1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሉባናጋ ብይንና የኮንጎ አስተያየት

ሰኞ፣ መጋቢት 10 2004

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የሄማ ጎሳ ሚሊሺያዎች ቡድን የቀድሞው መሪ ቶማስ ሉባንጋ ሕፃናትን ለውጊያው ተግባር በመልመል ለጦርነት አሰልፈዋል በሚል ዴን ኻግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ባቀረበባቸው ክስ ባለፈው ረቡዕ ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል የበየነበት ውሳኔው

https://p.dw.com/p/14Mk5
ምስል Reuters

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የሄማ ጎሳ ሚሊሺያዎች ቡድን የቀድሞ መሪ ቶማስ ሉባንጋ ሕፃናትን ለውጊያው ተግባር በመልመል ለጦርነት አሰልፈዋል በሚል ዴን ኻግ ኔዘርላንድስ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ባቀረበባቸው ክስ ባለፈው ረቡዕ ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል የበየነበት ውሳኔው ለፍርድ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክም ታሪካዊ ውሳኔ ሆኖ ታይቶዋል። በትክክልም፡ በምሥራቃዊው የሀገሪቱ ከፊል ለሚገኘውና እአአ ከ 1999    እስከ 2003 ዓም ድረስ በሄማ ጎሳ ሚሊሺያዎች እና በውሁዳኑ የሌንዱ ጎሳ መካከል ዘግናኙ ጭፍጨፋ ለታየበት አስከፊ የርስበርስ ጦርነት በተካሄደበት የኢቱሪ ክፍለ ሀገር ሕዝብም ወሳኝ ነበር። ፍርድ ቤቱ የዛሬ አሥር ዓመት ከተቋቋመ ወዲህ ብይን ሲያሳልፍ ይህ የመጀመሪያው ነበር። ሉባንጋ ወደ ዴን ኻግ የተዛወሩት በ 2006 ዓም ሲሆን ችሎታቸው የተጀመረው በ 2009 ዓም ነበር። በዚሁ አካባቢ  የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ሕዝብ የዴን ኻጉን ብይን እንዴት እንደተቀበለው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ዚሞነ ሽሊንድቫይን በኢቱሪ ክፍለ ሀገር ቡንያ በመገኘት ተከታትላዋለች።

የሀምሣ አንድ ዓመቱ ቶማስ ሉባንጋ ባቋቋሙት የኮንጎ ያርበኞች ህብረት ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ወደ ሀምሣ የሚጠጉ የፓርቲው ሰራተኞች፡ አባላት እና ከ ዓም ወዲህ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተባቸው የቶማስ ሉባንጋ ዘመዶች ራድዮ ከፍተው ብይኑን ሲጠባበቁ ነበር። የዴን ኻጉ ፍርድ ቤት ብይኑን በራድዮ ወይም በቴሌቪዥን በቀጥታ ያስተላልፋል የሚል ግምት ነበራቸው። ግን ለሳተላይቱ አገልግሎት ባለመከፈሉ ዜናውን ሊያደምጡ የቻሉት በኮንጎ ከተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ራድዮ ነበር።
 ሉባንጋ
ብይኑን እንደሰሙ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት የነበሩትና ሉባንጋ ነፃ ይሆናሉ የሚል እምነት ነው የነበራቸው ሁሉ ለተወሰነኑ ደቂቃዎች የሰሙትን ማመን አቅቶዋቸው ፀጥ ብለው ከቆዩ በኋላ፡ የፍርድ ቤቱ ተዓማኒነት አጠራጣሪ መሆኑን ነበር ያመለከቱት። የኢቱሪ ክፍለ ሀገር ምክር ቤት እንደራሴ እና የ የኮንጎ ያርበኞች ህብረት ፓርቲ ጠበቃ ፔሌ ካስዋራ ፍርድ ቤቱን የቅኝ ገዢዎች ፍርድ ቤት ሲል አጣጥለውታል።
« ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የፖለቲካ ተቋም ነው። ከሕግ ጋ የሚያገኛኘው ጉዳይ የለም። ዳኞቹ ሳይቀሩ ዲፕሎማቶች መሆናቸው ይህን የሚያረጋግጥ ነው። የተቋቋመው አፍሪቃውያንን፡ አፍሪቃውያን ባለሥልጣናትን ብቻ ለመፍረድ የተቋቋመ ነው። በፍርድ ቤቱ የቀረቡት አፍሪቃውያን ብቻ ናቸው፤ አንድም አውሮጳዊ ወይም አሜሪካዊ የለም። በኢቱሪ ተፈፀመ የሚባለውን ወንጀል ያካባቢ ፍርድ ቤት ቢመረምረው የተሻለ ይሆናል። መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ነበሩ ሕፃናቱን አግኝተው የመለመሉዋቸው፡ ያሰለጠኑዋቸው እና በመጨረሻም ሉባንጋ የመለመሉዋቸው ወታደሮች መሆናቸውን እንዲናገሩ የገፋፉዋችው። »
ይህ፡ ማለትም ምስክሮች የዓቃቤ ሕጉ ቡድን ክሱን የሚደግፍለት ቃል እንዲሰጡ ተፅዕኖ አሳርፎባቸዋል የሚለው ዓይነቱ የመከራከሪያ ሀሳብ በኢቱሪ ክፍለሀገር አዘውትሮ ተሰምቶዋል። ለዚህም ነበር የዴን ኻጉ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በተለይ በሉባንጋ አንጻር ቃላቸውን የሰጡትን ምስክሮችና የሉባንጋ ሚሊሺያዎች ፈፀሙት የተባለው ወንጀል ሰለባዎችን ከዓቃቤ ሕግ ቡድን ጋ ያገናኙት ወገኖችን በጥብቅ የወቀሰው። ምክንያቱም የኮንጎ ያርበኞች ህብረት ፓርቲ መሥራች ቶማስ ሉባንጋ የሄማ ጎሳቸው  ሚሊሺያ ቡድን በውሁዳኑ የሌንዱ ጎሳ ላይ በፈፀሙት ጭፍጨፋ ሳይሆን የአሥራ አንድና አሥራ ሁለት ዓመት ሕፃናትን በግዳጅ ለውጊያው ተግባር መልምለዋል በሚል ነው ፍርድ ቤት ክስ የመሠረተባቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ወታደሮች ሉባንጋ ለውጊያ ተግባር በግዳጅ መልምለዋቸዋል በሚል የቀረበውን ክስ፡ አሁን የሀያ አራት ዓመት ጎልማሳ የሆነ አንድ የቀድሞ ወታደር ብዙዎቹን አቻዎቹን በመወከል ሀሰት ሲሉ አስተባብለውታል።  
« የዛሬው ዕለት የተረጋጋ ነው። አዎ በውትድርና አገልግያለሁ። የኮንጎ ያርበኞች ህብረት ፓርቲ በውትድርና ሲወስደኝ አሥራ ሁለት ዓመቴ ነበር፤ ስወጣ ደግሞ አሥራ ስምንት ዓመቴ ነበር። ወላጅ አልባ ነበርኩ። እና በውዴታ ነው የተመለ,መልኩት፤ ያስገደደኝ አልነበረም። በዚያን ጊዜ በሕይወት ሊያቆየኝ የሚችል ነገር አልነበረም። እንዳልኩት ወላጆቼ ሞተውብኝ ነወር። »
የተመድና መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ብይኑ በጎሳዎች መካከል ግጭቱን እንደገና ይቀስቅስ ይሆናል በሚል ሰግተው ነበር። ግን በተለይ ችሎቱ ብዙ ዓመት በመፍጀቱ እና የሌንዱ ጎሳ አባላትም ክሱ ሲመሠረት እነሱን የሉባንጋ ሚሊሺያዎች ጭፍጨፋ ሰለባ አድርጎ ያላየበትን ውሳኔ መቀበል ግድ ስለነበረባቸው  በቡንያ የተፈራው ሁከት አልተፈጠረም። በአንፃሩ ሁሉ ሰላም እንደነበር የሌንዱ ጎሳ ቃል አቀባይ ፍራንስዋ ዳዳ ገልጾዋል።
« ጊዜ ራሱ በጎሳዎቹ መካከል ያለው ልዩነት እንዲቆም ድርሻ አበርክቶዋል። ሕዝቡ ዕለታዊውን ኑሮውን ከመግፋቱ ጋ ነው የሚታገለው። ጦርነት እስከሌለ ድረስ ሕዝቡ ባለፉት ዓመታት የደረሰበትን በደል ረስቶዋል። ብይኑ ውዝግቡን አብቅቶዋል ብለን እናምናለን። በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ላይ እምነት አለን። ይህንን ብንልም ግን በደስታ እንፈነድቃለን ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ከሳሾች እኛ አልነበርንምና። »   
ክሱን የመሠረተው የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ልዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ ሉባንጋን ጥፋተኛ መሆናቸውን ያረጋገጠው ብይን ከተሰማ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተከሳሹ ብዙ ዓመት የሚቆይ የእሥራት ቅጣት ያሰጋቸዋል። ምንም እንኳን የትኛውም ከባድ ቅጣት የግዳጁ ምልመላ ሰለባ የሆኑት ሕፃናት የደረሰባቸውን የዕድሜ ልክ ሥቃይ ባይቀንስም።  
« ጥያቄው  የብዙ ሕፃናትን ሕይወት ላበላሸ ግለሰብ ትክክለኛው ቅጣት የቱ ነው የሚለው ነው። ስንት ዓመት? ሉባንጋ በግዳጅ ለመለመሉት ለያንዳንዱ ሕፃን በአንድ ዓመት እሥራት ይቀጡ ካልን ፍርድ ቤቱ ከወሰነው ከፍተኛው የሠላሣ ዓመት እሥራት ቅጣት በላይ ሊደርስ ነው። በመግቢያው መግለጫችን እንዳስታወቅነው፡ ከፍተኛው የእሥራት ቅጣት እንዲበየንባቸው ነው የምንጥረው። »
የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክም መንግሥት ፍርድ ቤቱ በሉባንጋ ላይ ለሌሎች የጦር ወንጀልና ነፍስ ግድያን ለማራመድ ለሚፈልጉት ሁሉ መቀጣጫ የሚሆን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚያሳልፍ ተስፋ ማድረጉን የፍትህ ሚንስትሩ ኤማኑዌል ሉሶሎ ባምቢ ገልጸዋል። 

Niederlande UN-Gerichtshof Luis Moreno-Ocampo zu Sudan Darfur
ልዊስ ሞሬኖ ኦካምፖምስል AP
Lubanga Prozess Bilder Reaktionen
የሉባንጋ ደጋፊዎች ብይኑን ለመስማት ሲጠባበቁምስል Simone Schlindwein

አርያም ተክሌ

ዚሞነ ሽሊንድቫይን

መሥፍን መኮንን

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ