1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊዝበኑ ጉባኤና የሙጋቤ አወዛጋቢነት

ዓርብ፣ ኅዳር 27 2000

ህዳር ሀያ ሰባት በፓርቹጋል ሊዝበን በሚካሄደው የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ ላይ ላለመገኘት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር መወሰናቸው እንዳናደዳቸው የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሌቪ ምዋናዋሳ ከአንጌላ ሜርክል ጋር በተገናኙበት ወቅት ገለፁ።

https://p.dw.com/p/E87O
አንጌላ ሜርክል
አንጌላ ሜርክልምስል AP

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርዶን ብራውን፤በፖርቹጋል ሊካሄድ በታቀደው የአውሮጳ ኅብረትና የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ላይ ላለመገኘት መወሰናቸውን አስመልክቶ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በእርግጥ ግልፅ ትችት አላቀረቡም።ይልቁንስ የዚምቧቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በስብሰባው ላይ መገኘታቸው ከሠብአዊ መብት አያያዛቸው አንፃር ለብዙዎች ራስ ምታት እንደሚሆን አውቃለሁ፤ሆኖም ግን ስብሰባው ከምንም በላይ ይጠቅመናል ብለዋል።

የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ሌቪ ምዋናዋሳ በፖርቹጋሉ ጉባኤ ላይ የዚምቧቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያላቸውን ድጋፍ ሲያሳዩ ቆይተዋል። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርዶን ብራውን በስብሰባው ላይ ላለመገኘት መዛታቸውንም ተችተዋል።ምዋናዋሳ ምንም እንኳን የሙጋቤን ደካማ የሠብዓዊ መብት አያያዝ እንደሚያውቁ ቢገልፁም፤ሙጋቤ በሌሉበት ግን ስለአጠቃላዩ የአፍሪቃ ጉዳይ ማንሳት ይከብዳል ብለዋል።

እ.ኤ.አ. በሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዓ.ም ዛምቢያ የምጣኔ ሀብት አመራሯን ባልተጠበቀ ሁኔታ ገበያን ወዳማከለ ስልት መቀየሯ ያታወቃል።በሂደቱ የተከሰተውንም የተለያዩ ችግርች ለመቅረፍ የዛምቢያ መንግስት ሠፋፊ የግል ይዞታዎችን በመፍቀድ የመንግስት ድጎማን ለመቀነስ ሞክሯል።ይሁንና ግን የዛምቢያውያን ገቢ ከዕለት ዕለት እያሽቆለቆለ ነው የመጣው። ስልሳ ከመቶ የሚሆነው ነዋሪ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ የለት ገቢ ነው የሚተዳደረው።አብዛኛው ደሀ የሚኖረው በገጠር ሲሆን፤የዛምቢያ ትላልቅ ከተሞች ግን የተሻሉ ናቸው።

ከዓለም ባንክና ከዩናይትድ ስቴትስ በተጨማሪ ጀርመን የዛምቢያ ከፍተኛዋ ለጋሽ አገር መሆኗ ይታወቃል።በርሊን ያለው መንግስት በተለይ ለመልካም አስተዳደር፤ሙስናን ለመዋጋት እና የውሀ አስተዳደር ፕሮጅቶችን ለማሻሻል ለዛምቢያ አስፈላጊውን ገንዘብ መድቧል።

እ:ኤ.አ. በሁለት ሺህ ስድስትና በሁለት ሺህ ሰባት ብቻ ጀርመን ለዛምቢያ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ወደ አርባ ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች። በተጨማሪም ከአንድ ቢሊዮን ዩሮ በላይ የሚገመት የዛምቢያን ዕዳ ጀርመን በቀጥታ ሠርዛላታለች። ጀርመንና ዛምቢያ በሁለቱም ወገን ተመጣጣኝ የሆነ የጥሬ ዕቃዎችና ሌሎች ውጤቶች ገቢና ወጪን አስመልክቶ በዓመት የሀያ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ንግድ ያካሂዳሉ።ጀርመንና ዛምቢያ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር በበርሊን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።