፋውን የሩሢያን የትራክተር ወይም የእርሻ መኪና ኢንዱስትሪ ከጠንካራ የውጭ ፉክክር ለማዳን በሚል ነው። ግን ፉክክሩ አገር ከገባ ውሎ አድሯል።

“ምዕራባውያን አምራቾች ቢያንስ ሶሥታችን ለፉክክሩ ቀርበናል። ሩሢያ ማራኪ ገበያ ያላት ሲሆን እኛም የዚህ ተጠቃሚ ለመሆን እንፈልጋለን። ለሁሉም ቦታ አለ ብዬ ነው የማስበው። እናም በዚያም ቢሆን የማታ ማታ በተቀረው ዓለም የተለመደው ፉክክር መስፈኑ የማይቀር ነው”

ይህን የሚሉት በዓለም ላይ ሁለተኛው ታላቅ የእርሻ መኪናዎች አምራች የሆነው የጀርመን ኩባንያ የአግኮ ፕሬዚደንትና ሊቀ-መንበር ማርቲን ሪሸንሃገን ናቸው። ሪሸንሃገን እኛ ሶሥታችን የሚሉት የራሳቸውን ኩባንያና የአሜሪካውን ቀደምት የዓለም ገበያ መሪ ጆን ዴርን፤ እንዲሁም ክላስ የተሰኘውን ሌላ የጀርመን የቤተሰብ ኩባንያ ነው። በሃኖቨሩ አግሮ-ቴክኒካ ሶሥቱ ኩባንያዎች ጎን ለጎን በመሰለፍ ቀና ፉክክር ሲያደርጉ ሰንብተዋል። እነዚህ በወደፊቱ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ ኩባንያዎች እርግጥ እንደ ሌሎች ዘርፎች በከፋ ፉክክር አለመጠመዳቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ ብዙ ተፈታታኝ ስለሌላቸውም ነው። ከፍተኛ ቴክኖሎጂ በእርሻው ልማት ዘርፍ! በቅርቡ በየእርሻው መሬት ሮቦቶች ሲንቀሳቀሱ የሚታይበት ጊዜ መቃረቡ ይሆን? የሃኖቨሩ አግሪ-ቴክኒካ ትዕይንት ዘመናዊው ዕውቀት እየመጠቀ መሄዱን አመልክቷል። ሆኖም ግን ትራክተሮች ያለ ሰው የሚዘወሩበት ጊዜ ዕለታዊ እስኪሆን በተለያዩ ምክንያቶች ገና ጊዜ መፍጀቱ የማይቀር ነው።

MM/DW