1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህንድና የፓኪስታን ግንኙነት ከሙምባዩ ጥቃት በኋላ

ሐሙስ፣ ኅዳር 17 2002

በሙምባይ የአሸባሪዎች ጥቃት ከተጣለ ከአንድ ዓመትም በኋላ ጥቃቱን ከፓኪስታን ያቀደው እና ያካሄደው የአሸባሪዎች መረብ አሁንም እንደተጠናከረ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/Kh3w
ምስል AP

በጥቃቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች ትናንት በፓኪስታን የራዋልፒንዲ ከተማ በአንድ ጸረ ሽብርተኝነት ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከነዚህም መካከል የሙምባይን ጥቃት በማቀዱ ተግባር ዋነኛውን ሚና ይዘዋል የሚባሉት ዛኪኡር ሬማን ላክቪ ይገኙበታል። ከአንድ መቶ ስድሳ የሚበልጡ ሰዎች የተገደሉበት እና ስድሳ ሰዓታት የቆየው ደም አፋሳሹ ጥቃት አንደኛ ዓመት ሊታሰብ አንድ ቀን ሲቀረው በላክቪ ላይ ክስ መመስረቱ እንደ ትልቅ ምልክት ተቆጥሮዋል። ይህም ቢህን ግን፡ በጥቃቱ ይበልጡን የተበላሸው የህንድ እና የፓኪስታን ግንኙነት ወደመደበኛው ሁኔታ እስኪመለስ ድረስ ገና ብዙ ይቀረዋል።

ፓኪስታን የሙምባይ ጥቃት ከግዛትዋ መታቀዱን እና ጥቃቱን የጣሉት አሸባሪዎችም ፓኪስታናውያን መሆናቸውን አምና ለመቀበል ብዙ ሳምንታት ነበር የወሰደባት። ኢዝላማባድ ወደፊት ተመሳሳይ ትቃት እንዳይጣል ለማከላከል በቂ ርምጃ አልወሰደችም በሚል ኒው ዴሊ እስከዛሬ ትወቅሳለች። ይህንንም ምክንያት በማድረግ ከፓኪስታን ጋር ጀምራው የነበረውን ድርድር በጠቅላላ አቋርጣለች።

ህንድ የሙምባይን ጥቃት አቀነባብረዋል ተብለው ከተከሰሱት ተጠርጣሪዎች ችሎት ይበልጥ በአሁኑ ጊዜ ትልቁን ትኩረት ሰጥታ የምትከታተለው ፓኪስታን ለጥቃቱ ተጠያቂ ከሚባለው ላሽካር ኤ ታይባን ድርጅት በምህጻሩ ኤል ኤ ቲ ጋር ያላትን ግንኙነት ነው። የፓኪስታን ጦር እና የስለላ ድርጅት በህንድ፡ በተለይም፡ በካሽሚር ለምታካሂደው ጥቃት እያለች የላሽካር ኤ ታይባን ተዋጊዎችን ባለፉት ጊዚያት ማሰልጠንዋ የሚታወቅ ነው። ስለሽብርተኝነት ሰፊ ጥናት ያደረገው ፈረንሳዊው ጠቢብ ዣን ልዊ ብሩጊየር ይህ ግንኙነት ከመስከረም አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ እንዴት እንደቀጠለ በቅርቡ ባወጣው አዲስ መጽሀፍ በዝርዝር አስቀምጦታል።

Mumbai Attentat Zaki-ur-Rehman Lakhvi
ዛኪኡር ሬማን ላክቪምስል AP

እርግጥ፡ ፓኪስታን በአሁኑ ጊዜ ራሱን ከላሽካር ኤ ታይባን በይፋ አርቃለች። ይሁንና፡ የድርጅቱ መዋቅር አሁንም እንደተጠናከረ ነው። በዚሁ አኳያ ፓኪስታን ውስጥ የሚሰሙት መከራከሪያ ሀሳቦች የሀገሪቱ መንግስት ከታሊባንና ከሌሎች ሙስሊም ቡድኖች ጎን ሌላ አዲስ ጠላት ማፍራት አያስፈልገውም፤ ከዚህ በተጨማሪም፡ ላሽካር ኤ ታይባን በህቡዕ መንቀሳቀስ ከጀመረ መከታተሉ ይበልጡን አዳጋች ይሆናል የሚሉት ናቸው። ስለላሽካር ኤ ታይባን ሰፊ ዕውቀት የሰበሰቡት የዋሽንግተኑ ጠቢብ ስቴፈን ታንከል ይህን አባባል በተወሰነ ደረጃ ይረዱታል።

ቡድኑ በህቡዕ እንዲንቀሳቀስ ወይም ተስፋንጣሪ ቡድኖችን እንዲያቋቁም መገፋፋት አያስፈልግም በሚል የሚሰማው ስጋት ተገቢ ነው ብየ አስባለሁ። በሌላ በኩል ግን ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ይህን ለማድረግ ከጦር ኃይል አቅም ጎን የፖለቲካው በጎ ፈቃድ አለ ወይ የሚሰኘው ነው። ከታሪክ እንደታየው፡ ላሽካር ኤ ታይባን ሁሌም ለፓኪስታን በህንድ አንጻር የውክልና ጦርነት የሚያካሂድላት አስተማማኝ ቡድን ሆኖ ነው የቆየው። ፓኪስታን ቡድኑን አሁንም ለዚሁ ዓላማዋ ማራመጃ ትጠቀምበታለች የሚለው ጥያቄ በወቅቱ በርግጥ አከራካሪ ቢሆንም፡ አጋጣሚውን ወደፊትም ክፍት አድርጋ መጠበቁን እንደምትፈልግ አያጠራጥርም።

ለህንዳዊው ሰንዲ ዋሴልካር ቀደም ሲል የተደመጠው ሀሳብ በአሁኑ ጊዜ በፓኪስታን የሚታየውን ችግር ገላጭ አድርገው ተመልክተውታል። በወቅቱ በፓኪስታን የተቋቋመው ሲቭል መንግስት ደካማ መሆኑን በህንድ እና በፓኪስታን መካከል ስለቀጠለው ውዝግብ ያጠናውና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርበው መንበሩን ሙምባይ ያደረገው የስትራቴጂክ ፎርሳይት ቡድን ተንታኝ ሰንዲፕ ዋስሌካር አስረድተዋል።

ፓኪስታን በጦር ኃይሉ ቁጥጥር ስር መገኘትዋ ላይ ነው መዋቅራዊው ችግር ያለው። እና የጦር ኃይሉ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል ሁሌ ፍጥጫ መፍጠሩ አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት አስር እና አስራ አምስት ዓመታት የአሸባሪዎች ቡድኖች የፓኪስታን መንግስት አካል ሆነዋል። እነዚህ ቡድኖችም፡ ልክ እንደጦር ኃይሉ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ውዝግብ እና የኃይሉን ተግባር ማስፋፋቱን ስራየ ብለው ተያይዘውታል። በህንድ በኩል ደግሞ፡ በቢሮክራሲያው አሰራር እንደተለመደው በጣም ዝግመት የሚታይ ሲሆን፡ የህንድ መንግስት ቆራጥ ርምጃ ለመውሰድ ድፍረቱ ተጓድሎት ይገኛል።

ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዴት ሊያበቃ መቻሉ አሁንም ማጠያያቅ ይዞዋል። ዩኤስ አሜሪካ፡ በተለይ ኢዝላማባድ በታሊባን አንጻር ለበሚካሄደው ትግል ላይ ማትኮር ትችል ዘንድ፡ በህንድና በፓኪስታን መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ትልቅ ፍላጎት አላት። የህንድና የፓኪስታንን ግንኙነት ለብዙ አሰርተ ዓመታት የተከታተለው የዋሽንግተን የውድሮው ዊልሰን ማዕከል ተንታኝ ዴኒስ ኩክስ ከውጭ የሚደረግ ግፊት ውጤት ማሰኘቱን አብዝተው ይጠራጠሩታል።

ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይመስልም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባለፉት ጊዚያት ሞክሮዋል። አሁንም ሙከራውን ለይስሙላ ቀጥሎዋል። ሆኖም፡ ሁለቱ ወገኖች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ይበጃል የሚሉትን ነው የሚያደርጉት።

ህንዳዊው ሰንዲፕ ዋስልካር ግን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በፓኪስታን አኳያ የሚከተለውን ፖሊሲ ከቀየረ አንዳንድ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ቶማስ ቤርትላይን/አርያም ተክሌ/ነጋሽ መሀመድ