1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዙማ የሥልጣን ዘመን

ዓርብ፣ ጥር 19 2009

የደቡብ አፍሪቃዊቷ የድላሚኒ ዙማ የአራት ዓመታት የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ተቃርቧል ። የዙማ ሃላፊነት  በማብቃቱ ብዙዎች ቅር አይሰኙም ፤ ዙም ትተው የሚሄዱትም የተከፋፈለ የአፍሪቃ ህብረትን ነው ይላል የዶቼቬለው ሉድገር ሻዶምስኪ የዙማን የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ዘመን በቃኘበት ዘገባ ።

https://p.dw.com/p/2WVB9
Ruanda Rede Nkosazana Dlamini-Zuma Sitzung AU Gipfel
ምስል picture-alliance/Photoshot/P. Siwei

Bilanz Dlamini-Zumas - MP3-Stereo

የአፍሪቃ ህብረትን በሊቀመንበርነት ለመምራት በመመረጥ የመጀመሪያ ሴት ድላሚኒ ዙማ በሀገራቸው የነፃነት ተዋጊ ነበሩ እና ሥራቸው የተሳካ ይሆናል እንጂ እንከን ይኖረዋል ተብሎ አልተገመተም ። ይሁን እና ንኮሳዛና ድላማኒ ዙማ በሃላፊነት በቆዩባቸው 4 ዓመታት ውስጥ ከአዲስ አበባው የህብረቱ ጽህፈት ቤት ፣ ጥሩ ሥራ ሰርተዋል ብሎ የሚናገር ሰው ማግኘቱ ግን አስቸጋሪ ሆኗል ። ታዋቂው ናይጀሪያዊ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቺዲ አንሰልም ኦዲንካሉ በፓን አፍሪካ መፅሄት ላይ ስለ ዙማ ባሰፈሩት አስተያየት  ዶክተር ድላሚኒ ዙማ አፍሪቃን አያውቋትም ፤ ትኩረታቸው ወደ ሀገራቸው ፖለቲካ ለመመለስ  የነበራቸው ፍላጎት ላይ ብቻ ነበር ሲሉ ተችተዋቸዋል ። ዙማ በ2012 የተመረጡት በሦስት ዙር ከተካሄደ ድምጽ አሰጣጥ በኋላ ነበር ። እርሳቸው እንዲመረጡ ደቡብ አፍሪቃ ከፍተኛ ቅስቀሳ አካሂዳለች ። ይህ ደግሞ ከርሳቸው የቀደሙት የህብረቱ ኮሚሽን መሪ ጋቦናዊው ዦን ፒንግ ለተጨማሪ የሥልጣን ዘመን እንዲቆዩ ተስፋ አድርገው የነበሩትን ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገሮች አስቆጥቶ ነበር  ።ደቡብ አፍሪቃዊቷ የአፍሪቃ ህብረት ጉዳዮች ጠበብት ሊስል ሉው ቫውድራን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ  ዙማ ያኔ የተፈጠረውን ይህን ቅሬታ ፈጥነው ለማስተካከል ጥረት አላደረጉም ይላሉ  ።

Neue AU-Kommissionschefin Nkosazana Dlamini-Zuma mit Mandela
ምስል picture-alliance/dpa/GCIS

«ዙማ ሲመረጡ የተፈጠረውን አሉታዊ ስሜት ለማጥፋት ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል ። ወደ ሥልጣን የመጡትም ብዙ ተቀባይነት ሳይኖራቸው ነበር ። ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎቹ ሀገራት ነበሩ የሚቃወሟቸው ። ያኔ የተፈጠረው ክፍተት እየተጠገነ አይደለም ። ድላሚኒ ዙማም ክፍተቱን የማጥበብ ሙከራ አላደረጉም ። »

ብዙዎች እንግሊዘኛ ተናጋሪ የአፍሪቃ ሀገራት ደግሞ ለህብረቱ ትልቅ ቦታ የሚወዳደር ሰው ኃይል ካላቸው ሀገራት የሚወከል እንዳይሆን የሚለው ያልተጻፈው የአፍሪቃ ህብረት ደንብ ባለመከበሩ ተበሳጭተዋል ። ዙማ በጥቅምት 2012 ዓም የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት ሀኪም እና የደቡብ አፍሪቃ ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ነበሩ ። ሥራቸውን ሲጀምሩም ከርሳቸው ብዙ ተጠብቆ ነበር ።በሉዉ ቫውድራን አስተያየት በጠንካራ ሠራተኝነታቸው  እና በጥሩ ሃላፊነት መልካም ስም የነበራቸው ዙማ የአፍሪቃ ህብረትን ሥራ ይበልጥ ያቀላጥፋሉ ውጤታማም ያደርጋሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸው ነበር ። መቀመጫውን ካሜሩን ያደረገው «ቲንኪንግ አፍሪቃ »በተባለው የጥናት ተቋም የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አልፎንስ ዞዚሜ ታሜካማታም ዙማ ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

Dlamini-Zuma und Jacob Zuma
ምስል picture-alliance/dpa/J. Prinsloo

« ኃይል ካላት ሀገር የመጡ ጠንካራ ሴት ናቸው ። ሰዎች ትልቅ ራዕይ ፣የላቀ የአመራር ችሎታዎች  የሚያስቡትንም በነጻነት የመናገር እና በትላልቅ ውሳኔዎችም ላይ ተጽእኖ የማድረግ አቅም አላቸው ብለው ነበር የጠበቁት ።

ሆኖም እነዚህ ውሳኔዎች የርሳቸው ሳይሆኑ የአፍሪቃ ርዕሳነ ብሔራትና መራህያነ መንግሥት ነው ።ሉው ቫውድራን እንደሚሉት ከአፍሪቃ ህብረት ዋነኛ ድክመቶች አንዱ የሊቀመንበሩ ሥልጣን ውሱንነት ነው ። የህብረቱ ተቋማዊ ድክመት እና የገንዘብ ችግሮች ሳይጨምር ዙማ ፈጽሞ ትኩረት ያልሰጧቸው ቀውሶች ብዙ ናቸው ። ከነዚህም በክፍለ ዓለሙ የተካሄዱት የርስ በርስ ጦርነቶች ኢቦላ እና በሜዲቴራንያን ባህር ላይ የሞቱ በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች ጉዳይ፣ ኤልኒኞ እና ረሀብ እንዲሁም ቦኮሀራምን በዋነኝነት ይጠቀሳሉ ። ዙማ በኤቦላ የተጠቁ ሀገራትን ከመጎብኘት ፣ የቀድሞ ባለቤታቸውን ጄኮብ ዙማን ለመተካት በሚካሄደው ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ ለዝግጅት ደቡብ አፍሪቃ መሄዳቸው አስተችቷቸዋል ። ከዚህ ሌላ ደቡብ አፍሪቃን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት ከዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ለመውጣት መወሰናቸው ላይ ሲካሄድ ከነበረው ክርክር ራሳቸውን ማግለላቸውም እንዲሁ ከሚወቀሱባቸው ጉዳዮች  አንዱ ነው ። ይህን የሚያደርጉበትን ምክንያት የቡርኪናፋሶ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ሲያካ ኩሊባሊ ሲያስረዱ ፦

"ወይዘሮ ዙማ በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ተመልሰው ለመሥራት ተስፋ ያደርጋሉ ። ለዚህም ነው  ተመልሰው ሊያጠቋቸው በሚችሉ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ዝምታን የመረጡት ። »

ይሁንና ዙማ የሚወደሱባቸው ጉዳዮችም አልጠፉም ።  በሥልጣን ዘመናቸው  በአፍሪቃ ለሴቶች ጉዳይ ያሳዩት ቁርጠኝነት ከመካከላቸው አንዱ ነው  ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ