1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዚካ መድኃኒትን ፍለጋ

Mantegaftot Sileshiረቡዕ፣ ሐምሌ 27 2008

ሰውነትን በቀይ ሽፍታ ያለብሳል። በከፍተኛ ትኩሳት ያስጨንቃል። የአጥንት መገጣጠሚያዎችን እየቆረጠመ ኅመም ይፈጥራል። የዐይን መቅላትን ያስከትላል። ዋነኛ መተላለፊያው የትንኝ ንክሻ ነው። የዚካ ተሐዋሲ። የተሐዋሲው አስተላላፊ ትንኝ ትሮፒካል ሞቃታማ የአየር ክልል ውስጥ ይገኛል። ትንኙ ቢጫ ወባ፣ የቆላ ንዳድ የሚባሉትንም የማስተላልፍ አቅም አለው።

https://p.dw.com/p/1JaSx
Moskitos Symbolbild ZIKA Virus
ምስል Reuters/P. Whitaker

ዚካ፥ ከብራዚል ፍሎሪዳ

ትንኙ ቢጫ ወባ፣ የደንጊ ትኩሳት (የቆላ ንዳድ) የሚባሉትንም የማስተላልፍ አቅም አለው። በዚህ ትንኝ የሚተላለፈው የዚካተሐዋሲ ነፍሰ-ጡር ሴት፦ ሚጢጢ የራስ ቅል እና የተጎዳ አንጎል ያለው ጨቅላ እንድትወልድ ያደርጋል የሚሉም አሉ። የዚካ ተሐዋሲ በስፋት ከተሰራጨባት ብራዚል ባሻገር የዩናይትድ ስቴትሷ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥም መታየት ጀምሯል። ከወደ ቼክ ደግሞ ሳይንቲስቶች ዚካ የሚፈጥረውን ኅመም ለመፈወስ በሚደረገው የመድኃኒት ምርምር አዲስ ግኝት ላይ ደርሰዋል። እናስ ግኝቱ የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም ስጋት ላለው ለዚካ ተሐዋሲ ምን ፋይዳ ይኖረው ይኾን?

ተሐዋሲው ኡጋንዳ ውስጥ ከሚገኝ የመድኃኒት ምርምር ተቋም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1947 ዓ.ም እንዳፈተለከ ይነገራል። ከዚያን በኋላም ከሴኔጋል ተነስቶ ካምቦዲያ እስያ መድረሱ ይጠቀሳል። በቅርቡ ደግሞ የዚካ ተሐዋሲ ከተደላደለበት ከደቡብ አሜሪካ ወደ ሰሜን አቅንቷል።

ባለፈው ቅዳሜ የዩናይትድ ስቴትሷ ፍሎሪዳ ግዛት ዓሥር ሰዎች በዚካ ተሐዋሲ መጠቃታቸውን ይፋ አድርጋለች። ሚያሚ ውስጥ በትንኝ ንክሻ የተነሳ የዚካ ተሐዋሲ የተላለፈባቸው ሰዎች ቢያንስ 14 መድረሳቸው ተገልጧል። የፍሎሪዳ ሀገረ-ገዢ ተሐዋሲው እንዳይዛመት የድንገተኛ ቡድን በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲሰማራ መመሪያ አስተላልፈዋል። ሁኔታው የተሐዋሲው የስርጭት አድማስ ገደብ-የለሽ መሆኑን አመላካች ነው። ምሥራቅ አውሮጳ ውስጥ ግን የቼክ ሪፐብሊክ ሣይንቲስቶች ለመድኃኒት ግኝቱ ተስፋ ሰጪ የሆነ እመርታ ላይ መድረሳቸው ተዘግቧል። በቤተ-ሙከራ ተደጋጋሚ ጥረት የዚካ ተሐዋሲ ደካማ ጎንን ደርሰንበታል፤ በዚያም ቫይረሱን ልንመክተው እንችላለን ብለዋል።

«በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ፍላቪቬሪዴ የተሰኙ ተሐዋሲያን አሉ። ዚካ ከእነዚህ ቫይረሶች አንዱ ነው። ዘረ-መል መረጃዎችን ያቀፉ ተሐዋሲያን ናቸው። እናም ከቅርብ ጊዜ አንስቶ ትኩረታችንን ያደረግነው በነዚህ አይነት ተሐዋሲያን ላይ ነው። በተለይ ደግሞ ከዚካ ቫይረስ ጋር ተቀራራቢ የሆኑት የአንጎል መለብለብ እና መዛባትን የሚፈጥሩት ጀርሞች እና የምዕራብ ናይል ተሐዋሲያን ላይ አተኩረን ስንሠራ ነበር።»

ዶክተር ራዲም ኔንስካ እንዳሉት ከሆነ የቼክ መዲና ፕራግ ውስጥ በሚገኘው ቤተ-ሙከራ የሚያከናውኑት ምርምር በዚካ ተሐዋሲ ቤተሰቦች ላይ መሆኑ የዚካ ተሐዋሲን ለመዋጋት እገዛው ላቅ ያለ ነው። እጅግ የሥራ ውጥረት በሚታይበት የካርቦን እና ሌሎች ንጥረነገሮች እንዲሁም ባዮኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራ ተቋም (IOCB) ውስጥ ዚካን ለመዋጋት ሳይንቲስቱ በዋናነት ንጥረ ነገሮችን ያቀናጃሉ።

ተመራማሪው ዶክተር ራዲም ኔንስካ
ተመራማሪው ዶክተር ራዲም ኔንስካምስል Rob Cameron

«በመጀመሪያ ከዚካ ጋር ተቀራራቢ የሆኑት ሁለቱ ተሐዋሲያንን በመመርመር መድኃኒት ፍለጋው ላይ ማተኮራችንን ቀጠልን። ልክ ዚካ መሰራጨት ሲጀምር ደግሞ ዚካ ላይም ማተኮር እንዳለብን ወሰንን። ለእኛ ወደፊት ለመቀጠል ይኽ ትክክለኛው ሂደት ነበር።»

ዶክተር ራዲም ኔንስካ እና የምርምር ቡድናቸው የዚካ ተሐዋሲ ደካማ ጎን ላይ እንደደረሱበት እርግጠኞች ናቸው። ደካማ ጎኑን ማግኘታቸውም ተሐዋሲው ራሱን በራሱ የሚያባዛበትን ሒደት ለመዋጋት ያግዛቸዋል።

«ማንኛው ተሐዋሲ ራሱን በራሱ ለመተካት በሕይወት ዘመኑ አንዳች የእድገት ሒደት ያስፈልገዋል። ያ ኒውክሎሳይተስ እና ኒውክሎታይድስ ይሰኛል። እኛ ጣልቃ ገብተን የምንሠራው እነዚህ ሒደቶች ላይ ነው። ያ ደግሞ ተሐዋሲው ራሱን በራሱ እንዳያባዛ አድርጎ ሊያስቆመው ይችላል። ሆኖም ግን ያን ስናደርግ እጅግ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። ምክንያቱም የእኛም ሴሎች አስፈላጊያቸው የሆኑትን ኒውክሎሳይተስ እና ኒውክሎታይድስን ይጠቀማሉ። ስለዚህ የምንቀምመው ንጥረ-ነገር ነጥሎ የተሐዋሲው ብዜት ላይ ብቻ የሚያነጣጥር መሆን መቻል አለበት።»

ዶክተር ራዲም ኔንስካ ግኝታቸውን የበለጠ ምርምር እና ሙከራ እንዲደረግበት ዶክተር ዳንኤል ሩሴክ ለተባሉ ሌላ ሣይንቲስት ላኩ። ዶክተር ዳንኤል የቼክ ሪፐብሊክ ሁለት የምርምር ተቋማትን በኃላፊነት ይመራሉ። የቼክ የሳይንስ አካዳሚን እና የእንስሳት መድኃኒት ምርምር ተቋምን የሚመሩት ዶክተር ዳንኤል የተላከላቸውን ንጥረ-ነገር በዚካ ተሐዋሲ የተጠቃ ሕይወት ያለው ነገር ውስጥ በመክተት ምርምር አከናወኑ። ውጤቱ ተስፋ ሰጪ ነው። ዶክተሩ ግን ውጤቱን አስመልክተው ሲናገሩ እጅግ ተጠንቅቀው ነው።

የካርቦን እና ሌሎች ንጥረነገሮች እንዲሁም ባዮኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራ ተቋም (IOCB)
የካርቦን እና ሌሎች ንጥረነገሮች እንዲሁም ባዮኬሚስትሪ ቤተ-ሙከራ ተቋም (IOCB)ምስል Rob Cameron

«በእውነቱ ገና መነሻው ላይ ነው የምንገኘው። የትኞቹ ንጥረ-ነገር ውኅዶች ተሐዋሲው ላይ አጸፌታ እንደሚፈጥሩ ዐውቀናል። ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አግኝተናል። በንጥረ-ነገሮቹ ውኅድ ማነጣጠር የምንችልበትን የተሐዋሲውን ደካማ ጎን ለይተን ዐውቀናል። ሆኖም ግን የመጨረሻው ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም።»

አንዳንድ ሰዎች ንጥረ-ነገሩ እንዴት ነው ሥራ ላይ የሚውለው? በእንክብል መልክ ነው አለያስ በመርፌ የሚወጋ እያሉ ይጠይቁኛል ብለዋል ዶክተር ዳንኤል። ሆኖም ያን ለመመለስ ገና መሆናቸውን አክለው ተናግረዋል።

«ተሐዋሲው ላይ አጸፌታ የፈጠሩትን ንጥረ-ነገሮች በመድኃኒት መልክ ቀምመን መሞከር አለብን። ይኽ ቅድመ-መድኃኒት በመድኃኒት ቀማሚዎች ማሻሻያ ሊደረግበት ያሻል። የሰውነት ክፍላችን ላይ ትኩረት ተደርጎበት ሊሠራ ይገባል። አሁን ምርምር ከሚደረግባቸው ደቂቅ ህዋሳት ላይ በዝግታ ሊወገድም ይገባል። ስለዚህ ገና ረዥም ጊዜ ይጠብቀናል።»

ይኽ የዚካ መድኃኒት ምርምር ከነገ በስትያ ለሚጀምረው የሪዮ ኦሎምፒክ የሚደርስ አለመሆኑ እርግጥ ነው። ሁለት ሣምንታት ለሚዘልቀው የሪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ (በመላው ዓለም ከሚገኙ) ከ200 ሃገራት የተወከሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስፖርተኞች፣ የቡድን አባላት እና ደጋፊዎች እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

ተመራማሪዎች የኦሎምፒክ ውድድሩ ከሚኪያሄድባት ብራዚል ተሐዋሲው እንዳያፈተልክ ስጋታቸውን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ገልጠዋል። የብራዚል ጤና ጥበቃ ሚንስትር ከ20 ዓመታት በላይ የተከማቹ ሠነዶችን በማገላበጥ ብራዚል ውስጥ ከዚህ ቀደም የዚካም ሆነ መሰል ወረርሽኝ ተከስቶ አያውቅም ብለዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የሪዮ ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የለገሳቸውን ምክር ችላ እንደማይሉ ገልጠዋል።

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ባለፈው የካቲት ወር ላይ ባወጣው መግለጫ የዚካ ተሐዋሲ ስርጭትን ለመግታት የጉዞ እገዳ የሚደረግባቸው ሃገራት እንደሌሉ ጠቅሷል። ሆኖም ግን ሰዎች በተለይ ነፍጠ-ጡሮች የዚካ ተሐዋሲ ያለባቸው ሃገራት ሲሄዱ በትንኞች እንዳይነደፉ መጠንቀቅ እንዳለባቸው ተቋሙ መክሯል።

ብራዚል ውስጥ ነፍሰ-ጡሮች የራስ ቅላቸው እጅግ ሚጢጢ እና የተጎዳ አንጎል የያዙ ልጆች በብዛት በመውለዳቸው ከዚካ ተሐዋሲ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችል ይኾናል ሲሉ ተመራማሪዎች ጥርጣሬ አጭረዋል። ከመደበኛው እጅግ ባነሰ መልኩ የራስ ቅል መዛባት ክስተትን ተመራማሪዎች ማይክሮከፈሊ (Microcephaly) ይሉታል። ክስተቱ ከዚካ ተሐዋሲ በፊት የነበረ በመሆኑ ግን በእርግጥ ዚካ ያመጣው ይሁን ሌላ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

አሁን የታየው የዚካ መድኃኒት እመርታ ምናልባት በሚቀጥሉት አምስት አለያም ዐሥር ዓመታት ውስጥ የዚካ ተሐዋሲ መዛባትን ሊያስቆም ይችል ይኾናል። ምናልባትም ክትባትም ይገኝ ይኾናል። ክትባቱ ግን ረዥም ጊዜ ሊወስድ የሚችል እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Mosquito Mücke
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Miller

ነጋሽ መሐመድ