1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊቢያ ዉጊያ፤ኔቶና የድርድር ጥያቄ

ማክሰኞ፣ የካቲት 29 2003

ሕዝባዊ ሠላማዊ አመፅ ወደ ጠመንጃ ዉጊያ ከተቀየረ ወዲሕ ግን ሕዝባዊዉ ድል በመጀመሪያ ፍጥነቱ አልቀጠለም።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊም የአመፁባቸዉን ሐይላት በሐል ከመደፍለቅ አላመነቱም።ታንክ፥ መድፍ፥ ተዋጊ ጄት፥ ሔሊኮብተር፥ የታጠቀዉ የቃዛፊ ታማኝ ጦር አማፂያኑ የሚቆጣጠሯቸዉን ከተሞች እያጠቃ ነዉ።

https://p.dw.com/p/R7Dx
አማፂያኑ-ቢን ጀዋድምስል picture alliance/dpa

የሊቢያዉ መሪ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ታማኝ ጦርና የሐገሪቱ አማፂ ሐይላት ምሥራቃዊ ሊቢያ የሚያደርጉት ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።የቃዛፊ ታማኞች ትናንት ሁለት የምሥራቃዊ ሊቢያ ሥልታዊ ከተሞችን ከአማፂያኑ እጅ አስለቅቀዉ ተቆጣጥረዋል።በሌሎች ከተሞች የሚደረገዉ ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።በዉጊያዉ መሐል የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መልዕክተኞች ከአማፅያኑ ጋር ለመደራደር መጠየቃቸዉን አንድ የአማፂያኑ ቃል አቀባይ አስታዉቃል።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሐገራት በሊቢያዉ ዉጊያ ጣልቃ መግባት በሚለዉ ሐሳብ ላይ የጋራ አቋም አልያዙም።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።

የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን አገዛዝን የሚቃወመዉ ሕዝብ አደባባይ መዉጣት እንደጀመረ የቤንጋዚ፥ የራስ ላኑፍ፥ የበርጋ፥ የቢን ጀዋድ፥ የዛዊያ እና የሌሎችም ከተሞች አስተዳዳሪዎች፥ ፖሊሶች፥ ወታደሮች አልፎ ተርፎ ሚንስትሮችና ዲፕሎማቶች ሠልፋቸዉን ከአመፀዉ ሕዝብ ጋር ማሳማራቸዉ አርባ-ሁለት ዘመን ለዘለቀዉ ለቃዛፊ ሥርዓት የፍፃሜዉ መጀመሪያ አይነት ነበር።

ሕዝባዊ ሠላማዊ አመፅ ወደ ጠመንጃ ዉጊያ ከተቀየረ ወዲሕ ግን ሕዝባዊዉ ድል በመጀመሪያ ፍጥነቱ አልቀጠለም።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊም የአመፁባቸዉን ሐይላት በሐል ከመደፍለቅ አላመነቱም።ታንክ፥ መድፍ፥ ተዋጊ ጄት፥ ሔሊኮብተር፥ የታጠቀዉ የቃዛፊ ታማኝ ጦር አማፂያኑ የሚቆጣጠሯቸዉን ከተሞች እያጠቃ ነዉ።

የቃዛፊ ታማኞች ትናንት ቢን ጃዋድ እና ዛዊያ የተባሉትን የነዳጅ ዘይት ጉርጓድና ማከማቻ ከተሞችን ከአማፂያኑ እጅ አስለቅቀዉ ተቆጣጥረዋል።አማፂያኑ የዛዊጃን ከተማ ለቀዉ ወደ ራስ ሐኑፍ ከማፈግፈጋቸዉ በፊት የቃዛፊ ታማኝ ጦር በከፈተዉ ጥቃት ቁጥሩ በዉል ያልታወቀ ሠላማዊ ሰዉ መገደሉን የከተማይቱ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

«ጭፍጨፋ ነዉ።አልሞ ተካሾች እየገደሉን ነዉ።ከተማይቱ ዉስጥ እየተዘዋወሩ ነዉ።»
ይላሉ ከዛዊያ ነዋሪዎች አንዱ።የቃዛፊ ታማኞች ራስ ላኑፍ የተሰኘችዉን ከተማ ለመያዝ በሰወስት ግንባር የከፈቱትን ጥቃት አማፂያኑ ማክሸፋቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና አማፂያኑ እና አንዳድ የከተማይቱ ነዋሪዎች እንዳስታወቁት የጋዛፊ ታማኝ ጦር የራስ ላንፉን መዳራሻ ዛሬ በጄት ደብድቧል።በድብደባዉ ሥለደረሰዉ ጉዳት እስካሁን በትክክል የታወቀ ነገር የለም።

NO FLASH Libyen Kämpfe
አማፂያኑ-በርጋምስል picture alliance/dpa

አንድ የአማፂዉ ሐይላት ቃል አቀባይ እንዳለዉ ኤስ ሲዳር በተባለችዉ ከተማ ዛሬ ጠዋት ከተጣለዉ የአዉሮፕላን ቦምብ ቢያንስ አንዱ የአንድ ቤተ-ሰብ አባላትን አሳፍራ የነበረች የቤት መኪናን አንድዷል።በዉጊያዉ ምክንያት የበርጋና የራስ-ላኑፍ ነዳጅ ወደቦች ነዳጅ መላክ አቁመዋል።

የቃዛፊ ታማኞችን የአየር ድብደባ ለማስቆም አለም አቀፍ የበረራ ማዕቀብ እንዲጣል የቀረበዉ ሐሳብ ሐያሉን አለም እስካሁን አላግባባም።የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ዋና ፀሐፊ አንድረስ ፎግሕ ራስሙስን፣«እስከመቼ»-ይላሉ።«ቃዛፊና ሥርዓታቸዉ የራሳቸዉን ሕዝብ ሆን ብለዉ መግደላቸዉን ከቀጠሉ አለም አቀፉ ማሕበረሰብና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እጃቸዉን አጣጥፈዉ የሚቀመጡበት ምክንያት አይታየኝም።»

የዩናይትድ ስቴስ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ጆን ኬሪ በሊቢያ ላይ የበረራ ማዕቀብ ለመጣል ከወዳጆቻችን ጋር መመካር አለብን ይላሉ።«ከወዳጆቻችን ጋር በመሆን የበረራ ማዕቀብ ለመጣል መዘጋጀት አለብን።»

ይሁንና በፕሬዝዳት ባራክ ኦማባማ መስተዳድር ከፍተኛ ተሰሚነት አላቸዉ የሚባሉትን የሴናተር ኬሪን ሐሳብ የኦባማ ልዩ አማካሪ ቢል ዴለይ አይቀበሉትም።«ሥለ በረራ እግዳ የሚያወሩት ሰዎች ሥለምን እንደሚያወሩ በትክክል አያዉቁትም።»ያም ሆኖ ዛሬ ሩሲያን የሚጎበኙት ምክትል ፕሬዝዳት ጆ ባይደን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በሊቢያ ላይ የበረራ እገዳ እንዲጥል የሩሲያ መሪዎችን ድጋፍ ሳይጠይቁ እንደማይቀር ተዘግቧል።ሩሲያ ማዕቀብ መጣሉን አትደግፈዉም።

Libyen Kinder spielen auf Panzer in Bengasi Flash-Galerie
የቤንጋዚ ልጆች ዕቃ፤ዕቃ በታንክምስል dapd

ከሊቢያ ደግሞ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ከአማፂያኑ ጋር ለመደራደር መጠየቃቸዉን የሊቢያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ የተቃዋሚዎች ስብስብ አስታዉቋል።አንድ የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ የቃዛፊ መልዕክተኞች አቀረቡትን ያሉትን የድርድር ሐሳብ ምክር ቤቱ አልተቀበለዉም።ገለልተኛ ወገኖች ግን ጥያቄዉ መቅረቡን አላረጋገጡም።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ