1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዘረመሉ የተለወጠ ዘር ጣጣ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 5 2008

ጥጥ የቡርኪናፋሶ «ነጩ ወርቅ» በመባል የሚታወቅ ምርቷ ነዉ። ለበርካታ አስርት ዓመታት የምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር የጥጥ ምርት ከአህጉሩ በምርጥነቱ ይታወቅ ነበር። በ1990ዎቹ የተከሰቱት ጥጥ አምካኝ ተባዮች እና ድርቅ የቡርኪናፋሶን የጥጥ ምርት እንዳልነበረ አዉድሞ አምራቾቿን ለክስረት ዳርጓል።

https://p.dw.com/p/1JNmP
Burkina Faso Baumwolle Farm
ምስል Getty Images/I.Sanogo

ዘረ መሉ የተለወጠ ዘር ጣጣ

ቡርኪናፋሶ የጥጥ ምርቷን የሚጎዳ ቀዉስ ሲገጥማት ሞንሳንቶ በመባል የሚታወቀዉ የአዝርዕትን ዘረመል በቴክኒዊሎጂ በመለወጥ ተግባር የተሰማራ ድርጅት ችግር መቋቋም የሚችል ዘረመሉ የተለወጠ ጥጥን ማብቀል ብትጀምር ይህ እንደማይከሰት እና የምርቱም መጠን ከፍ እንደሚል መፍትሄ በሚል ሃሳቡን ያቀረበዉ። ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2003ዓ,ም አንስቶም የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ለዚሁ ጉዳይ ከሞንሳንቶ ጋር ዉል ተፈራረመ። ዘረመሉ የተለወጠዉ የጥጥ ዘር ለጥጥ አምራች ገበሬዎቹ ታደለ። 70 በመቶ የሚሆነዉ የጥጥ ማብቀያ ሄክታር መሬትም ዘረመሉ በተለወጠ የጥጥ ዘር ተሸፈነ። የተገኘዉ ዉጤት ግን ዘላቂነት አልነበረዉም።

ዉሎ አድሮ ነገሮች ተለዋወጡ፤ የቡርኪናፋሶ ፕሬዝደንት ሮኽ ማርክ ካቦሬ በሚያዚያ ወር ላይ ከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2018 ጀምሮ ዘረመሉ የተለወጠ ጥጥ በሀገራቸዉ መሬት ላይ እንደማይዘራ ተናገሩ። ቀደም ሲል የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋቾች ርምጃዉን በይፋ ሲተቹ ሰሚ አላገኙም ነበር። ፕሬዝደንቱ አሁን ለምን ከዚህ ዉሳኔ ላይ ደረሱ? ጥጥ አምራች ገበሬዎቹ ዘረመሉ የተለወጠዉ ጥጥ እንደማንኛዉም ጥጥ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሚቀርብ መሆኑን ቢያምኑም ጥራቱ እንደ ነባሩ ጥጥ እንዳልሆነ፣ በዓለም ገበያ ላይም ተፈላጊነቱ ቀንሶ ዋጋዉ ዝቅተኛ በመሆኑም ገቢያቸዉ ሲያሽቆለቁል አስተዉለዉ ቁጣቸዉ ግሎ ሲያማርሩ ከርመዋል። የቡርኪናፋሶ ሦስት ግዙፍ የጥጥ አምራቾች እና የጥጥ አምራቾች ማኅበራት እንደሚሉት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 እስከ 2016ዓለም ባሉት ጊዜያት የ82 ሚሊዮን ዶላር ክስረት ደርሶባቸዋል። ዘረመሉ የተለወጠ የጥጥ ዘር ያቀረበላቸዉ ሞንሳንቶም ካሳ እንዲከፍላቸዉ ጠይቀዋል። ሆኖም ድርጅቱ የቀረበበትን ወቀሳ በቀላሉ የሚቀበል አልሆነም፤ እንደዉም አምራቾቹ ከእሱ ያገኙትን የጥጥ ዘር በመዝራታቸዉ የጥጥ ምርታቸዉ መጨመሩን እንዲሁም ብዙ የተባይ ማጥፊያ መጠቀም እንዳላስፈለጋቸዉ በመግለጽ ይሞግታል። ኢትዮጵያዊዉ የዘረመል እና የአዝርዕት ተመራማሪ ዶክተር መላኩ ወረደ ዛሬ ይህ ጉዳይ እንደችግር ቡርኪናፋሶ ላይ ተነስቶ አደባባይ ወጣ እንጂ ነባር ዘሮችን በዘረመል ኢንጂነሪንግ እየለወጡ የአፍሪቃ ሃገራት እንዲጠቀሙበት ሲደረግ እና ሲያከራክር መቆየቱን ገልጸዉልናል።

Gentechnisch veränderte Tomaten
ዘረመሉ የተለወጠ ቲማቲምምስል Getty Images

ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮችን እና የአዝርዕት ተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎችን የሚያቀርበዉ ሞንሳንቶ በቡርኪናፋሶ ጥጥ ብቻ ሳይሆን ከአዉሮጳ ኮሚሽንም በኩልም ጠንከር ያለ ጥያቄ ቀርቦበታል። ድርጅቱ ለአዝርዕት ተባይ ማጥፊያነት የሚያቀርበዉ ግሊፖሴት የተባለ ኬሚካል ለካንሰር ሊያጋልጥ ይጥላል በሚለዉ ክስ ምክንያትም ካለፈዉ ሰኔ ወር አንስቶ ተጨማሪ ምርመራ እና ማረጋገጫ እንዲደረግበት የአዉሮጳ ኅብረት ወስኗል።

ቡርኪና ፋሶ የገጠማትን ኪሳራ በመጥቀስ ዘረመሉ የተቀየረ የጥጥ ዘርን ከእንግዲህ ላለመዝራት ብትወስንም ደቡብ አፍሪቃ፣ ግብፅ እና ሱዳን ይህንኑ የጥጥ ዘር ማምረታቸዉን ቀጥለዋል። ማላዊ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ናይጀሪያ እና ጋና የማሳ ላይ ሙከራዎችን በማካሄድ ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮችን የማብቀል ዉሳኔ በየሀገራቸዉእየተጠባበቁ እንደሚገኙ በደቡብ አፍሪቃ ጆሃንስበርግ የሚገኘዉ የአፍሪቃ ብዝሀ ሕይወት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ሀይደ ስዋንቤ ይናገራሉ።

«ቡርኪና ፋሶ ዉስጥ ችግሩን ካየን በኋላ ናይጀሪያ ዘረመሉ የተለወጠ የጥጥ ዘር እንዲዘራ መፍቀዷ በጣም አስገራሚ ነዉ። ይህ የአፍሪቃ መንግሥታት ቁጭ ብለዉ ከዚህ ቴክኒዎሎጂ ጋር እንዴት ወደፊት መዝለቅ እንደሚቻል እንዲያስቡበት ያደርጋቸዋል ብለን ጠብቀን ነበር። ሆኖም እስካሁን አላደረጉትም።»

የነገሩን አስቸጋሪነት የተረዱት እና የመንግሥታቸዉ ርምጃ ያሳዘናቸዉ ናይጀሪያዉያን ግን ዝም አላሉም። ማሪያን ባሴይ ኦርቩጂ የሕግ ባለሙያ ናቸዉ። ለአካባቢ ተፈጥሮ መብት የሚሟገተዉ የመሬት ወዳጆች የተሰኘዉ ተቋም የናይጀሪያ የሰብያዊ እና የምግብ መብቶች ተሟጋች እና የምግብ ሉዓላዊነት መርሃግብር ሥራ አስኪያጅነት የተሰጠዉ ፈቃድ አጠያያቂ ነዉ ይላሉ።

Gentechnisch veränderte Baumwolle in Burkina Faso
ዘረመሉ የተለወጠዉ የቡርኪናፋሶ ጥጥምስል DW

«ለሞንሳንቶ ፈቃድ ብሔራዊ የብዝሃ ሕይወት ደህንነት አስተዳደር ተቋማችን ነዉ። ርምጃዉ ከፍተኛ ተቃዉሞ አስከትሏል። ምክንያቱም ፈቃዱ የተሰጠበት መንገድ አጠያያቂ ነዉ። ፈቃዱ የተሰጠዉ እሁድ ቀን ሲሆን በማግስቱ ደግሞ በዓል ነበር። አሁን አምስት ሚሊየን የሚሆኑ ጉዳዩ የቆረቆራቸዉ ናይጀሪያዉያን ገበሬዎች፤ ሴቶች፤ ተማሪዎች ሲቪል ማሕበራት ጭምር ፊርማቸዉን አሰባስበዉ ለተቋሙ ልከዋል።»

ግሪንፒስ የተሰኘዉ ለአካባቢ ተፈጥሮ መጠበቅ የሚሟገተዉ ድርጅት እንደሚለዉ በመላዉ ዓለም ከተዘሩት ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮች 90 በመቶዉ የሞንሳንቶ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስም ዘረመላቸዉ የተለወጠ የምግብ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸዉን ታበረታታለች። ሀይደ ስዋንቤ በፃፉት አንድ ጽሑፍ የማይክሮ ሶፍት መሥራች ቢል ጌትስ እና ባለቤታቸዉ ሚሊንዳ ጌትስም አፍሪቃ ዉስጥ የሚከሰተዉን ረሃብ ለመቆጣጠር ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮችን መጠቀም ያስፈልጋል ለሚለዉ ፕሮጀክታቸዉ አማካኝነት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያፈሱ አመልክተዋል። ስዋንቤ እንደሚሉት የአፍሪቃ መንግሥታት ሞንሳንቶን እና የዘረመል ኢንጂነሪንግ እንዲስፋፋ የሚያበረታቱትን አካላት የመቋቋም አቅማቸዉ ደካማ ነዉ።

የጆሃንስበርጉ የአፍሪቃ የብዝሃ ሕይወት ማዕከል እንደሚለዉ 80 በመቶ የሚሆነዉ ምግብ አፍሪቃ ዉስጥ የሚመረተዉ በአነስተኛ ገበሬዎች ነዉ። ዘረመሉ የተለወጠ ዘር ንግድ ዉስጥ ያሉት መክሰራቸዉ አይቀርም። ምክንያቱን በማዕከሉ የምርምር ተግባር የተሰማሩት ሃይዲ ስዋንቤ ይናገራሉ፤

«ቴክኒዎሎጂዉ በጣም ዉድ ነዉ። ዘረመላቸዉ በተለወጠ ዘሮች ለመሥራት ቢያንስ 500 ሄክታር መሬት ያስፈልጋል። በአፍሪቃ ደግሞ በአማካኝ ለእርሻ የሚኖረዉ ከአንድ እና ከአስር ሄክታር መሬት አይበልጥም። ይህም እጅግ ትልቅ ነዉ። ይህ ስኬል ካልተጠበቀ ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮችን ይዞ የትም መድረስ አይቻልም፤ ምክንያቱም በጣም በጣም ዉድ ነዉ።»

Gentechnisch veränderter Mais
ዘረመሉ የተለወጠ በቆሎምስል picture-alliance/dpa

እሳቸዉ እንደሚሉት የደቡብ አፍሪቃ ገበሬዎች ዘረመሉ የተለወጠ የበቆሎ ዘር ለመግዛት ብዙ ገንዘብ ማዉጣት አለባቸዉ። አንዴ ያንን መዝራት ከጀመሩም በየዓመቱ ዘር መግዛት ይኖርባቸዋል። እንደ ነባሩ ዘር ከበቀለዉ ለዘር ብሎ የሚቀነስ የለም። በዚያም ላይ እንደግሊፖሳት ያሉትን ፀረ ሰብል ተባይ መድኃኒቶችም ሆነ ማዳበሪያ ከሞንሳንቶ ይገዛሉ። የአዉሮጳ ኅብረት በጀመረዉ ምርመራ እና አቋም ገፍቶበት የተጠቀሰዉ ፀረ ሰብል ተባይ መድኃኒት ለጤና አስጊነቱን አረጋግጦ ካገደ የአፍሪቃም ሆነ የመካከኛዉ ምሥራቅ ሃገራት ይህን ኬሚካል መጠቀማቸዉ ሊታገድ ይችላል የሚልም ተስፋ አላቸዉ።

በተቃራኒዉ ዘረመላቸዉ የተለወጠ ዘሮችን ለሽያጭ የሚያቀርቡት ድርጅቶች ለአየር ንብረት ለዉጥም ሆነ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዉ ሕዝባቸዉን መመገብ ያልቻሉ ሃገራትን አሁን በሚያደርጉት የማግባባት ስልት በቀላሉ ማንበርከክ እንደሚችሉ ነዉ ባለሙያዎቹ የሚናገሩት። ሞሳንቶን በምሳሌነት ያነሱት ዶክተር መላኩ ወረደ ከ15 ዓመታት በፊት ድርጅቱ ሥራዉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለሚያካሂደዉ ዘመቻ 70 ቢሊዮን ዶላር መድቦ ይንቀሳቀስ እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ