1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃሳብ ነፃነት በቱኒዚያ

ረቡዕ፣ የካቲት 25 2007

የቱኒዚያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የድረገጽ ጸሐፊ በሆነዉ ቱኒዚያዊ ያሲን አያሪ ላይ የጦሩን ስም በማጥፋት ወንጀል እስራት ፈረደ። ያሲን የተከሰሰዉ የሀገሪቱ የጦር ኃይል መኮንኖች እና የመከላከያ ባለስልጣናት የሚፈፅሙትን የገንዘብ ብክነት አስመልክቶ ከሀገሩ ዉጭ ሆኖ በድረገጽ በመጻፉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1El4o
Tunesien Proteste für die Freilassung des Bloggers Yassine Ayari
ምስል AFP/Getty Images/F. Belaid

በሌለበት ቀደም ሲል ክስ ተመስርቶበት የሶስት ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበት ነበር።ፍርድ ቤቱ ዉሳኔ ተቺዎችንም ሆነ በቱኒዚያ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት መታፈኑን የሚገልፁ ወገኖችን አላስደሰተም።

ያሲን አያሪ ራሱ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ከጂሃዲስቶች ጋ በነበረ ግጭት የተገደሉ የጦር መኮንን ልጅ ነዉ። የ33ዓመቱ የድረገጽ ጸሃፊ ወይም ብሎገር፤ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋች የሆነዉ ሂዉመን ራይትስ ዎች ለአዲሲቱ ቱኒዚያ አይረባም ሲል የተቸዉን ወታደራዊ መኮንኖችና የመከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ገንዘብ እያባከኑ መሆኑን የሚገልፁ ጽሑፎችን ከሀገር ዉጭ በቆየባቸዉ ጊዜያት በመጻፉ ተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል። በሌለበትም ሶስት ዓመት እንዲታሰር ተወስኖበት ነበር። ባለፈዉ ታህሳስ ወደሀገሩ ተመልሶ አዉሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ተይዞ የጦር ፍርድ ቤቱ ዳኛ ፊት ቀረበና የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት። ጠበቃዉ ባቀረቡት ይግባኝም ትናንት የስድስት ወር እስራት ተወሰነበት። አያሪስ ዳኛዉ ብያኔዉን ሲያሰሙ የድል ምልክት በጣቱ እያሳየ ደስታዉን ገልፆ ወደእስር ቤቱ ታጅቦ ሄደ። በቱኒዚያ ሃሳብን በፃነት መግለፅ እንቅፋት እየገጠመዉ መሆኑን በመግለፅ ለተቃዉሞ ከጦር ፍርድ ቤቱ ደጃፍ የተሰበሰቡት ወገኖች ግን ዉሳኔዉን አጥብቀዉ ተቃወሙ አወገዙ።

Tunesien Freiheit für den Blogger Yassine Ayari
ያሲን አያሪምስል DW/S. Mersch

«ወታደራዊ ፍርድ ቤት ይዉደም፤ ቱኒዚያ ወታደራዊ መንግሥት የላትም፤ ቱኒዚያ የሲቪል አሰተዳደር ናት፤ ወታደራዊ የፍርድ ሂደትን እንቃወማለን።»

የሚሉ መፈክሮቻቸዉንም አሰሙ። የድረገጽ ጸሐፊዉ ያሲን አያሪ እናት ብይኑ ፖለቲካዊ ይዘት አለዉ ነዉ ያሉት፤

«ይህ ፖለቲካዊ ፍርድ እንጂ ከዚያ ያነሰም ከፍ ያለም አይደለም። የቱኒዚያ ወጣቶች ገና ረዥም ጉዞ እንደሚጠብቃቸዉ ላሳስባቸዉ እወዳለሁ። መጀመሩ ከባድ ነዉ፤ በቀጣይም ቀላል ላይሆን ይችላል። ያሲን ጀምሮላቸዋል እነሱ ደግሞ አሁን መቀጠል ይኖርባቸዋል።»

ያሲን አያሪ በመንግሥት ላይ የሚታዘበዉን በግልፅ ከመተቸት ተቆጥቦ አያዉቅም። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም በሕዝባዊ አመፅ ከስልጣን የተሰናበቱት የቀድሞ የቱኒዚያ ፕሬዝደንት ዚን ኤል አቢዲን ቤን አሊን አገዛዝም በመተቸት ይታወቃል። ደጋፊዎቹ የድረገጽ ጸሐፊዉ ቅጣት የተፈረደበት ባለፈዉ የቱኒዚያ ምርጫ ስልጣን ላይ የወጣዉ የፕሬዝደንት ቤጂ ካይድ ኤስቤሲ ፓርቲኒዳ ቱኒዝን የሚተቹ ጽሁፎችን በመጻፉ ነዉ የሚል ጥርጣሬ አላቸዉ። እናም የእሱ መከሰስ ቤን አሊን ከስልጣን ያባረረዉ የቱኒዚያ ሕዝባዊ አብዮት ያስገኘዉን አዲሱን ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት የሚፃረር መሆኑን አበክረዉ ይገልጻሉ።ትናንት የቱኒዚያ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ብይን ሲያሳልፍ ተቃዉሞ ካሰሙት አንዷ፤

Tunesien Proteste für die Freilassung des Bloggers Yassine Ayari
ከጦር ፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት የተቃዉሞ ሰላማዊ ሰልፍምስል AFP/Getty Images/F. Belaid

«የተሰማዉን ብቻ ነዉ በፌስቡክ ላይ የጻፈዉ። ወታደራዊዉን ተቋም ተችቷል፤ እናም ያደግሞ መብቱ ነዉ። እዚህ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አለን፤ ለዚህም ነዉ አብዮት ያካሄድነዉ።»

ትላለች።

ያሲን አያሪ በቱኒዚያ ሕዝባዊ አብዮቱ ከመቀስቀሱ አስቀድሞም ፌስቡክ ላይ ትችቶቹን ሲያስነብብ ቆይቷል። በድረገጽም የቱኒዚያ መከላከያ ሚኒስቴርን ግድፈቶች፤ ከምንም በላይ ደግሞ ጦሩ በዉስጡ የተሰገሰጉ በሙስሊም ፅንፈኝነት የሚጠረጠሩ ወታደሮች መኖራቸዉና ጥፋት ሊያደርሱ እንደሚችሉ እየታወቀ መከላከል ሲቻለዉ ርምጃ ባለመዉሰዱ ባለፈዉ ዓመት በተከሰተ ግጭት 15 ወታደሮች መገደላቸዉን ዘርዝሮ በመተቸት ጽፏል። መረጃዎች እንዳሉትና ለምክር ቤት መርማሪ ኮሚቴ ለማቅረብም ዝግጁ ነበር። ያም ቢሆን ግን በስም ማጥፋትና የወታደሮችን ሞራል በማንኳሰስ ተከሰሰ።

የቱኒዚያ ሕዝብ ለጦር ሠራዊቱ ያለዉ አመለካከት አዎንታዊ ነዉ፤ ብዙዉን ጊዜም ትችት ሲሰነዝርበት አይታይም። አሸባሪዎች ጥቃት በሚሰነዝርቡበት ወቅት የፀጥታ ኃይል አባላትም ሰለባ የሚሆኑበት አጋጣሚ ስለሚበዛም ትስስሩን ያጠበቀዉ ይመስላል። እንዲያም ሆኖ የኮሎኔል ልጅ የሆነዉ የድረገጽ ጸሐፊ ችግሮችን ነቅሶ እንከኖችን አዉጥቶ ይህን አይነኬ ተቋም ደጋግሞ ተችቷል። ያም ቢሆን በጦር ፍርድ ቤት መዳኘቱን ቱኒዝ የሚገኘዉ የድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስሚን ካቻ ተገቢ አይደለም ይላሉ፤

Yasmine Kacha Reporter ohne Grenzen
ያስሚን ካቻምስል DW/S. Mersch

«አንድ የድረገጽ ጸሐፊን የጦሩን ስም አጠፋ ብሎ ጦር ፍርድ ቤት ማቅረብ ተቀባይነት የለዉም። የጦሩን ስም አጥፍቷል ከተባለም መዳኘት ያለበት በሲቪል ፍርድ ቤት መሆን ነበረበት። በዚያ ላይ ይህ የሚያመላክተዉ ነገር አለ ጦሩን ስም ማጥፋት ማለት ሁሉንም ማለት ሊሆን ይችላል። በዚህ መሠረትም ነገ ደግሞ ለሕዝቡ የሚጠቅም የተደበቀ ምስጢር አጋላጮችም ይህን በማድረጋቸዉ ሊከሰሱ ነዉ ማለት ነዉ።»

ሂዉማን ራይትስ ዎች የቱኒዚያ ምክር ቤት በስም ማጥፋት ወይም የመንግሥት ተቋማትን በመተቸት ምክንያት እስራት የሚበይነዉን የሀገሪቱን ሕግ እንዲያሻሽል፤ እንዲሁም ሲቪሎች በጦር ፍርድ ቤት መዳኘታቸዉን እንዲያስቀር ጠይቋል። ያሲን አያሪ ከታሠረ አንስቶ ከተቆጠረለት የስድስት ወራቱን እስር ፈጽሞ በመጪዉ ሰኔ ወር ይፈታል የሚል ተስፋ አለ።

ሣራ መርሽ/ ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ