1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ቀውስ

ዓርብ፣ የካቲት 18 2003

የሊቢያው ቀውስ ተቀጣጥሏል። ሞአመር ጋዳፊ አልቄይዳ ሊቢያን እየበጠበጠ ነው ይላሉ። አብዛኞቹ የምስራቅ ሊቢያ ከተሞች በተቃዋሚዎች እጅ ላይ ወድቀዋል።

https://p.dw.com/p/R4Hp
ምስል picture alliance/dpa

በሊቢያ የተቀሰቀሰው አመጽ ወደ ከፋ ዕልቂት ከተቀየረ ወዲህ ዓለም ዓቀፉማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ግፊቶች ከየአቅጣጫው እየበረከቱ ናቸው። የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ ባለፈው ማክሰኞ 75 ደቂቃ የፈጀ ዲስኩር ካሰሙ በኋላ ሁኔታዎች ከመርገብ ይልቅ ከረውና ተባብሰው ቀጥለዋል። ጋዳፊ ትላንት በመንግስት ቁጥጥር ስር ለሚገኘው ቴሌቪዥን ጣቢያ በስልክ በሰጡት መግለጪያ ከሊቢያ ብጥብጥ ጀርባ አልቄይዳ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሊቢያ በአደገኛ ሁኔታ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ታመራለች የሚለው ስጋት በተጠናከረበት በአሁኑ ወቅት መንግስታት ስለሚወስዱት እርምጃ አንድ አቋም መያዝ አቅቶአቸው ገና እየተነጋገሩበት ነው።የሊቢያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መሳይ መኮንን ዘገባ አለው።  

ሊቢያ በህዝብ ተቃውሞ፤ በታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ ትናጥ፤ ትታመስ ይዛለች። ዛሬ 11ኛ ቀኗ ላይ ትገኛለች። ከየአቅጣጫው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ጋዳፊ ቁልፍ የሚባሉ ትልልቅ ከተሞች ከእጃቸው ወጥተዋል። ትላንት ከርዕሰ ከተማዋ ትሪፖሊ በ50 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዝ ዛዊያህ በተሰኘች የሊቢያ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ በሚገኝባት ከተማ በመንግስትና በታጠቁ ተቃዋሚዎች መሃል የተደረገው ከባድ ወጊያ የጋዳፊን ዳጃፍ ያንኳኳ መስሏል።

አትሞ

በትላንቱ የአዝ ዛዊያህ ውጊያ 100 ሰዎች እንደተገደሉና ወዲያውኑ እንደቀበሩዋቸው የአይን እማኞች ሲገልጹ ዛሬ የወጡ ሪፖርቶች ግን የተገደሉት 25 ብቻ እንደሆኑ የሚያሳዩ ናቸው። አንድ የአዝ ዛዊያህ ነዋሪ ለአልጀዚራ በስልክ እንደገለጹት የጋዳፊ ሃይሎች ሰላማዊ ሰዎች ፊትለፊት ተኩሰው ሲገድሉ ነበር።

ድምጽ

«ተኩሱን እንዲያቆሙ ተማጸናቸው። ነገር ግን አላቆሙም። የሚተኩሱት በቀጥታ ወደ ህዝቡ ነበር። ጭቅላት እየመቱ ነበር የሚገድሉት። ያመለጣቸውንም አባረው ይገድሉ ነበር። እናም ህዝቡን ይገድላሉ። እንዲሸበርም ያደርጋሉ።»

ያለፈው ማክሰኞ አረንጓዴውን የሊቢያ ህገመንግስት እያሳዩ ለ75 ደቂቃዎች በማስፈራሪያ የታጀበ ዲስኩር ያቀረቡት የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ ትላንትም ድምጻቸውን አሰምተዋል። ማክሰኞ ዕለት እንደ ብዙዎች ግምት ምሽግ ከሚመስል ኮንክሪት ህንጻ ውስጥ ሆነው ነበር ጋዳፊ በቁጣ እየተርገፈገፉ ከአረንጓዴው ህገመንግስታቸውም እያጣቀሱ በእኔ ላይ የተነሳ ፍርዱ ሞት ነው ሲሉ የነበሩት ። ትላንት ግን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሳይሉ በስልክ ነበር የተናገሩት። እንደማክሰኞው ባያስፈራሩም፤ የምዕራባውያንን ቀልብ ለማግኘት በሚመስል መልኩ ጣታቸውን አልቄይዳ ላይ ጠንቁለዋል። ከዚህ ሁሉ ብጥብጥና ዕልቂት ጀርባ አልቂይዳ አለ--አሉ ጋዳፊ ትላንት በስልክ።

ድምጽ

«ይህ ሁሉ የሆነው በአልቄይዳ ፍላጎት ነው። እናንተ የአዝ ዛዊያህ ነዋሪዎች፤ የተከበረውን የጃማህሪያ መመሪያ በቢን ላደን እየቀየራችሁ ነው። ቢንላደን በሊቢያ አከባቢ ብጥብጥ ለመፍጠር ለወራት ሲዘጋጅ ነበር። ልጆቻችሁን በመጠቀም ዕልቂት የሚፈጠርበትን ሴራ ሲጎነጉን ነበር። ቢን ላደንና ተከታዮቹ ናቸው ልጆቻችሁን አስታጥቀው ዕልቂቱን የሚፈጽሙት። ያዝዋቸውና ለፍርድ እንዲቀርቡ አድርጓቸው።»

Libyen Unruhen Protest Demonstration Tripolis
ምስል APTN/AP/dapd

ጋዳፊ በስልክ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ የፈለጉበት ምክንያት ምንአልባት የተቃዋሚዎች ወደ ትሪፖሊ መጠጋት ለደህንነታቸው አስግቶ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል። ሆኖም የሊቢያን የዕልቂት ምክንያት ሰበቡን ጠምዝዘው ከአልቄይዳ ጋር ማላተማቸው በተለይ ምዕራባውያን ሀገራት በእሳቸው ላይ ማዕቀብ ለመጣል በሚነጋገሩበት ጊዜ ላይ መሆኑ አነጋግሯል። 20 ደቂቃ  በወሰደው የጋዳፊ የስልክ መልዕክት አልቄይዳን የሊቢያ ዕልቂት ተጠያቂ ቢያደርግም ከምዕራባውያን ዘንድ እስከአሁን የተሰጠ ምላሽ የለም። ሊቢያ 11ኛ ቀኑን በያዘው ቀውስ አብዛኞቹ የምስራቅና ምዕራብ ክፍሎቿ በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር ገብተዋል። ሚስራታ የተሰኘች ሶስተኛ የሊቢያ ትልቋ ከተማም ከጋዳፊ መዳፍ ልትወጣ ከጫፍ ደርሳለች። ሚስራታን ለመያዝ ዛሬ ተቃዋሚዎቹ ከጋዳፊ ሃይሎች ጋር እየተናነቁ ናቸው። በቱኒዚያ ድንበር ላያ በምትገኘው አራተኛዋ ትልቅ ከተማ ዞዋራ  የጋዳፊ አስተዳደር መፍረሱም ተረጋግጧል። የዞዋራ አንድ ነዋሪ እንደሚለው

ድምጽ

«ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረናል። ፖሊስ ጣቢያውን፤ የደህንነት ማዕከሉን ሁሉንም ቦታዎች።»

በእርግጥ በጋዳፊ ሙሉ ቁጥጥር ስር የምትገኝ ከተባለች ምናልባት ርዕሰ ከተማዋ ትሪፖሊ ትጠቀስ ይሆናል። በዚያም ቢሆን ዛሬ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ከስፍራው የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ጋዳፊ ከመጨረሻው ይዞታቸው የሚፈነቀሉበት ሰዓት በጣም እየተቃረበ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ። በእርግጥም ዛሬ ትሪፖሊ ውጥረት ነግሶባት ውላለች። ሰላማዊ ሰው መገደሉ እንደመሰንበቻው ዛሬም ቀጥሏል።

አትሞ

በእርግጥ ኮነሬል ሞአመር ጋዳፊ በቀላሉ እጅ የሚሰጡ አይመስሉም። ልጃቸው አንድ ጥይት አንድ ሰው እስኪቀር ካሉ በኃላ እሳቸውም ሞቴ እዚሁ ነው ብለው ከገለጹ ወዲህ ጠንከር ያለ አጸፋዊ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል። ዋንኛ የአመጹ እምብርት በሆነችውና ከእጃቸው ከወጣች ሳምንት ባለፋት ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ቤንጋዚ ላይ ጥቃት ከፍተዋል። ግን የተሳካላቸው አልሆነም። ቤንጋዚዎች ከጋዳፊ ተገላገልን ካሉ በኋላ ፌሽታ ላይ ናቸው። በደስታ የሰከረ አንድ የቤንጋዚ ነዋሪ ነጻ ውጥተናል ይላል።

ድምጽ

«ነጻ። ይህ ሁሉ በቃ! ስሜቴ ነጻ ነው»

ጋዳፊ በቤንጋዚ ዳግም ቢመጡ በእርግጥ አንድ የታጣቂዎች አለቃ እንዳለው እስከ ሞት እንዋጋለን።

ድምጽ

«ህዝቤ እየሞተ ነው። ጋዳፊ እየገደለን ነው። እስከምንሞት እንዋጋለን።» 

ሁኔታዎች ተካረዋል። ሊቢያ እየነደደች ሆና አስራአንደኛ ቀኗን ሸኘች። ጋዳፊ በገንዘብ ስጦታና በደሞዝ ጭማሪ በመደለል ደጋፊዎቻቸው የሞት ሽረት ትግሉን እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል። የሚከዷቸው ባለስልጣናቶቻቸው ቁጥር እየጨመረ ነው። ዛሬ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጋዳፊ ወንጀለኛ ነው ብለው ከጎናቸውም እንዳልሆኑ ገልጸው ከድተዋል። ሰው እያለቀ ስደቱ በተጧጧፈበት በዚህን ጊዜ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለሚወስደው እርምጃ ከአንድ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳቃተው አለ። በእርግጥ በሊቢያ የሚገደለው ሰው ቁጥር ጨምሯል። 2000 ሺህ ደርሷል። ኧሁንም ሊቢያ እየጬሰች ናት።    

መሳይ መኮንን

ሂሩት መለሰ