1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዜጎችን ከሳዉዲ የማዉጣቱ ርምጃ

ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2006

የኢትዮጵያ መንግስት ከስዑድ አረቢያ ከሃምሳ ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ወደሀገር ቤት መመለሳቸዉን አስታወቀ። የመንግስት ቃል አቀባይ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት ለዚሁ ተግባር በጀት ተመድቦ በሚካሄደዉ ዘመቻም በየዕለቱ ወደስምንት ሺህ ገደማ የሚሆኑት እየገቡ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1APey
ምስል AFP/Getty Images

እንዲያም ሆኖ ግን እዚያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸዉ ዜጎችን ቁጥር ኢትዮጵያም ሆነች ስዑድ አረቢያ በትክክል ለመግለፅ መረጃዉ እንደሌላቸዉ ነዉ የተገለጸዉ።

አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከአዲስ አበባ እንደዘገበዉ የስዑድ አረቢያ መንግስት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸዉ የዉጭ ዜጎች የሰጠዉ የምህረት ቀነ ገደብ ካለቀ በኋላ በወሰደዉ ርምጃ እስካሁን ወደኢትዮጵያ የተመለሱት ከሃምሳ ሺህ በላይ ሆነዋል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይን የጠቀሰዉ ይህ ዘገባ እንደሚለዉም ወደአስር ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ የተገመተዉ የሕገወጥ ኗሪዎች ብዛት ወደሀገር የመመለሱ ተግባር ሲከናወን እጅግ አሻቅቦ ወደሰማንያ ሺህ ተገምቷል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ጂዳ ዉስጥ የታሰሩት 23 ሺህ ፤ ያልተመዘገቡትም እንዲሁ 23 ሺህ እንደሚደርሱ ይናገራሉ። መዲና እና መካም ቁጥራቸዉ በትክክል ያልታወቀ ኢትዮጵያዉያን እንዳሉ ነዉ የሚገለጸዉ። አንዳንዶች በዚህ ሁኔታ ወደሀገር የተመለሱትን ጨምሮ ቁጥሩ ከመቶ ሺህ ይልቃል ባይ ናቸዉ።

Zum Thema - Zwei Tote bei Krawallen illegaler Einwanderer in Saudi-Arabien
ምስል Reuters/Faisal Al Nasser

የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጥቅሉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም 200,000 ሴቶች ሥራ ፍለጋ ከሀገር መዉጣታቸዉን ያመለክታል። ዓለም ዓቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ILO ከእነዚህ ወገኖች አብዛኞቹ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸዉ፤ ዝቅተኛ ክፍያም እንደሚሰጣቸዉ፤ አድሎና መጥፎ የሥራ ቦታቸዉም ደረጃዉን ያልጠበቀ እንደሆነ ይገልጻል። ስዑድ አረቢያ ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን የገጠማቸዉ ችግር ሀገር ዉስጥም ሆበነ በመላዉ ዓለም የሚገኙ ዜጎችን አስቆጥቷል። የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ ሳዉዲ ስለሚገኙት ዜጎች ቁጥር ተመዝግበዉ የወጡ ባለመሆናቸዉ ሁለቱም መንግስታት ትክክለኛዉ መረጃ እንደሌላቸዉ በመግለፅ፣ ያም ቢሆን ግን መንግስት ዜጎቹን ወደሀገር በመመለሱ ተግባር መጠመዱን ያመለክታሉ፤

መንግስት ለዚሁ ተግባር 2,6 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ ሳዉዲ የቆዩ ዜጎችን የመመለሱን ዘመቻ በማከናወን ላይ ሲሆን ከተመላሾች አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸዉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ፈቃዳቸዉን እንዲያስተካክሉ የሳዉዲ መንግስት የሰጠዉ የምህረት ጊዜ ካበቃ ወዲህ በሺዎች የሚገመቱ ኢትዮጵዉያን ከባድ ችግር ላይ መዉደቃቸዉን ሲገልፁ ቆይተዋል። አቶ ጌታቸዉ እነዚህን ወገኖች የመመለሱ ተግባር ከመንግስት አቅም በላይ አይደለም ነዉ ያሉት፤

Zum Thema - Zwei Tote bei Krawallen illegaler Einwanderer in Saudi-Arabien
ምስል Reuters/Faisal Al Nasser

ሳዉዲ ዉስጥ የመካ ኗሪ እንደሆኑ የገለፁልን ኢትዮጵያዊ በርካታ ዜጎች በአሰሳ ወጥተዉ በአንድ ስፍራ ያለምንም ከለላ መከማቸታቸዉን በማመልከት ቀደም ሲል ሪያድ ላይ የገጠመዉ ዓይነት ችግር እዚያም እንዳይገጥም ስጋታቸዉን ይገልጻሉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም ከወጣዉ ያልወጣዉ ይበረክታል፤

ከዚህም ሌላ አንዳንድ ዘገባዎችም የሳዉዲ መንግስት ኢትዮጵዉያን ስደተኞችን ወደየመን አስገድዶ መላኩን ያመለክታሉ። መንግስታቸዉ ስለዚህ የደረሰዉ መረጃ እንዳለም አቶ ጌታቸዉን ጠይቄያቸዉ በይፋ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ በማመልከት፤ ኢትዮጵያዊ ነን ብለዉ ሪያድ እና ጄዳ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ የተመዘገቡ ዜጎችን በየተራ የመለሱ ሥራ ግን እየተከናወነ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ