1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ሽግግርና የዉጪዉ ጫና

ሰኞ፣ ነሐሴ 23 2003

ከሊቢያ ጋር በረጅም ጊዜ የሚደረገዉ የንግድና የምጣኔ ሐብት ግንኙነትም ፕሮፌሰር ሮላንድ ማርሻል እንደሚሉት በየሐገራቱ የሸቀጥ አቅርቦትና ፍላጎት፥ በየዘመኑ ገበያና በሸቀጡ ጥራት የሚበየን ነዉ-የሚሆን።እስካሁን ለቃዛፊ የጦር መሳሪያ ስትቸበችብ የነበረችዉ ሞስኮያ ከእንግዲሕ ፓሪስ፥ ለንደን፥ ዋሽንግተኖች የሚከፍቱትን ቀዳዳ ማነፍነፍ ግዷ ነዉ።

https://p.dw.com/p/Rihf
ምጪዉ፦ሙስጠፋ አብዱጀሊልምስል picture alliance/landov

የሐኒባል መሸጋገሪያ፥ የሮሞች ጉዞ ማሳረጊያ፥ የሙስሊሞች መረማመጂያ፥የቱርኮች፥ የአዉሮጶች መደርጂያ፣ መጠናከሪያ፥ የዑመር ሙክታር መፋለሚያይቱ ሐገር አሮጌ ገዢዋን አሰናብታ ላዲስ ተሞሽራለች።ሊቢያ።የዜጎችዋ ምኞት አሮጌዉን አሠናብተዉ አዲስ የሚተኩላት ወገኖች ፍላጎትን እንዴት ታስተናግድ ይሆን?የሊቢያ ሽግግር መነሻ ያለፈ ታሪኳ ማጣቀሻ፥ የምዕራቡ ዓለም አቋም መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የአፍሪቃ ሕብረት እንደ ሕብረት አሁንም ሁሉም የሊቢያ ተፋላሚ ሐይላት ተደራድረዉ የጋራ የሽግግር መንግሥት ይመስርቱ እንዳለ ነዉ።ከአፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ቁንጮዋ፥ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባሊቱ ደቡብ አፍሪቃ የሕብረቱን የጋራ አቋም በጠንካራ ምክንያት ትደግፋለች።የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ያኮብ ዙማ ደጋግመዉ እንዳሉት የዓለም ሐያል-ሐብታም ሐገራት በአፍሪቃን የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል።

«የበለፀጉት ሐገራት የተደረገዉን ስምምነት ጥሰዉ በአፍሪቃ የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መወሰናቸዉን ከምናይበት ሁኔታ ዉስጥ ነን።ስምምነት የተደረገበት (የተመድ) ዉሳኔ ፍፁም ተቀባይነት በሌላዉ ሁኔታ ተጥሷል።»

አንዳድ የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎችና የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ደቡብ አፍሪቃ ቃዛፊን የምትደግፈዉ ሐገሪቱ በጥቂት ነጭ-ዘረኞች ትገዛ በነበረበት ወቅት ለጥቁሮችና ክልሶች የእኩልነት መብት ይታገሉ የነበሩ ሐይላትን የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መንግሥት ይደግፍ ሥለነበረ ነዉ።የደቡብ አፍሪቃዉያን የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ኤ ኤን ሲን) ትግል የማይደግፍ አፍሪቃዊ ነበር ወይ ነዉ ጥያቄዉ።

ኔልሰን ማንዴላን በድፍን ዓለም የሠላም አብነት፥ የእኩልነት ቀንዲል፥ የመቻቻል ቁንጮ ያደረገዉን ያን ትግል ቃዛፊ ያኔ በመደገፋቸዉ አሁን ከተደገፉ ጥፋቱን በምክንያት ማስረገጥ ሲበዛ ከባድ ነዉ።

ያምሆኖ ኢትዮጵያ እስከ ናጄሪያ፥ ከግብፅ እስከ ሩዋንዳ ያሉ የአፍሪቃ ሐገራት ግን ከሕብረታቸዉ ዉሳኔ ተንሸራተዉ ሠልፋቸዉን ዙማ «ዉሳኔ የጣሱ» ካሉት ሐያል ዓለም ጋር አስተካክለዋል።ያረጁ፥ ያፈጁትን ቃዛፊን ተቃዉመዉ «ብሔራዊ የሽሽግግር ምክር ቤት» የተሰኘዉን የዘመኑን-ዘመነኛ ሐይል ደግፈዋል።

Libyen durchlöcherte Muammar al Gaddafi Plakat in Tripolis
ቃዛፊ-ማዓሠላማምስል dapd

በእርግጥም የዚያች በረሐማ ሠፊ፥ ሐብታም ሐገር ገዢ፥ አብዮታዊ መሪ፥ የአፍሪቃ ንጉሰ ነገስት የአርባ ሁለት ዘመን የገዢነት ጉዞ ሩጫቸዉን ጨርሰዋል።ሕይወታቸዉ እንጂ አገዛዛቸዉ አልሞተም ማለት ያሳስታል።ጠላቶቻቸዉ ትሪፖሊ ላይ የፈጠረቋትን ሕልቅታቸዉን ተወለደዉ-ባደጉባት ሲርት ላይ በጥሶ ለመጣል ወደዚያዉ እየገሰገሱ ነዉ።«እዚያ ዉጊያ ይገጥመናል ብዬ አልጠብቅም።የሲርት ልጆች እኛን ይደግፋሉ።ገሚሶቹ በፊትም አማፂ ቡድን መስረተዋል።የሚያምኗቸዉን ሰዎች መርጠዋልም።ሁከትና ጥፋትን መከላከል ይሻሉ»

የብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሙስጠፋ አብዱል ጀሊል።እናም ሊቢያዉያን ብዙዎች እንደሚያምኑት ምናልባት በኢድ አል-ፊጥር ማግስት ዘመነ-ቃዛፊ ለነበር ዝክር ከቤተ-መዘክር መወርወራቸዉ አይቀርም።

ከአፍሪቃዉያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ክስመት፥ ከአረብ-ሙስሊሞች ጠንካራ ክንድ ዝለት፥ ከሮሞች ዉድቀት በኋላ እስካሁን የነበረና ያለዉ የሊቢያ ማንነት ከሊቢያዉን እኩል የአረቦች፥ የቱርኮች፥ የምዕራቦች፥ ከምዕራቦች መሐል የጣሊያኖች አገዛዝ የፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ ጥቅም ዉጤት ነዉ።

እርግጥ ነዉ ጣሊያኖች እብዙ ሥፍራ ተከፋፍለዉ የሮማ አያት ቅድመ አያቶቻቸዉን የሐያልነት ገድል-ድልን ለምዕተ-ዓመታት ከመተረክ ሕልማቸዉ በአስራ-ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ማብቂያ ሲባንኑ ሮሞችን የተኩት ቱርኮች፥ የጥንቶቹ የሮማ ገባሮች ብሪታንያና ፈረንሳ ዓለምን አስገብረዉ ጠበቋቸዉ።ጣሊያኖች እንደነሱዉ ሁሉ ዘግይተዉ ከደረጁት፥አርፍደዉ ከነቁት ጀርመኖች ጋር አብረዉ አይሪቃን ለመቀራመት ሲንጠራሩ አይናቸዉ ከግዛታቸዉ አምስት መቶ ኪሎ ሜትር ከምትርቀዋ ከቱርክ ቅኝ ተገዢ ግዛት ላይ አረፈ።

የአስራ-ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ-ዘመን ፍፃሜ፣ ከ1229 ጀምሮ ከስድስት መቶ ዓመታት በላይ ገሚስ ዓለምን ለገዛዉ ለገናናዉ የኦስማን ቱርክ ሥርወ-መንግሥት ፍፃሜ መጀመሪያ ዘመን ነበር።ከሰሜን አፍሪቃ ጫፍ ሞሮኮ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፣ የሚገኙትን ሐገራት ቅኝ የምትገዛዉ ፈረንሳይ የጣሊያኖች አይን ያረፈባቸዉን የቱርክ ቅኝ ተገዢ ግዛቶችን ከሰፊ ግዛትዋ ለመቀየጥ የቱርኮችን ዉድቀት አድፍጣ የምትጠብቅበት ወቅትም ነበር።

በዚሕም ምክንያት ጣሊያኖች ኋላ ሊቢያን የመሠረቱትን የትሪፖሊታንያ፣ የባርካ እና የፌዛን ግዛቶችን ከቱርኮች ለመረከብ መከጀላቸዉን ፈረንሳዮች እንደ ጥቅም ሽሚያ ነበር ያሉት።ፈረንሳዊዉ የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር ሮላንድ ማርሻል እንደሚሉት ያኔ ሊቢያ የተጀመረዉ የአዉሮጳዉያን የጥቅም ሽሚያ እስካሁንም እንደቀጠለ ነዉ።


«እኒያ ፉክክሮች ነበሩ በቃዛፊ ዘመንም ቀጥለዋል።እንዳዲስ የሚጋነኑ አይደሉም።»

ብቻ ጣሊያኖች ያኔ ፈረንሳዮችን ለመርታት ያገኙት አቋራጭ ሰወስቱን ግዛቶች ካለቀቁላቸዉ ሞሮኮን እንዲለቁላቸዉ መጠየቅ ነበር።ከብዙ ዉይይት በሕዋላ ሰወስቱን ግዛቶች ጣሊያኖች እንዲቆጣጠሩ፣ ሞሮኮን ፈረንሳዮችን እንደያዙ እንዲቀጥሉ የሁለቱ ቅኝ ገዢዎች ሹማምንት ተስማሙ።ታሕሳስ 1900።
በአስራ-ሁለኛዉ አመት ኢጣሊያ አግያን ባሕር ላይ የሚገኙ ደሴቶችን ለቱርክ ስትለቅ ቱርክ ባንፃሩ ሰወስቱን ግዛቶች ለኢጣሊያ አስረከች።1912።

የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች እንደ ሁሉም የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች በየደረሱበት ሐገራት ሕዝብ ላይ እንደፈፀሙት ሁሉ የሊቢያን ሕዝብ ፈጅተዉታል።ረግጠዉታል። አግዘዉታል።ዑመር ሙክታር የመሩትን የነፃነት ትግል ለመደፍለቅ የኢጣሊያ ቅኝ ገዢ ጦር በከፈተዉ ዘመቻ ብቻ ኢላን ፓፔ የተሰኙ የታሪክ አጥኚ እንደፃፉት በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሊቢያዊ ፈጅቷል።የዚያኑ ያክል ሊቢያ ነፃነትዋን ከተቀዳጀች ከ1951 ጀምሮ የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅ እስከተቀሰቀሰበት እስካለፈዉ የካቲት ድረስ ከኢጣሊያ ጋር የነበራትን አይነት ግንኙነት ከየትኛዉም ምዕራባዊ ሐገር ጋር ኖሯት አያዉቅም።

ከየካቲት በሕዋላ ግን ለጣሊያኖች ቤንጋዚ ላይ ያቀርቶ ሌላ ታሪክ መጥቶ አይነት ሳይዘፈንላቸዉ አልቀረም።የሊቢያ መንግሥት እያለ ለሊቢያ አማፂያን የርዕሠ-ብሔርነት ዕዉቅና በመስጠት የዓለምን የዲፕሎማሲ ታሪክ የቀየሩት፥ ሊቢያን እንድትቀጣ፥ እንድትደበደብ ያስወሰኑት፥ ፕሬዝዳት ዙማ ተጣሰ ባሉት ዉሳኔ ሰበብ ከአማፂያኑ ወግኖ ሊቢያን የሚደበድብ ጄት ቀድመዉ ያዘመቱት ሜሱ ሳርኮዚ እንጂ ሲኞር ቤርሎስኮኒ አይደለም።

ሳርኮዚ ወድሞቻችን ያሏቸዉ አማፂያን እስከፈለጉ ድረስ ወታደራዊዉ ዘመቻ እንደሚቀጥል ባለፈዉ ሐሙስ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

«የሊቢያ ወንድሞቻችን እስከፈለጉ ድረስ ወታደራዊዉን ዘመቻ ለመቀጠል ፍቃደኞች ነን።ይሕ ማለት አፀፋ ጥቃት እስካለ ድረስ በተመድ ዉሳኔ ቁጥር 173 መሠረት የሊቢያ ወዳጆቻችን ለመደገፍ ፈረንሳይ ዝግጁ ናት።»

በፕሬዝዳት ሳርኮዚ ማብራሪያ መሠረት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ወዳጅ-ጠላት ብሎ የፈረጀዉ ነበር ማለት ነዉ። በዚሕም ብሎ በዚያ ፈረንሳዮች በ1900 እየቆጠቆጣቸዉ ለኢጣሊያኖች አሳልፈዉ የሰጧትን ሊቢያን ዘንድሮ የዘመኑ-ሐያል ዓለም በሚፈቅደዉ የፖለቲካ፥ የዲፕሎማሲ መርሕ፥ በሚፈቅደዉ የቋንቋ ጨዋታን-አስልተዉ ከጃቸዉ አስገቧት።

የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የአረብ ሶሻሊስታዊ አብዮት መርሕ-መፈክር የሊቢያን ሕዝብ በየአደባባዩ በሚያስቦርቅበት፥ የአረብ አፍሪቃ ወጣት ልብ በሚያማልልበት፥ከደቡብ አሜሪካ እስከ ፍልስጤም፥ ከኤርትራ እስከ ደቡብ አፍሪቃ፥ ከሰሜን አየርላንድ-እስከ ባስክ የሚገኙ አማፂያን ትሪፖሊን ደጅ በሚጠኑበት በ1970ዎቹ የቃዛፊ የቂል በትር ከዋሽንግተን ቀጥሎ ለንደን ላይ ነበር-ያረፈዉ።

ቃዛፊ ሊቢያ የሚገኘዉን የብሪታንያ የነዳጅ ኩባንያን የብሪቲሽ ፔትሮሊየም (BP) ንብረትን በሙሉበ1971 ወረሱ።በዚያዉ ዓመት ብሪታንያ ባንኮች ዉስጥ የነበረዉ የሊቢያን ሐብት በሙሉ አስወጡ። ለለንደኖች የቅርብ ቀንደኛ ጠላት ለአየር ላንድ ሪፐብሊካን ጦር (IRA) የጦር መሳሪያና ገንዘብ ያንቆረቁሩ ገቡ።ዘንድሮ ያረጀ-ያፈጀዉን የቃዛፊን ሥርዓት ለመፈንገል ሊቢያዎች አንድ-ሲሉ ፈረንሳዮች ሁለት፥ ብሪታንያዎች ሰወስት የማይሉበት ምክንያት በርግጥ አልነረም።

ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን የሊቢያን አማፂያንን እንደ ሳርኮዞ ወዳጆቻችን ለማለት አልደፈሩም።አማፂያኑ የቃዛፊን ርዕሠ-መንበር እንዲረከቡ ብሪታንያ ዙሪያ መለስ ድጋፍ መስጠቷን እንደምትቀጥል ግን አልሸሸጉም።

«በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ምክር ቤትም ዉስጥ አዲሶቹ የሊቢያ ባለሥልጣናት የሚፈልጉትን ሕጋዊ፥ ዲፕሎማሲያዊ፥ ፖለቲካዊና ገንዘባዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አስቀድመን እርምጃ እንወስዳለን።የታገደዉ የሊቢያ ሕዝብ ገንዘብ በቅርቡ እንዲለቀቅ እናደርጋለን።»

Flash-Galerie humanitäre Krise in Libyen
ሊቢያ ዛሬምስል dapd

ከሊቢያ ጋር በረጅም ጊዜ የሚደረገዉ የንግድና የምጣኔ ሐብት ግንኙነትም ፕሮፌሰር ሮላንድ ማርሻል እንደሚሉት በየሐገራቱ የሸቀጥ አቅርቦትና ፍላጎት፥ በየዘመኑ ገበያና በሸቀጡ ጥራት የሚበየን ነዉ-የሚሆን።እስካሁን ለቃዛፊ የጦር መሳሪያ ስትቸበችብ የነበረችዉ ሞስኮያ ከእንግዲሕ ፓሪስ፥ ለንደን፥ ዋሽንግተኖች የሚከፍቱትን ቀዳዳ ማነፍነፍ ግዷ ነዉ።

በአጭር ጊዜዉ ዳግም ግንባታ፥ በሥልጠናና የአዲስ መንግሥትን መዋቅርን በመዘርጋት-ማማከሩ መስክ ደግሞ ማርሻል እንደሚሉት ግንባር ቀደሞቹ ፈረንሳይና ብሪታንያ ናቸዉ።

«ባጭር ጊዜ በርግጥ ብሪታንያና ፈረንሳይ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ኮንትራቶችን በበላይነት ለመዉሰድ መሞከራቸዉ አይቀርም።በረጅም ጊዜ ግን የንግድ ግንኙነት የሚወሰነዉ ሰዎች በሚያቀርቡት ሸቀጥ ጥራት ነዉ።ምናልባት ጣሊያኖች በሊቢያ ምጣኔ ሐብታዊና የንግድ መደብ እስካሁን የዘረጉት መዋቅር ሥላለ የአጭር ጊዜዉ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል።ሥለዚሕ ጣሊያን በሆነ ጊዜ የቀድሞ ስፍራዋን ልታረጋግጥ ትችላለች።አሁን ግን ትርዒቱን የሚመሩት አቶ ካሜሩንና አቶ ሳርኮዚ ናቸዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት በጋራ እንዳሉት አዲሱ የሊቢያ መንግሥት ልክ እንደ ቃዛፊ ሁሉ የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይሻገሩ የባሕር በሩን መዝጋት አለበት።ልክ እንደቃዛፊ ሁሉ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን ማሰር ወይም የሜድትራኒያን ባሕር አካባቢ እንቅስቃሴያቸዉን መቆጣጠርም ግድ አለበት።ከቃዛፊ ምዕራባዉያን ደጋግመዉ እንዳሉት በርግጥ መወገድ አለባቸዉ።ስደተኛን የማገት፥ ተጠርጣሪን የማሰር መርሐቸዉ ግን ይቀጥላል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ