1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃኖፈሩ፣ የመረጃ ሥነ-ቴክኒክ ትርዒት፣

ረቡዕ፣ የካቲት 23 2003

እ ጎ አ የ 2011 ፤ ማለትም የዘንድሮው ፣ የሃኖፈር ዓለም አቀፍ በጀርመንኛው አህጽሮት «ሴ ቢ ት » በመባል የሚታወቀው፣ የቢሮና የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ማዕከል፣ እ ጎ አ መጋቢት 12 ቀን 1986 ዓ ም በሰሜን ጀርመን ከተማ፣ በሃኖፈር ከተጀመረ ወዲህ፣

https://p.dw.com/p/R5kC
የ"ክላውድ ኮምፒዩቲንግ" የምስል ምልክት፣ምስል DW/Arahan, Dev - Fotolia.com

ከጊዜ ወደጊዜ፤  የሥነ ቴክኒኩን  ፣ የኢንዱስትሪውን፣ የኤኮኖሚውንና  የንግዱን  ማኅበረሰብ ይበልጥ እያማለለ መምጣቱ  ይነገርለታል። በዚህ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ትርዒት ዘንድሮ ምን አዲስ ነገር ይሆን ለትርዒት የቀረበው?

ከትናንት በስቲያ በልዩ ግብዣ፣ከንግዱ  ዓለም መሪዎች ጋር  የተገኙት የጀርመን መራኂተ-መንግሥት  አንጌላ ሜርክልና የዘንድሮዋ  ተጋባዥ ሀገር በሆነችው  ቱርክ  ጠ/ሚንስትር ሪቸፕ ኤርዶጋን  ትናንት ጧት ፤  ሐኖፈር ላይ በይፋ የተከፈተው የዘንድሮው የ ሴ ቢት ትርዒት፣ «ቶቢ» በሚባለው የእስዊድን ኩባንያ የተሠራው፤ በዓለም ውስጥ  የመጀመሪያው ፣ ዓይንን በማሽከርከር የሚሠራው «ላፕ ቶፕ»ቀርቦበት ብርቅ-ድንቅ! ተብሏል።

ይኸው በዐይን ቁጥጥር የሚሠራው የቶቢ «ላፕቶፕ» የሆነው ሆኖ በብዛት ተሠርቶ ለህዝብ ጥቅም ገበያ ላይ የሚውለው ከ 2 ዓመት በኋላ እንደሚሆን ነው የተገለጠው።

የጀርመን ቴሌኮም፤ ልዩ ጥራት ባለው ተንቀሳቀሽ ስልክ Long Term Evolution (LTE)በተሰኘው ሥነ-ቴክኒክ፣ በፍጥነት ከእጅ ስልክ  የተለያየ መረጃን ለማግኘት፤ በ «አይፓድ» እና በመሳሰለው ለሚሠራበት፣  በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቧል። ይኸው ሥነ ቴክኒክ ውድ የመረጃ ማስተላለፊያ ገመድ ሳይዘረጋ ፣ ለገጠር ኑዋሪዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ይቻላል።  ፣ ቮዳፎን፣ 02፣ እና የጀርመን ቴሌኮም፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ፣ ያለገመድ በ LTE  ደንበኞች ፣ በኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ማሠራጫ መሥመሮች አሽሽለው መሥራቱን ተያይዘውታል።

ሌላው ፤ « ክላውድ ኮምፒዩቲንግ»  ነው። ክላውድ ኮምፒዩቲንግ፤ አንድ ደንበኛ፤ በቢሮም ሆነ በመኖሪያ ቤቱ፣ ያለ ሶፍትዌርም ሆነ የኮምፒተር ሞተር(ፕሮሰሰር) በድረ-ገጽ  የሚጠቀምበት ፤ የሚገለገልበት አሠራር ነው። 

ይኸው፣ ለቢሮና ለቤት የሚጠቅመው  የኢንተርኔት አገልግሎት ፣  የንግዱ ዓለም በቁጠባ የተቀላጠፈ ሥራ ማከናወን የሚችልበትን ብልሃት  ነው። መሆኑም  ነው የሚነገረው። ተጠቃሚዎች፤  በያመቱ  ለ «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ»፣ 1,6 ቢሊዮን ዩውሮ(2,2 ቢልዮን ዶላር ) እንደሚያውጡ ነው የሚገመተው። ከንግድ ደንበኞች ጋር ፣ ይኸው የአገልግሎት ዘርፍ ዘንድሮ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ 3,5 ቢሊዮን ዩውሮ ገቢ እንደሚያገኝ የሚጠበቅ  ሲሆን፤ ከሆነ ፣ ካምናው የ 55 ከመቶ ዕድገት  ያሳያል ማለት ነው። « ክላውድ ኮምፒዩቲንግ» አንድ ደንበኛ፤ በቢሮም ሆነ በመኖሪያ ቤቱ፣ ያለ ሶፍትዌር፣ በድረ-ገጽ  የሚጠቀምበት ፤ የሚገለገልበት አሠራር ነው።  

በዚህ  የ «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ» መርኀ ግብር ይበልጥ ያተኮረው እውቁ የሶፍትዌር ኩብንያ ማይክሮሶፍት ነው። «ዊንደውስ» እና «ማይክሮሶፍት  ኦፊስ» ኩባንያው እንደ ወተት ሰጪ ላሞች ፣ በአመዛኙ  ገንዘብ  በገፍ የሚያልብባቸው የገቢ ምንጮቹ ናቸው።  ማይክሮሶፍት ከዚህ ሌላ፤ ድምፁን አጥፍቶ፤ በድረ-ገጽ፤  በተለይም በ « ክላውድ»  ላይ አትኮሮ መቆየቱ ን በጀርመን የማይክሮሶፍት ቅርንጫፍ ኀላፊ ፣ ራልፍ ሃውፕተር ያስረዳሉ። ክላውድ ኮምፒዩቲንግ ይላሉ ራልፍ ሃውፕተር፣ የኢንተርኔት የአገልግሎት ዓይነት ሂደትን  የለዋወጠ ነው። ይህ ደግሞ ለኤኮኖሚው ልዩ ማነቃቂያ ኅይል  የሚሆን ነው። «ክላውድ ኮምፒዩቲንግ፣»  በኅብረተሰቡም በኩል ለውጥ የሚያንፀባርቅ ነው። የክላውድ ኮምፒዩቲንግ አገልግሎት፣ ከህዝብ ብዛት ጋር ተያይዘው በሚከሠቱ ማኅበራዊ ችግሮች፤የጤና አጠባበቅ፣  አስተዳደርና በመሳሰሉት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ አሠራሩም ይበልጥ ግልጽነትንና ፍጥነትን የሚያካትት ነው። ማይክሮሶፍት የጀርመን ቅርንጫፍ፣ በክላውድ ሥነ ቴክኒክ በመመርኮዝ፤ እያንዳንዳቸው የፈጠራ ሥራንና ውጤትን የሚሹ  30 ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ቃል ከመግባቱም፤ በአውሮፓ ፣ ጀርመንን   በክላውድ ኮምፒዩቲንግ ረገድ መሪ ሀገር ለማድረግ ከመጣር እንደማይቦዝን ራልፍ ሃውፕተር አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ፣ ጀርመናውያን በሥነ ቴክኒክ በተለይም በመገናኛ ዘርፎች የሚደረገውን ሁሉንም ዓይነት አሠራር የሚደግፉ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ጉግል በጀርመን ሀገር የተለያዩ ከተሞችን ጉዳናዎች በተንቀሳቃሽ ምስል ለመቅረጽ ያደረገውን ሙከራ የተቃወሙ ጀርመናውያን  ጥቂቶች አልነበሩም። ክላውድ ኮምፒዩቲንግን በተመለከተ ፣ አብዛኞቹ መሪ ኩባንያዎች፤ በጀርመን መሠረት ያላቸው አይደሉም። መሪዎቹ፤ IBM, Amazon, Google,Microsoft  እና  Salesforce.com  ናቸው።  

50 ከመቶው የጀርመን ኩባንያዎች፤ የራሳቸውን አገልግሎት መምራትና መረጃዎችንም በሚገባ መጠበቅ እንደሚችሉ  የሚናገሩ ባይታጡም፣ 

የ ሃኖፈሩን ዓለም አቀፍ የቢሮና የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ትርዒት በበላይ ኀላፊነት እንዲያዘጋጅ ያበቃው፣  የጀርመን የዲጂታል አንዱስትሪ ፌደሬሽን Bitcom ፕሬዚዳንት አውጉስት ቪልሄልም ሺር፣ የመረጃ ስብስብ ጥበቃን በተመለከተ ፣ ጀርመናውያን ደረጃውን በጠበቀ  ዓለም አቀፍ ስምምነት ውስጥ ሊሳተፉ ይገባል ባይ ናቸው።

አውጉስት ቪልሄልም ሺር፣ በመረጃ ሥነ ቴክኒክ ረገድ አጋጥሞ የነበረው የገንዘብና የኤኮኖሚ ቀውስ ከእንግዲህ ያለፈ ታሪክ ነው በማለት በጀርመንና  በአውሮፓው ኅብረት አገሮች ዘንድሮ ዕድገት እንደሚገኝ ነው የገለጡት።

«በአጠቃላይ፣ በ 2011 ፤ የ 2 ከመቶ ዕድገት መመዘገቡ አይቀርም። ድንገት የሚያስደንቅ ውጤት ቢመዘገብ ደግሞ ልንገረም አይገባም። ምክንያቱም፤ ለፈጠራ ሥራ ዘርፍ ዐቢይ ግምት እንደመሥጠታችን መጠን፤ አንዳንድ ዕድገቶችን  እጅግ በተፋጠነ ሁኔታ ማስመዝገብ ይቻላል።  እንዲህ ዓይነቱን ውጤት ደግሞ ሁልጊዜ አስቀድሞ በትክክል መገምገምም  ሆነ መመልከት አይቻልምና!»

በጥናት የተመሠረተው ግምት እንደሚጠቁመው ከሆነ የጀርመን፤ የመረጃ ሥነ-ቴክኒክ ፣ የመዝናኛ ሥነ ቴክኒክና የመገናኛ መሣሪያዎች ኩባንያዎች በአጠቃላይ 145,5 ቢሊዮን ዩውሮ ሳይዝቁ አይቀሩም። ያም ሆኖ፣  ሺር፤   ከፍተኛ ጥራት ባለው የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ገበያ፣ ዩናይትድ እስቴትስ፣ ከዚያም አልፎ ከአዳጊ አገሮች መካከል የመጠቁት ህንድ ፣ ቻይናና  ብራዚል ፤ ሩሲያ ጭምር የመሪነቱን ቦታ ሳይዙ አልቀሩም። ጀርመን ከዚያ ተከታይ ሆኜአለሁ ነው የምትለው።   

በሃኖፈሩ የሴቢት ትርዒት ተጋባዥ እንግዳ የሆነችው ቱርክ፣ ያልታሰብ እርምጃ ማሳየቷን የትርዒት ማሳያው ማዕከል ቃል አቀባይ Hartwig Saß እንዲህ ሲሊ መሥክረዋል።

«ቱርክ ፤ በዓለም አቀፉ የመተጃ ሥነ-ቴክኒክ ድብቅ ሻምፒዮና ትመስላላች።  ከአንድ 5 እና  6 ዓመት ገደማ በፊት ወዲህ ፤ ቱርክ ከውጭው ዓለም ጋር የነበራትን  የንግድ ሚዛን በሰፊው እንዲለወጥ አድርጋለች። ለረጅም ጊዜ ቱርክ፣ የኮምፒዩተር መሣሪያዎችን ከውጭ ነበረ የምታስገባው ። ከዚህ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችንም እንዲሁ! አሁን ግን በዓለም አቀፍ ገበያ መሳተፍ የምትችልበት በር ተከፍቷል። ይህንንም በዚህ በ «ሴቢት» ትርዓት ላይ ማየት ይቻላል። ለብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችም፣  ቱርክ ፣   በገበያና ገንዘብን ሥራ ላይ በማዋል  ረገድ የምታማልልና ጥሩ ዕድገትም ማስመዘገብ የሚቻልባት ናት።»   

 ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ