1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሄልሙት ሽሚት ስርዓተ ቀብር

ሰኞ፣ ኅዳር 13 2008

ቀድሞው የጀርመን መራሔ መንግሥት ሄልሙት ሽሚት ስርዓተ ቀብር ዛሬ በሀምበርግ የቅዱስ ሚኻኤሊስ ቤተ ክርስትያን ተፈፀመ። ሶሻል ዴሞክራቱ እና «ዲ ሳይት» የተባለው ጋዜጣ ተባባሪ አሳታሚ የነበሩት ሄልሙት ሽሚት ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው ህዳር 10፣ 2015 ዓም ነበር በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት።

https://p.dw.com/p/1HAiV
Deutschland Begräbnis von Helmut Schmidt in Hamburg
ምስል picture-alliance/dpa/A. Heimken



በዚሁ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ በተደረገበት እና ከ1,800 የሚበልጡ ከፖለቲካው፣ ከንግዱና ከማህበራዊ ዘርፎች የተውጣጡ እንግዶች በተገኙበት የስንብት ስነ ስርዓት ላይ ከተሳተፉት መካከል የጀርመን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ፣ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ የፌዴራዊው ምክር ቤት ፕሬዚደንት ኖርበርት ላመርት፣ የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ሊቀመንበር እና ምክትል መራሔ መንግሥት ዚግማር ጋብርየል፣ እንዲሁም፣ ከፍተኛ የአውሮጳ ህብረት ባለስልጣናት፣ የቀድሞ የጀርመን መራሔ መንግሥት ጌርሀርት ሽረደር፣ የቀድሞ የጀርመን ፕሬዚደንቶች ሮማን ሄርሶግ፣ ሆርስት ከለር እና ክሪስትያን ቩልፍ ፣ የቀድሞው የዩኤስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሄንሪ ኪስንገር እና የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ዢስካር ዴ ስታ(ን) ይጠቀሳሉ።

Staatsakt für Helmut Schmidt
ምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

ቪሊ ብራንትን በመተካት ከጎርጎሪዮሳዊው 1974 እስከ 1982 ዓም ድረስ ጀርመንን የመሩት ሄልሙት ሽሚት በአመራር ዘመናቸው ከገጠሟቸው ትልቅ ተግዳሮቶች መካከል፣ ለምሳሌ፣ በተለይ በ70ኛዎቹ ዓመታት በዓለም የናዳጅ ዘይት ዋጋ በናረበት ጊዜ የተከተሉት ኤኮኖሚ ፖሊሲ፣ እንዲሁም፣ የግራ አክራሪ ተስፈንጣሪው የቀይ ጦር አንጃ የተባለው ቡድን የሽብር ጥቃት እና የእገታ ተግባር ባካሄደበት ጊዜ የወሰዱት ቆራጥ ርምጃ ይጠቀሳሉ። በቤተክርስትያኑ ከተካሄደው ይፋ የስንብት ስነ ስርዓት በኋላ የቀድሞው መራሔ መንግሥት አስከሬን በሞተር ቢስክሌቶች ታጅቦ የመጨረሻ እርፍት ወደሚያገኝበት የኦልስዶርፍ መካነ መቃብር በተጓዘበት ጊዜ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችበመንገድ ዳር በመገኘት ስንብት አድርገዋል።

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ