1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዝብ ቆጠራ በኬንያ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 23 2001

ኬንያ ውስጥ ካለፈው ሰኞ ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የህዝብ ቆጠራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/JKmn
የኬንያ ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪምስል AP Photo

ይኸው አንድ ሳምንት የሚቆየው የህዝብ ቆጠራ በምስራቅ አፍሪቃዊቱ ሀገር ውስጥ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነው። በቆጠራው የሚገኘው መረጃ ባለፈው አሰርተ ዓመት በሀገሪቱ የተደረጉ ለውጦችን፡ ለምሳሌ ከተሞች የተስፋፉበትንና የኤድስ ተጽዕኖ ደረጃን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመገምገም እንደሚረዳው የኬንያ መንግስት ተስፋ አድርጎዋል።

ይሁንና በተዘጋጀው መዘርዝር ላይ የሰፈረው የኬንያውያኑን ነገድ የሚጠይቀው ጥያቄ በሀገሪቱ ትልቅ ክርክር አስነስቶዋል። ጥያቄው በተለይ፡ በኬንያ ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት ይፋ መሆን በኋላ ግጭት ከተነሳ ከአስራ ስምንት ወር በኋላ መጀመሩ ስህተት መሆኑን ነው ብዙዎቹ የሚናገሩት። አንዳንድ ሀያስያንም ከመዘርዝሩ የሚገኘው መረጃ አላግባብ ስራ ላይ እንዳይውል ስጋታቸውን ከወዲሁ እያሰሙ ነው። ሆኖም፡ የኬንያ መንግስት ቆጠራው የህዝቡን አሰባሰብ ለይቶ ለማወቅና የተሻለ ዕቅድ ለማውጣት ስለሚረዳ አስፈላጊ ነው ሲል ነበር የተከራከረው። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪም በኬንያ ቴሌቪዥን ባሰሙት ንግግራቸው ህዝቡ የቆጠራውን ሂደት እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

« የሀገሪቱ ህዝብ የሚቆጠርበት ጊዜው አሁን ነው። »

በዚሁ ከአስር ዓመት በኋላ ስለ ኬንያውያኑ መረጃ ለማሰባሰብ በመካሄድ ላይ ያለውን የህዝብ ቆጠራ ለማሳካት አንድ መቶ አርባ ሺህ ረዳቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ይሁንና፡ ህዝቡ የጥያቄውን መዘርዝር፡ በተለይ፡ ከየትኟው ጎሳ ነህ ነሽ የሚለውን ጥያቄ በደስታ ለመመለስ ዝግጁ አልሆነም፤ ባለፈው ዓመት ከምርጫው በኋላ የተቀሰቀሰው ኃይል የታከለበት ግጭት ትውስታ ከህዝቡ አዕምሮ ገና አልጠፋምና፡

« ከየትኛው ነገድ ወይም ጎሳ ነህ ብሎ መጠየቁ ተገቢ አይመስለኝም። ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ በኋላ ሁከት መነሳቱን አይተናል። እና ይህ በጥያቄው መዘርዝር የሰፈረው ጥያቄም ተመሳሳይ ግጭት እንዲነሳ ድርሻ ሊያበረክት ይችል ይሆናል።

ነበር ያለው የሀያ ዘጠኝ ዓመቱ ማታ ማታ በዘበኝነት የሚሰራው ዴኒስ።
የተለያዩት የኬንያ ብሄር/ብሄረሰቦች ለብዙ ሳምንታት ደም ያፋሰሰ ግጭት ማካሄዳቸው አይዘነጋም፤ በዚያን ጊዜ ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ የሚበልጥ ህዝብ ሲገደል ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ለቀው ተሰደዋል፤ አንዳንዶቹ እስከዛሬ ሁከቱ ካበቃ ከአንድ ዓመት በኋላም ወደ ትውልድ መንደራቸው መመለስ እንኳን አልቻሉም።

Nairobi Stadtansicht Kenia
ናይሮቢምስል picture-alliance / TPH Bildagentur / Spectrum

በዚህም የተነሳ አንድ በወቅቱ የተቋቋመ አንድ ቡድን ኬንያውያን አሁን በሀገራቸው በተጀመረው የህዝብ ቆጠራ ላይ ከየትኛው ነገድ መሆናቸውን የሚጠይቀውን ጥያቄ እንዳይመልሱ ዘመቻ ጀምሮዋል። ኬንያውያኑ ከየትኛው ነገድ መሆናቸውን የሚያሳየው የጥያቄ መዘርዝር ሌላ ድብቅ ዓላማ ሊኖረው እንደሚችል የቡድኑ ሊቀ መንበር ሬጊናልድ ኦኩሙ እያስጠነቀቁ ነው።

«ላንዳንድ ነገዶች የተለዩ ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ወይም መንገዶችን ለመስራት ስንል በዚህ የጥያቄ መዘርዝር መጠቀም ይኖርብና? ኬንያ ነጻነትዋን ከተጎናጸፈች ካለፉት አርባ ስድስት ዓመታት ወዲህ የተለያዩት ጎሳዎችዋ ተጋብተውና ተዋልደው ባንድነት ተዋህደው ይኖራሉ። ብዙዎቹ እንዲያውም የነገዳቸውን ቋንቋ እንኳን መናገር አይችሉም። »

ኦኩሙ እአአ በ 1984 ዓም በርዋንዳ የተፈጸመውን የጎሳ ጭፍጨፋ ያስታወሱት ኦኩሙ እንዳስረዱት፡ ርዋንዳ ውስጥ ከስምንት መቶ ሺህ የሚበልጡ የቱትሲ ጎሳዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተገደሉበት የጎሳ ጭፍጨፋ ሊካሄድ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ማ የየትኟው ጎሳ ነገድ አባል መሆኑን የሚያመለክት ዝርዝር ተዘጋጅቶ እንደነበር አስታውቀዋል። ኬንያም ባለፈው ዓመት ከፕሬዚደንታዊው ምርጫ በኋላ ካሳለፈችው መጥፎ ተሞክሮ በኋላ ተመሳሳይ ስህተት መፈጸም እንደማይኖርባት ነው ኦኩሙ ያሳሰቡት።

የኬንያ ብሄራዊ የመዘርዝር ተመልካቹ መስሪያ ቤት ግን በሁለቱ መካከል ተመሳሳይነት አለ ብሎ አያምንም። የዜጎች ነገድን የሚያስታውቅ የህዝብ ቆጠራ ሂደት ትክክለኛ ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው ኬንያዊው የብሄራዊ የመዘርዝር ተመልካቹ መስሪያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኮልንስ ኦፒዮ።

« ጥያቄው ባህላዊ ትርጓሜ ይዞዋል። ህዝቡ እንዴት ኑሮውን እንደሚመራ መረጃ ይሰጣል። የሚወለዱትንና የሚሞቱትን የሀገሪቱ ዜጎችን ቁጥር ለይቶ ለማወቅም ያስችላል። »
በዚያም ሆነ በዚህ ግን ዴኒስን የመሳሰሉ ብዙ ኬንያውያን የጥያቄ መዘርዝሩ ሊያስከትለው ይችል ይሆናል የሚሉትን ችግር ለማስወገድ የራሳቸውን መፍትሄ አዘጋጅተዋል።


« ከየትኛው ነገድ ትወለዳለህ ብለው ከጠየቁት፡ ግልጹን መልስ ይሰጣቸዋል። ኬንያዊ መሆኑን ይነግራቸዋል። »
መስሪያ ቤቱ ከአራት ወራት በኋላ የቆጠራውን የመጀመሪያ ውጤት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የመጨረሻ ውጤት ይወጣል። ይፋ የሚደረገው ውጤት ስለ ነገድ ጥያቄ በርግጥ ዝርዝር መረጃ ማቅረቡ በውል አይታወቅም።

አንትየ ዲክሃንስ/አርያም ተክሌ