1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በሀገረ ጀርመን

ሐሙስ፣ ግንቦት 18 2008

«ቅዱስ ያሬድን በቅድስና ሕይወቱ ብቻ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ብቻ ነዉ ብሎ ከማሰብ ለኢትዮጵያዉያን የዋለዉን ያበረከተዉን የሥነ-ጽሑፍ የዜማ የድርሰት አስተዋጽኦ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አዉቆ ቢዘክሩት ጥሩ ነዉ ብዬ አስባለሁ»

https://p.dw.com/p/1Iuui
Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern Jahresgottesdienst
ምስል privat

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በሀገረ ጀርመን

ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በሚል ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እዚህ ጀርመን ካልስሩወኸ ከተማ በተካሄደዉ አዉደ ጥናትና ዝክረ በዓል ላይ ቅዱስ ያሬድን በተመለከተ የጥናት ፅሑፍ ያቀረቡት በሃንቡርግ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በግዕዝ ቋንቋና ስዋስዉ የዶክትሪት ትምርትን በመከታተል ላይ የሚገኙት መጋቤ ሚስጥር ህሩይ ኤርሚያስን ነበር የተናገሩት።

ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የተሠወረበት ግንቦት 11 ቀን በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ -ክርስትያን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል። ዘንድሮ በአዉሮጳ የመጀመርያ የሆነዉ የቅዱስ ያሬድ መታሰብያ ቀን በጀርመን ካልስሩወኸ ከተማ ታስቦ ዉሎአል። ለሦስት ቀናት በዘለቀዉ በዚህ ክብረ በዓል ላይ ከኢትዮጵያና ከተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት የመጡ ኢትዮጵያዉያን በቅዱስ ያሬድ ዙርያ የተለያዩ የጥናት ጽሑፎችን አቅርበዋል፤ የቅዱስ ያሬድ ዜማም ተስተጋብቶአል። በዚህ ዝግጅት በካልስሩወኸ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በዓል ላይ የጥናት ጽሑፋቸዉን ያቀረቡ ምሑራኑን ይዘን የኢትዮጵያዊዉን ሊቅ ማንነት እንቃኛለን።

« የበዓሉ ዝግጅት ርዕስ ወይም መሪ ቃል ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በሀገረ ጀርመን የሚል ነዉ። ይህ እጅግ በጣም ጥሩና መሠረታዊ አስፈላጊ ርዕስ ነበር፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን አንጻር መከበር ነበረበት፤ ቀኑ የተመረጠበት ደግሞ ቅዱስ ያሪድ የተሰወረበት ወይም ያረበት ቀን ተብሎ የሚታሰበዉ፤ ግንቦት 11 ቀን በመሆኑ ነዉ። እንዲህ ባለ መልኩ ግን ማለት ብዙ ምሁራን በአካዳሚዉ የሚገኙ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ሁለት ሦስት ጊዜ ተክብሮአል፤ ግን እንዲህ በሰፊዉ አላየሁም። እኔም ያጋጠመኝ እዚህ ጀርመን ነዉ። የቅዱስ ያሬድን በዓል በጀርመን ሳከብርም ይህ የመጀመርያዬ ነዉ። በበዓሉ ላይ ያቀረብኩት ቅዱስ ያሬድ ከመጽሐፍ ጋር በተገናኘ መልኩ መጽሐፎቻችን ስለ ቅዱስ ያሬድ ምን እንደሚሉ እና ፤ ስለ ቅዱስ ያሬድ ክብር የተዘጋጁ መጽሐፍት በቤተ-ክርስትያናችን ያሉትን ዝርዝር ለማቅረብ ወይም ቅኝት ለማድረግ ነዉ የሞከርኩት»

በሃንቡርግ ዩንቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በግዕዝ ቋንቋና ስዋስዉ የዶክትሪት ትምርትን በመከታተል አምስት ዓመት እንደሆናቸዉ የነገሩን መጋቤ ሚስጥር ህሩይ ኤርሚያስ በካልስሩወኸ ዝግጅት ላይ ሌላዉ የጥናት ፅሑፍ ያቀረቡ ምሑር ነበሩ

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern ihren Jahresgottesdienst in Daxlanden
በበርሊን ነዋሪ የሆነዉ ጀርመናዊ ሊዮናርድ ባህ በዝግጅቱ ላይምስል Tekle Sirak
Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern Jahresgottesdienst
ምስል privat


«እኔ ያቀረብኩት በቅኔ ድርሰት አጀማመር ታሪክ ዉስጥ የቅዱስ ያሬድ ድርሻ ወይም አስተዋጽኦ ምንድን ነዉ በሚል ርዕስ ላይ ነዉ። ቅዱስ ያሬድ የዜማ ብቻ ሳይሆን የቅኔም ደራሲ ወይም ጀማሪ አባት እንደሆነ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፍን ነዉ ያቀረብኩት ነዉ። በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሊቃዉንት በኩል የተለያዩ አስተያየቶች ወይም ቱፊቶች አሉ። ለምሳሌ ጎንጅ የሚባለዉ የቅኔ ቤት መምህራን ቅኔን የጀመረዉ ተዋናይ የሚባል በ 16ኛዉ ክፍለዘመን የነበረ ሊቅ ነዉ ብለዉ ነዉ የሚያምኑት። ይህ ተዋናይ ቅኔን ከመጀመሩ በፊት ወደ ግሪክ መጥቶ ሰባት ቋንቋዎች ጥበቦች ተምሮ ተመልሶ እንደሄደና ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ ቅኔን እንደፈለሰፈ ቅኔዉንም ለአጼ እስክንድር እንዳስተማረ ይናገራሉ ያምናሉ። ነገር ግን ብዙዎቹ ሊቃዉንት የሚቀበሉት፤ ዋድላ የተባለዉ የቅኔ ቤት ቱፊት ቅኔን ለመጀመርያ ጊዜ የጀመረዉ ተዋናይ ሳይሆን ቅዱስ ያሬድ ነዉ። ምክንያቱም፤ ቅዱስ ያሬድ ድጓ በተባለዉ የቅኔ ድርሰት ዉስጥ 22 የዜማ አርስቶች አሉት፤ የዜማ አርስቶቹ የተወሰኑት ዛሬ የቅኔ መጠርያ ሆነዉ የሚያገለግሉት ይዘዜ፤ ዋዜማ፤ ስላሴ ዘይዜ መወድስ ይክብሪይቲ እጣነሞገር የሚባሉትን የያዙ ናቸዉ።»


ሁለተኛ የምስጋና ድርሰቶቹ ሁሉም ባይሆኑ የተወሰኑት፤ እንደ ቅኔ ሚስጥር አዘል የሆኑ ቤት የሚመቱ ናቸዉ። ዮኃንስ ዘገብሎን ወይም ገብላዊ የተባለ በ 15ኛዉ ክፍለ ዘመን የነበረ ሊቅ፤ ቅኔ የሚባለዉ ጥበብ ለቅዱስ ያሬድ ተገልጾለት እንደነበረ አዉቆ እግዚአብሔር ይህን ጥበብ እንዲገልጽለት ደብረታቦር ሱባኤ ገባ፤ እናም ሱባኤዉን ሲጨርስ፤ መንፈስ ቅዱስ ለቅዱስ ያሬድ እንደተገለፀለት፤ ለርሱም ገልጾለት ይሄን አልምቶ አስፍቶ ተናግሮታል። እናም የዋድላ ቅኔ ቤት መስራች ዮኃንስ ዘገብሎን ነዉ ተብሎ ቢታመንም የቅኔ ጀማሪ ወይም የቅኔ አባት ግን ቅዱስ ያሬድ መሆኑን ነዉ፤ በዋድላ ሊቃዉንት ዘንድ የሚተረከዉም ፤ ታሪክም የሚያምነዉ። እናም በዝግጅቱ ላይ በጽሑፊ ላይ ለማሳየት የሞከርኩት ይህን ነዉ። የተወሰኑ የቅዱስ ያሪድን ምስጋናዎች ለጉባኤዉ አሳይቻለሁ። እነዚህ ዜማዎች በትክክል ቅዱስ ያሬድ የቅኔ ጀማሪ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸዉ »


ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እዚህ ጀርመን ካልስሩወኸ ከተማ በሚገኘዉ የኢትዮጵያ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ያሬድን አስመልክቶ የሦስት ቀናት አዉደ ጥናትና ተካሂዶአል። በቅዱስ ያሬድ ዙርያ በጥናትና በምሑራን ደረጃ እንዲህ አይነት ትልቅ ዝግጅት ያጋጠመኝ እዚህ ጀርመን ሲሉ በደቡባዊ ጀርመን ባየር ግዛት በሙኒክ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት ረዳት ፕሮፊሰር አምሳሉ ተፈራ ገልፀዉልናል።

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern Jahresgottesdienst
ምስል privat


ቅዱስ ያሬድ ማን ነዉ ለኢትዮጵያዉያን ?
« ቅዱስ ያሬድ ማን ነዉ ለኢትዮጵያዉያን ኢትዮጵያዊነትን በጥሩ መልኩ ሊገልጽና ሊያሳይ በሚችል ሁኔታ ልናቀርበዉ ልንጠቅሰዉ የምንችለዉን የዜማ ታሪካችንን የቅኔ የምርምር የፍልስፍና ያመጣልን ያስተዋወቀን ደርሶ የሰጠን የማንነታችን መገለጫ የሆነ አባት ነዉ። ጻድቅ ነዉ፤ ሊቅ ነዉ መናኝ ነዉ፤ በሥነ-ጽሑፍ ረገድም፤ ለሥነ-ጽሑፍ መሰረት የሆነ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስራች ነዉ። ቅዱስ ያሬድን መርሳትም መዘንጋትም የሚቻል ነገር አይደለም። ዜማዉ አያስፈልገንም፤ ቅኔዉ ፍልስፍናዉ ምርምሩ አያስፈልገንም፤ ካልተባለ በስተቀር ኢትዮጵያዊ ሆኖ ቅዱስ ያሬድን መዘንጋት አይቻልም። ከዚህም አንጻር ነዉ፤ መረሐ-ግብሩን በአዉሮጳ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲዘጋጅ በአዉሮጳ ሃገረ ስብከት በኩል አጽድቀንና ወስነን ፕሮግራሙ በአዉሮጳ ደረጃ የተከበረዉ፤ በየዓመቱም የሚቀጥል በዓል ይሆናል። በየአገሩ ይዞራል አዉሮጳ ዉስጥ ያሉ ሃገሮች ጣልያን ስዊዘርላንድ በመሳሰሉት በሚገኙ ቤተክርስታኖቻችን በሙሉ የሚከበር በዓል እንዲሆን አድርገን የጀመርነዉ።


መላከ ስብሃት ተክሌ ሲራክ በጀርመን በካልስሩኸ ምዕራፈ ቅዱሳንና የክሮንበርግ ቅዱስ ሩአኤል ወቅዱስ ያሬድ ቤተ-ክርስትያን አስተዳዳሪ ፤ በጀርመንዋ ከተማ ስለተካሄደዉ በዓል ሲገልፁ፤

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern Jahresgottesdienst
ምስል privat


« የቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በአል መቼም በዋናነት የኢትዮጵያዉያን ይባል እንጂ በዓሉ ለዓለም ነዉ ማለት ይቻላል። ከቅዱስ ያሬድ የተቀነባበረን ዜማ የሚያዉቅና የተነሳ አልነበረም። ስለዚህ ቅዱስ ያሬድ የዓለም ሁሉ የዜማ መሠረት ነዉ። እና ግን በቤተክርስትያናችን የዓለሙን ዜማ፤ ከሱ ዜማ ለይተን ነዉ የምናየዉ። ስለዚህ ይህ ለኢትዮጵያዉያን ታላቅ በዓላቸዉ ነዉ። በአዉሮጳም ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ የቅዱስ ያሬድ በዓል የተከበረዉ። ከዚህ በኃላ ግን አገረ ስብከቱ በዋናነት እየመራዉ በዓሉ በሰፊዉ ነዉ የሚከበረዉ፤ በዚህ በዓል ኢትዮጵያዉያኑም ነጮቹም እጅግ ደስተኞች ነበሩ። ስለዚህ ዜማን ስናነሳ መሠረቱ ቅዱስ ያሬድ ስለሆነ የኛ ቤተ-ክርስትያን ያለ ቅዱስ ያሬድ ጨርሶ የተዘጋች ነች ማለት ይቻላል። መክፈቻዋ ቁልፏ የቅዱስ ያሪድ ዜማ ነዉ። ያለቅዱስ ያሪድ ይህች ቤተ ክርስትያን ምንም ዉበት የላትም ማለት ይቻላል። የቅዱስ ያሬድ ታሪክ መነሻዉም መድረሻዉም ኢትዮጵያ ነዉ።»


ቅዱስ ያሬድ የዛሬ 1503 ዓመት፤ በ505 ዓ,ም ን እንደተወለደ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። ይላሉ፤ መላከ ስብሃት ተክሌ ሲራክ፤ ቅዱስ ያሬድ ንብ ማለት ነዉ ።


« ቅዱስ ያሬድ ማነዉ ብለን ከስሙ ስንነሳ ያሬድ ማለት ርደት ማለት ነዉ፤ መዉረድ ማለት ነዉ። ዋናዉ ግን ቅዱስ ያሬድን የሚገልፀዉ ንብ ማለት ነዉ። ንብ የተለያዩ አበባዎችን ቀስማ ወይም ለቅማ የጣፈጠ ማር እንደምትሰራ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ከተለያዩ ቅዱስ መጻሕፍት አምጥቶ ቀምሞ፤ ያማረ የጣፈጠ ዜማ እናም ሚስጢር ያለዉ ድርሰቶችን የደረሰ ስለሆነ፤ ያሬድ ማለት ንብ ማለት ነዉ ሲሉ ይገልፁታል ሊቃዉንት።»


ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ቤተ- ክርስቲያን ሰማያዊ ዜማን ከማበርከቱም ሌላ በትምህርት ሂደትም አስተዋጽዖ ማድረጉ የድጓን፣ የጾመ ድጓን የዝማሬ መዋሥዕትንና የቅዳሴን ትምህርት ማስተማሩ ብሎም ለቅኔ ትምህርትም መሠረት መጣሉ ይነገራል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ነዉ እንጂ ይሄኔ አውሮጳዊ ወይም አሜሪካዊ ቢሆን ኖሮ ስሙ ምን ያህል በገነነ ነበር፤ መንገዱም ትምህርት ቤቱም፤ ሕንፃዉም ሆነ አደባባዩ በስሙ በተጠራ ነበር። የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ለነገሩ መዲና አዲስ አበባ ብርቅዬ ምሁራንና ከያንያንን ያፈራ በቅዱስ ያሬድ የተሰየመ ተቋም ይገኛል፤ «ያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት» ።
በካልስሩወኸ ከተማ ደምቆ በታየዉ ዝክረ ቅዱስ ያሬድ በዓል ላይ በጀርመንና ከተለያዩ አዉሮጳ ሃገሮች የመጡ

Deutschland Äthiopisch-orthodoxe Christen feiern Jahresgottesdienst
ምስል privat

ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን መገኘታቸዉን ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል። አካባቢዉ ላይ የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበዉ ወደ 400 የሚሆኑ በነጭ ባህላዊ ልብስ የደመቁ ኢትዮጵያዉያን እና ኤርትራዉያን ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተዉት እንደነበር፤ የቅዱስ ያሬድን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ማንነት በመጠርጠር ጽፎአል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ መሰናዶዉን የድምፅ ማዕቀፉን በመቻን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሐመድ