1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17 2004

በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የኢንዱስትሪ ትዕይንት፤ የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽን ባለፈው ዕሑድ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው።

https://p.dw.com/p/14kGe
ምስል DW

በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የኢንዱስትሪ ትዕይንት፤ የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽን ባለፈው ዕሑድ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው። የዘንድሮው አበር አዘጋጅ ሕዝባዊት ቻይና ስትሆን በትዕይንቱ ላይ ጎላ ብላ መታየቷም አልቀረም። የጀርመን ኩባንያዎች በተፋጠነ ዕድገት ስትራመድ የመጣችውን ግዙፍ እሢያዊት አገር የሚመለከቱት ዛሬ እንደ ተፎካካሪ ብቻ ሣይሆን እንደ ጠቃሚ የኤኮኖሚ ተባባሪም ጭምር ነው።

በዘንድሮው ትዕይንት ከ 69 ሃገራት የመጡ አምሥት ሺህ ኩባንያዎች አዳዲስ የምርትና አገልግሎት ውጤቶቻቸውን አቅርበው እያስተዋወቁ ሲሆን ከነዚሁም ግማሹ ከውጭ የመጡ ናቸው። ከቻይና ብቻ 500 ኩባንያዎች ሲመጡ ይህም ትዕይንቱን በይፋ መርቀው በከፈቱት በጀርመኗ ቻንስለር በወሮ/አንጌላ ሜርክልና በቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር በዌን ጂያባዎ የሁለቱ መንግሥታት የጠበቀ የኤኮኖሚ ትብብር መለያ ሆኖ ነው የታየው።

ትብብሩን ሁለቱም መንግሥታት አጥብቀው ይፈልጉታል። የጀርመን ኩባንያዎች በተለይም የኢንዱስትሪ መኪናዎችን የሚያመርተው ዘርፍ ለምሳሌ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ምሶሶ እንደመሆኑ መጠን ትብብሩን የቻይናን ያህል ይሻዋል። ለጀርመን ለጊዜው የአውሮፓ ሕብረት ሃገራት ዋነኞቹ ገበዮች ቢሆኑም የኤኮኖሚና የፊናንሱ ቀውስ ይህን ሁኔታ እየቀየረው ነው የመጣው። እናም የጀርመን ምርት ተፈላጊነት በዚህ በአውሮፓ እያቆለቆለ ሲመጣ የዕድገት ዕድል የሚታየው ቻይናን፣ ሕንድን ወይም ብራዚልን በመሳሰሉት ተራማጅ ገበዮች ሆኗል።

ቻይና በእሢያ ቀደምቷ የጀርመን የኤኮኖሚ ሸሪክ ስትሆን ትብብራቸው የጀርመን ኩባንያዎች ትርፍ ለማግኘት፤ ማለት በርካሽ ወጪ ለማምረት በቻይና የሚሰፍሩበት የበላይነት ጊዜ ሆኖ ነው ዓመታት ያሳለፈው። ይሁንና አሁን ሁኔታው ሲለወጥ ትብብሩና የንግድ ልውውጡ ውስብስብ እየሆነ ሄዷል። በሌላ አነጋገር የቻይና ኩባንያዎችም በጀርመን በሰፊው እየሰፈሩ ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ የቻይና ኩባንያዎች በዚህ በጀርመን 158 በሚሆኑ ፕሮዤዎች ላይ መዋዕለ-ነዋይ አድርገው ነበር።

ወደ ኢንዱስትሪው ትዕይንት መለስ እንበልና የዘንድሮው የሃኖቨር ትዕይንት በተለይ የሚያተኩረው በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ላይ ነው። በዚህ የተፈጥሮ ጥበቃ ዘርፍ ጀርመን በቴክኖሎጂ ዕውቀት ርቃ የተራመደች ስትሆን ቻይና ደግሞ ታላቁ ገበያ ናት። በሌላ በኩል እርግጥ ቻይናም በቴክኖሎጂ ፈጣን ዕርምጃ እያደረገች ስትመጣ ከገበያነት ወደ ከባድ ተፎካካሪነት በመለወጥ ላይ መሆኗ የተሰወረ ነገር አይደለም። ይህም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በሃኖቨሩ ትርዒት መክፈቻ እንዳስገነዘቡት የጀርመን ኢንዱስትሪ ለፉክክር እንዲዘጋጅ ቀስቃሽ ነው።

«የትዕይንቱ አበራችን ቻይና ሌሎች ሃገራት በምን ፍጥነት ወደፊት እየገሰገሱ አንደሀነ እያሳየችን ነው። ስለዚህም አሁን እዚህ እንደምንታዘበው በምርምርና ፈጠራ የተመላው የጀርመን የኢንጂነር ጥበብ ወደፊት በመራመድ መቀጠል ይኖርበታል»

ቻይና ዛሬ ለጀርመን የምርት መኪና አውጭና የፋብሪካ ግንቢያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋነኛዋ የውጭ ንግድ ገበያ ናት። ይሄው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ ቻይና የሸጠው ምርት በ 19 ሚሊያርድ ኤውሮ ይገመታል። ለንጽጽር ያህል ከአሥር ዓመታት በፊት ይሄው በአምሥት ሚሊያርድ ኤውሮ ብቻ የተወሰነ ነበር። የቻይና ኩባንያዎች በዓለም ዙሪያ የሚሸጧቸውን ምርቶች የሚሰሩት እንግዲህ በአብዛኛው በጀርመን መኪናዎችና በጀርመን በተተከሉ ፋብሪካዎች ጭምር መሆኑ ነው።

Autosalons in der südchinesischen Stadt Hangzhou
ምስል DW

እርግጥ ቻይናም ከበለጸገው ዓለም ላይ ለመድረስ በምታደርገው ጥረት ብዙ ወደፊት ስትራመድ ዛሬ ራሷ የምርት መኪናዎችን መስራት ብቻ ሣይሆን በረቀቀ ደረጃ ለማምረት ከምትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰችም አገር ናት። ጀርመንን ለመሳሰሉት አስጊ ተፎካካሪ የምትሆንበት ጊዜ እንግዲህ ብዙም ሩቅ የሚሆን አይመስልም። በወቅቱ በሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት ላይ የቻይና ኩባንያዎች ከዚህ በፊት ከአገር ውጭ ባልታየ መጠን በብዛት በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የጀርመን የምርት መኪና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ወኪሎች ተፎካካሪያቸው ምን ያህል እንደተራመደች ለማየት ጥሩ አጋጣሚ ማግኘታቸውን ነው የዘርፉ ፌደራል ማሕበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሃነስ ሄሰ በትዕይንቱ መክፈቻ ዋዜማ ያመለከቱት።

«የቻይና ኩባንያዎች እዚህ በሃኖቨር ከምርጥም ምርጥ የሆኑ ምርቶቻቸውን ነው ለትዕይንት የሚያቀርቡት። እናም በቴክኖሎጂ የመጠቁ ምርቶችን የማየት ዕድል ይኖረናል። እንግዲህ እኛ የምናቀርበውን ከዚሁ የማነጻጸር ዕድል ይኖረናል ማለት ነው። ይህም ቻይና የት እንደደረሰች ለመለየት የሚረዳን ይሆናል»

የጀርመን የምርት መኪና ግንቢያ ዘርፍ ለማንኛውም የቻይናን ፈጣን ዕርምጃና በፉክክር እየቀረበች መሄድ እንደ ቀስቃሽ ማስታወሻ እንጂ እንደ አደጋ አድርጎ አይመለከተውም። ለነገሩ ዘርፉ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ የተነሣ የገጠመው ችግር ቀላል አልነበረም። ምርቱ በስፊው በማቆልቆል በሩብ እስከመቀነስ ነበር የደረሰው። ይህ የሆነው ከሶሥት ዓመታት በፊት ሲሆን ኩባንያዎቹ የቀውሱን መዘዝ ለመቋቋም በርካታ ዓመታት እንደሚያስፈልጓቸው ነበር በጊዜው የተገመተው።

ግን የጀርመን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከቀውሱ በፊት ከነበረው ደረጃ ሙሉ በሙሉ አይድረስ እንጂ በሚገባ መልሶ ለማገገም እንደታሰበው ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። እርግጥ ዘንድሮ በዘርፉ የትርፍ ዕድገት ባይጠበቅም ወኪሎቹ የሚናገሩት ይሄው አዝማሚያ መልሶ የማቆልቆል ምልክት እንዳልሆነ ነው። የምርት መኪናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የጀርመን ኤኮኖሚ ጠቃሚ መሠረት እንደመሆኑ መጠን ይዞታው በአገሪቱ ዕርምጃ ላይ ትልቅ ወሣንነት አለው።

Bildergalerie Hannover Messe Highlights Bild 2
ምስል DW

በአገሪቱ ከታላላቅ አንቀሳቃሽ ሞተሮች አንስቶ እስከ ትናንሽ ፑምፓዎች በማምረት ተግባር የተሰማሩ 950 ሺህ ያህል ሠራተኞች ሲኖሩት ታላቁ ቀጣሪ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑ ነው። ጀርመንም አንዴ የውጭ ንግድ የዓለም ሻምፒዮን የሚል ቅጽል መጠሪያን ማትረፍ የቻለችው በዚሁ ዘርፍ ጥንካሬ ነበር። እርግጥ ይሄው ክብረ-ወሰን ዛሬ ቻይና ዕጅ ገብቷል። ታዲያ ለጀርመን ኩባንያዎች ከቻይና ጋር የተያዘው ሽርክና ዕድልም አደጋም የተዋሃደው ሆኖ መታየቱ አልቀረም።

አደጋው በተለይ ቻይና ብቁ ተፎካካሪ እስክመባል ደረጃ እያደገች መምጣቷ ነው። የቻይና መንግሥት የምርት መኪናዎችን ዘርፍ ቁልፍ መስክ አድርጎ በመለየት ይህንኑ ለማሳደግ ሲጥርና ስኬታማ ዕርምጃ ሲያደርግም ቆይቷል። የሩቅ ምሥራቋ ግዙፍ አገር ከአሁኑ በዓለም ላይ ታላቋ የምርት መኪናዎች የሚሰሩባት አገር ናት። እርግጥ እስካሁን አብዛኛው ምርት ለአገር ውስጥ ገበዮች ሲቀርብ ቆይቷል።

ሆኖም አሁን የውጭ ንግዱ እየጨመረ ነው። በዚሁ ደግሞ ጀርመንና ቻይና በብዙ አገሮች አንዱ ለሌላው እንቅፋት ወይም ተፎካካሪ እየሆኑ መሄዳቸው አልቀረም። ፉክክሩ ጠንክሮ ከሚገኝባቸው መስኮች አንዱም የነፋስ ኤነርጂ ማመንጫ መሣሪያዎች መስክ ሲሆን ከዚሁ ዘርፍ ኩባንያዎች ባለቤቶች አንዱ ዮአሂም ፉርሌንደር ፉክክር አለ ደግ፤ ግን ፍርሃቻ ላይ መውደቅ አያስፈልግም ባይ ናቸው።

«እርግጥ ለቻይና አክብሮት አለን። ፍርሃቻ ግን ፈጽሞም! ከጥቂት ዓመታት በፊት ለቻይና ታላቅ የነፋስ ኤነርጂ ማመንጫ አምራች ኩባንያ ሊሤንስ፤ ፈቃድ ስንሸጥ ኩባንያው የተሣካ ዕርምጃ ማድረጉንም እናውቃለን። ሆኖም ቻይና በዓለም ላይ ገና ተናጠል መንግሥታትን በሙሉ ለማዳረስ አልበቃችም። ከዚሁ ሌላ ብዙ መንግሥታት የኤነርጂው መሣሪያ በአገራቸው ኩባንያዎች መሰራቱን ነው የሚፈልጉት። ብራዚል ለምሳሌ 60 በመቶው በአገር አምራች መሰራቱን ትሻለች። ቻይና ደግሞ ይሄን የምታሟል አይደለችም። ምክንያቱም ምርቱን ቻይና ውስጥ ሰርታ ወደ ውጭ መላኩን ነው የምትመርጠው»

የጀርመናዊው የፉርሌንደር ኩባንያ በአንጻሩ ከዚህ ቀደም በሕንድ ሲያመርት ቆይቷል። በቅርቡም በተመሳሳይ ተግባር በብራዚል፣ በቪየትናምና በኡክራኒያ በተመሳሳይ ስራ ለመሰማራት እየተዘጋጀ ነው። ኩባንያው ለሃኖቨሩ ትዕይንት ያቀረበው የነፋስ ኤነርጂ ማመንጫ ሞተርና ጀነሬተሩን በአንድ የጠቀለለ ይዘት ያለው ሲሆን በዚሁ ከአንድ መደበኛ መሣሪያ 60 በመቶ ክብደትን የሚቀንስ ነው።

ዝቅተኛ ክብደት ደግሞ ቀላል ትራንስፖርትና ቀላል መገጣጠም ማለት ነው። ይህን መሰሉ የነፋስ ሃይል ማመንጫ እንግዲህ እንደ አውሮፓ መንገዶችና ማመላለሻ በሚገባ ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ማራኪ ይሆናል። በሌላ በኩል በክብደቱ ቢቀልም ሃይል በመስጠቱ ረገድ ግን ከትልልቆቹ የማያንስ ነው።

ቻይና ለጊዜው እርግጥ በረቀቀ ቴክኖሎጂ ረገድ ከምዕራቡ ዓለም ለመድረስ ገና የተወሰኑ ዓመታት የሚቀሯት ይመስላል። በሆንም ይህን ለመለወጥ የማታደርገው ጥረት የለም። ሙያተኞቿን በከፍተኛ የትምሕርት ተቋማቷ በተሻል ጥራት በዕውቀት ለማነጽ ከያዘችው ጥረት ባሻገር የተማሩ የውጭ ዜጎችን በመመልመልም ላይ ናት። የዚሁ ዓላማም የቻይና ምሁራንን እጥረትና የሚጎለውን ብቃትም መሸፈን ነው። እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ 1600 የሚበልጡ የውጭ ምሁራን ተመልምለዋል።

Hafen Shanghai
ምስል picture-alliance/dpa

ቻይና ከምዕራቡ ዓለም በአጠቃላይና ከጀርመን ጋርም ያላት ችግር በተለይ የአዕምሮ ሃብት ጥበቃን የማታከብር መሆኗ ነው። ቻይና በሕገ-ወጥ መንግድ ቅጂ በማድረግ በዓለም ገበዮች ላይ የማትረጨው ምንም ነገር አይገኝም። ይህ የአዕምሮ ሃብት ባለቤትነት መብት መጣስ ደግሞ በገበዮች ላይ ያለውን ፉክክር ፍትሃዊነት ያሳጣል። ስለዚህም ውሎ አድሮ መቀጠል የሌለበት ነገር ነው።

ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ በሃኖቨሩ ትዕይንት አኳያ ቻይና ለበለጠ የኤኮኖሚ ትብብር ስትል የአዕምሮ ሃብት ጥበቃን እንደምታሻሽል ቃል-ገብተዋል። የውጭ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በቻይና ኩባንያዎች ፊት አድልዎ ሊደረግባቸው አይገባም ነው ያሉት። እርግጥ ይህ ሲሰሙት ጥሩ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን እያደር መታየት የሚኖርበት ጉዳይ ነው።

ያም ሆነ ይህ ቻይና በኢንዱስትሪ ልማት ቀደምት ለመሆን እስከ 2015 ድረስ 450 ሚሊያርድ ኤውሮ ለማውጣት ታስባለች። ቁልፍ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን በማስፋፋት፣በአዲስ የኤነርጂ ምንጮች፣ በባዮ-ቴክኖሎጂና በተፈጥሮ ጥበቃ ወዘተ ለመምጠቅ ታቅዷል። ቻይና የኢንዱስትሪ ዘርፏ በአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቷ ላይ የሚኖረው ድርሻ እስከ 2020 ከአምሥት ወደ 15 በመቶ እንዲያድግ በማድረግ በቴክኖሎጂ ቀደምት የሆኑትን ሃገራት ለማስከንዳት ተሥፋ ጥላለች፤ ታልማለች።

እስከዚያው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም አሁን በወቅቱ እንደሚታየው በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት ሃገራት የዘመናዊ ዕድገት ፍላጎት በፈጠረለት ሰፊ ገበያ ተጠቃሚ ሆኖ ይቀጥላል። ከዚያ በኋላ ግን ምዕራቡ ዓለምና የጀርመን ኢንዱስትሪም የሚኖረው ምርጫ ለፉክክር ብቁ ሆኖ ለመቀጠል መዘጋጀት ነው። ባሉበት መርገጡ ከእንግዲህ የሚቻል አይሆንም።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ