1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዛንዚባር፤ ምርጫና መዘዙ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 23 2008

በከፊል ራስ ገዝዋ በዛንዚባር ከአንድ ሳምንት በፊት የተካሄደው ምርጫ ከተሰረዘ በኋላ በግዛቲቱ ውጥረት ሰፍኗል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጓዳ ሰራሽ ቦምቦች ከፈነዱ በኋላ የዛንዚባር መንገዶች በወታደሮች እየተጠበቁ ነው። ዋነኛው የግዛቲቱ ተቃዋሚ ፓርቲ ሁኔታው ካልተስተካከለ የተቃውሞ ሰልፍ እጠራለሁ ሲል አስፈራርቶ ነበር ።

https://p.dw.com/p/1GyxV
Ali Mohammed Shein Zanzibar
ምስል DW/M. Khelef

በከፊል ራስ ገዝዋ በዛንዚባር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደው ታንዛንያ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ ባካሄደችበት ጥቅምት 14 2008 ዓም ነው። ይሁንና በዚሁ እለት የተካሄደው ምርጫ ከፍተኛ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል ያለው የዛንዚባር የምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ዓርብ ምርጫው መሠረዙን አስታውቋል። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር የምርጫው ሂደት ትክክለኛ እንዳልነበረና የሕግ ጥሰትም እንደተከሰተ ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ድምፅ ተጭበርብሯል፣ ሁለት ጊዜም ተሰጥቷል። በዚህ የተነሳም ምርጫው እንደገና መካሄድ እንደሚኖርበት ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል። በምህፃሩ CUF የተባለው ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የምርጫ ኮሚሽኑን ውሳኔ ተቃውሞ የምርጫው አሸናፊ መሆኑንም አስታውቋል። የፓርቲው ሊቀመንበር ሰይፍ ሻሪፍ ሃማድ ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ ድሉን ለዋነኛ ተቀናቃኛቸው ለፕሬዛዳንት አሊ መሀመድ ሻይን አሳልፈው እንደማይሰጡ ሲያስጠነቅቁ ነበር። ተቃዋሚዎች ምርጫው የተሰረዘው የምርጫ ኮሚሽን ጫና ስለተደረገበት ነው ይላሉ። የቀድሞው የCUF ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር ኢብራሂም ሊፑምባ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ቆጠራው እንዲጠናቀቅ እና አሸናፊውም ይፋ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

Tansania Präsidentschaftswahl Seif Sharif Hamad
ምስል DW/M. Khelef

«የመፍትሄ ቁልፉ የቻማ ቻማ ማፑንዲዚ በምህፃሩ CCM ሊቀ መንበር እና በዛንዚባር የርሳቸው ምክትልና የደሴቲቱ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሊ ሞሀመድ ሺን ናቸው። የዛንዚባር ምርጫ ኮሚሽን በምህፃሩ YEC ምርጫው መሰረዙን ያሳወቀው ተገዶ ነው። CCM በምንም ዓይነት ሁኔታ ለተቃዋሚዎች በምርጫ ስልጣን እንደማያስረክብ ለረዥም ጊዜ ሲናገር ነበር። ይህ ደግሞ በጣም አደገኛና እኔን የሚያሳስበኝ ነገር ነው። የውጭና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች በሙሉ ምርጫው ሰላማዊ ነበር ብለዋል። ጥፋት እንዳይደርስ ለማድረግ የምርጫ ኮሚሽን የድምፅ ቆጠራውን አጠናቆ አሸናፊውን በሰላማዊ መንገድ ማሳወቅ አለበት።»

CUF መሪ ሃማድ ጉዳዩ መፍትሄ ካልተፈለገለት የተቃውሞ ጥሪ ለማስተላለፍ ዝተው ነበር። ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ ዛንዚባር ውስጥ በደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ቦምቦች ፈንድተዋል። ፍንዳታዎቹ ጉዳት ባያስከትሉም ኤኮኖሚዋ በውጭ አገር ጎብኝዎች ላይ ጥገኛ በሆነው በዚህች ሃገር ስጋት መጫሩ አልቀረም። ለዛንዚባሩ ውዝግብ ሰላማዊ መፍትሄ ፍለጋው ቀጥሏል። ተሰናባቹ የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴ ባለፉት ቀናት ያለ እረፍት ምክክር በማድረግ ላይ መሆናቸውን ባለፈው እሁድ አስታውቀዋል። ተቃዋሚው ሃማድም አንድ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ እስኪደረስ ድረስ ደጋፊዎቻቸው እንዲረጋጉና በትዕግስት እንዲጠባበቁ ትናንት ጠይቀዋል። ታንዛንያ የሚገኙ የአፍሪቃና ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የዛንዚባር ምርጫ መሠረዝ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው እየተናገሩ ነው። አንዳንድ ነዋሪዎችም ምርጫው ሰለማዊ ከተባለ በኋላ በመሠረዙ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። ዩሱፍ መሀመድ የምርጫ ኪሚሽን ውጤቱን ባለማሳወቁ ቅር ከተሰኙት ውስጥ አንዱ ናቸው።

Sansibar Wahlen CUF Anhänger
ምስል DW/M. Ghassani

«ዩሱፍ መሀመድ ዩሱፍ እባላለሁ በዛንዚባር የፖለቲካ ሁኔታ አዝኛለሁ። የምርጫ ኮሚሽን ምርጫውን ለምን ሰረዘ? የሀገር ውስጥና ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች ምርጫው በነፃና ትክክለኛ መንገድ ተካሂዷል ካሉ በኋላ መሠረዙ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብቶች መገደብ ነው።»

ዛንዚባር በቅርብ ዓመታት የሃይማኖትና ግጭቶችና የፖለቲካ ውጥረቶች የተከሰቱባት ሀገር በመሆኗ ምርጫው በመሠረዙ ምክንያት ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩ አልቀረም። መንግሥት ሌላ አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ሺን በፕሬዝዳንትነት ሃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ