1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

'የልማታዊው መንግስት' ቅርቃር

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2008

በኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ውጥረት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት በአዲሱ ዓመት የአወቃቀር ለውጥ እንደሚያደርግ ፍንጭ ሰጥቷል። የጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ፓርቲም ይሁን መንግስት የገጠመውን ቀውስ በዘላቂነት መፍትሔ ለማበጀቱ ግን ተቺዎቹ ጥርጣሬ አላቸው።

https://p.dw.com/p/1Jt9g
Äthiopien vor der Wahl Wahlplakat in Addis Abeba
ምስል picture-alliance/dpa/C. Frentzen

የልማታዊ መንግስት ቅርቃር

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ማግሥት ከሩብ ምዕተ-ዓመት በላይ በሥልጣን የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ «የልማትና የዴሞክራሲ ጮራ» ፈንጥቋል፤«የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና» አግኝተዋል፤ «የህዝብ ተጠቃሚነት» ተረጋግጧል ብሏል። እውነታው ግን ከመግለጫው እጅጉን የራቀ ይመስላል። በትናንትናው ዕለት እንኳ የአማራ ክልላዊ መንግስት የአገሪቱ ጦር እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መተላለፉን አስታውቋል።በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ተቃውሞዎች ለጊዜው ጋብ ያሉ ቢመስልም በመጪዎቹ ቀናት ግብይትን የማቆም የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ በማሕበራዊ ድረ-ገጾች ጥሪ ተበትኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ «ሁላችንም እንደገና በጥልቀት መታደስ ይገባናል» ሲሉ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ 'ልማታዊ መንግስት' ለገጠመው የከረረ ተቃውሞ ተገቢ ምላሽ በመስጠት መፍትሔ ለማበጀቱ ግን በርካቶች ጥያቄ አላቸው።
Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson
ዶ/ር አወል አሎ የህግ ምሁር ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በለንደን የኤኮኖሚክስ ት/ቤት (London School of Economics) የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ናቸው። ዶ/ር አወል አሁን በኢትዮጵያ በተቀሰቀሱት ተቃውሞዎች የሚነሱ ጥያቄዎች በቀላሉ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተብለው የሚለዩ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።
በአፍሪቃ ፈጣን ኤኮኖሚያዊ እድገት አስመዝግባለች የሚባልላት ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አልተሳካላትም። የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ሲቪክ ማህበራት እና መገናኛ ብዙኃን ተገፍተው የበይ ተመልካች ከሆኑ ሰነባበቱ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የኢትዮጵያ መንግስት ተቺዎቹን ያለ በቂ ምክንያት ያስራል፤ ይከሰላል እያሉ ይተቻሉ። ዶ/ር አወል በኢትዮጵያ የመንግስት አወቃቀርም ይሁን በገዢው ፓርቲ ያለው ውክልና ፍትሐዊ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። በእሳቸው አባባል የኢትዮጵያ መንግስት የሚያቀነቅነው ልማታዊነት ይህንንው እውነታ ለመሸፈን የቀረበ አጀንዳ ነው።
የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት ካካሄደው ጉባዔ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በሰጡት መግለጫ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ መፍጠር የሚችሉ እቅዶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት እንዲህ አይነት ቃል ሲገባ የመጀመሪያው አይደለም። ከቀጣናው አገራት አኳያ የተሻለ መረጋጋት የነበራት ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እና ብድር የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፤ መንገዶች የባቡር አገልግሎት ብትገነባም በርካታ ኤኮኖሚያዊ ችግሮች አሉባቸው። ዶ/ር አወል ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት ቢኖርም በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አላመጣም ሲሉ ይናገራሉ።
Brasilien Olympische Spiele Rio 2016 21 08 - Marathon Feyisa Lilesa
ምስል Getty Images/AFP/O. Morin
የምሥራቅ እስያ አገራት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ኤኮኖሚያቸውን ለማሸጋገር 'የልማታዊ መንግስት' ሞዴልን መከተላቸው ይነገራል። ኢትዮጵያ ይህንኑ ስልት ስትከተል ከምሥራቅ እስያ አገራት ጋር የሚያመሳስላትም የሚለያያትም ጉዳዮች መኖራቸውን በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሙለታ ይርጋ ለደቡብ አፍሪቃው ስቴለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ሊደርሺፕ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሑፍ የምሥራቅ እስያ አገራት 'የልማታዊ መንግስትን' ሞዴል በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሲከተሉ ኢትዮጵያ በአንፃሩ አምባገናዊነትን መምረጧን ገልጠዋል። ዶ/ር አወል አሎ ኢትዮጵያ የምትከተለው ይኸው 'የልማታዊ መንግስት ሞዴል' አሁን ከማይመለስበት የውድቀት ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝ የተወካዮች ምክር ቤት በመጪው አዲስ ዓመት ሥራውን በይፋ ሲጀመር በመንግስታቸው ውስጥ የአወቃቀር ለውጥ እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተዋል። ምን አልባትም ሹም ሽር ሊካሄድ እንደሚችል ይጠበቃል። የገዢው ፓርቲ እርምጃዎች አገሪቱ የገጠማትን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት ስለመቻሉ ግን የሚታወቅ ነገር የለም።
እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ