1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልማት ዕርዳታ- እና ኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጥር 4 2008

የኢኮኖሚያዊ ትብብርና እና ልማት ድርጅት ባለፈው ኅዳር ይፋ ባደረገው ዘገባ ዩናይትድ ስቴትስ፤ብሪታንያ፤ ጀርመን እና የልማት እገዛ ኮሚቴ አባል አገሮች 137.2 ቢሊዮን ዶላር የተመዘገበ የልማት እገዛ ማቅረባቸውን አትቷል። ኢትዮጵያ የልማት እገዛውን በመቀበል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ተሰልፋለች።

https://p.dw.com/p/1Hcf4
Äthiopien Textilindustrie Fabrik Näherin
ምስል Jeroen van Loon

የልማት እርዳታና ኢትዮጵያ

በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. የበለጸጉ አገራት 137.2 ቢሊዮን ዶላር የተመዘገበ የልማት እገዛ (Official development assistance) መስጠታቸውን የኢኮኖሚያዊ ትብብርና እና ልማት ድርጅት (OECD) አስታውቋል። ይህ ከቀደመው 2013 ዓ.ም በ2 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው ነው። በድርቅና ረሐብ ተለይታ የምትታወቀው ኢትዮጵያም የባለጠጎቹ ዳረጎት ከማይለያቸው አገራት መካከል አንዷ ናት። በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያገኘችው የተመዘገበ የልማት እገዛ መጠን 3.6 ቢሊዮን ዶላር ነበር። የኢኮኖሚያዊ ትብብርና እና ልማት ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. ለደሐ አገሮች የተሰጠው የልማት እርዳታ ከምንጊዜውም ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል። ያስሚን አህመድ በየኢኮኖሚያዊ ትብብርና እና ልማት ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ ሰብሳቢ ቡድን ዋና ኃላፊ ናቸው።
«ከፍተኛ የእርዳታ ተቀባይ አገሮች አፍጋኒስታን፤ቪየትናም እና ሶርያ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተቀብለዋል። በመቀጠል እያንዳንዳቸው 3.6 ቢሊዮን ዶላር የተቀበሉት ፓኪስታንና ኢትዮጵያ ይገኛሉ።ኢትዮጵያ በተመለከተ ከልማት እገዛ ኮሚቴ አባላት ብቻ ሳይሆን አባል ካልሆኑ አገሮች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎችን ሰብስበናል። በዚህ መሰረት በ2013/14 በአማካኝ ለኢትዮጵያ የታወቀ የልማት እገዛ በማቅረብ ቀዳሚው የዓለም ባንክ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ፤ብሪታንያ፤የአፍሪቃ የልማት ፈንድ እና የአውሮጳ ህብረት ተቋማት ተከታዩን ደረጃ ይይዛሉ።»

Utopie Äthiopien
ምስል Gino Kleisen

ባለፈው ዓመት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች በሚያደርገው ድጋፍ የራሱን ህግጋት እና መርሆዎች በተደጋጋሚ ጥሷል ተብሎ መተቸቱ አይዘነጋም። ወቀሳው የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በጋምቤላ ክልል ለሚያደርገው የግዳጅ የሰፈራ መርሐ-ግብር ሲጠቀምበት ቆይቷል የሚል ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ተቺዎች በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመጥቀስ እንደ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ያሉ አገሮች የሚሰጡትን የልማት እርዳታ አጠቃቀም እንዲፈትሹ ሲወተውቱ ይደመጣል። የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም ከዓለም የእርዳታ ተቀባዮች ተርታ በቀዳሚነት የተመዘገበችው ኢትዮጵያ የምትቀበለው ገንዘብ እየጨመረ ቢመጣም በግለሰብ ደረጃ ሲሰላ አነስተኛ ነው ባይ ናቸው።

ባለፈው ኅዳር ወር የ2014ን አጠቃላይ የልማት እርዳታ መጠን በሚያሳየው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተቀበለችው የተመዘገበ የልማት እገዛ ለተለያዩ ሥራዎች የዋለ መሆኑን ያትታል። ቀዳሚው ግን የመሰረተ ልማት ስራዎች መሆናቸውን ያስሚን አህመድ ይናገራሉ።
«ያቀረቡት እርዳታ የተለያየ መልክ አለው። እኛም የእርዳታ ገንዘቡ በተመደበባቸው ዘርፎች መረጃዎችን ሰብስበናል። ለምሳሌ በ2014 የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግስት እና የሲቪክ ማህበረሰብ የማህበራዊ ዘርፍ እና የውሃ አቅርቦት የሚሆን ገንዘብ አቅርቧል። ለትራንስፖርት፤ ግብርና፤የደን እና የአሳ ሐብት ልማት፤ለኢንደስትሪ እና የማዕድን ዘርፉ የሚሆን የልማት ገንዘብ የተሰጠባቸው ቀዳሚ ዘርፎች ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ትኩረት በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። በዚህም ለስነ-ህዝብ ፕሮግራሞች እና የሰብዓዊ እርዳታ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኙ ናቸው። ብሪታንያ የትምህርት እና የጤና ዘርፉን በመደገፍ ላይ ትኩረት አድርጋለች።»

Äthiopien äthiopische Oppositionelle
ምስል DW

ለኢትዮጵያ መንግስት የተመዘገበ የልማት እገዛ ከሚያቀርቡት መካከል አንዱ የሆነው የአፍሪቃ የልማት ፈንድ በኢኮኖሚያዊ መሰረተ-ልማት ዘርፉ ውስጥ የትራንስፖርት፤እና የሸቀጣቀጥ ንግድ ዘርፉን መደገፉን ያስሚን አህመድ ተናግረዋል። የአውሮጳ ህብረት በበኩሉ ማህበራዊ መሰረተ-ልማት እና የሰብዓዊ እርዳታ ላይ ትኩረት አድርጓል።

ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚመጣ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት አቅዳ ነበር። ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰው የመዋዕለ ንዋይ መጠን ለረጅም አመታት ውስን ነበር። በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ከሰባት አመታት በፊት አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው የገንዘብ መጠን 108.5 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በየዓመቱ በእጥፍ እድገት አሳይቷል። ህንድ እና ቻይናን ከመሳሰሉ አገራት ርካሽ የሰው ጉልበት፤የኤሌክትሪክ ኃይል ፍለጋ ፋብሪካዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያዘዋወሩት ኩባንያዎች ለእድገቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ለውጭ ባለ ወረቶች አበረታች ፖሊሲዎች ማዘጋጀቱም በተጨማሪነት ይጠቀሳል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት የምታገኘው ገቢ የተመዘገበ የልማት እገዛን መተካት ይችላል? ያስሚን አህመድ
«ያለፉትን አስራ አምስት አመታት ተሞክሮ ስንመለከት የተመዘገበ የልማት እገዛ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገሮች ቋሚ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ከውጭ አገራት የሚገኘው ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ያልተረጋጋ እንዲሁም በገበያ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለዋወጥ ነው። ስለዚህ ከውጭ አገራት የሚገኘው ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት የተመዘገበ የልማት እገዛን ይተካል ብዬ አላስብም። እንዲያውም ለተመዘገበ የልማት እገዛ ደጋፊ ተደርጎ ነው የሚወሰደው።»ሲሉ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም ከኢትዮጵያ አመታዊ በጀት እስከ 40 በመቶው ከተመዘገበ የልማት እገዛ የሚገኝ እንደነበር ያስታውሳሉ።ኢኮኖሚው ለረጅም አመታት በልማት እርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱን የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው በእርዳታ የሚገኝ ገንዘብን ለታቀደለት ዓላማ በመጠቀም የተሻለ አፈጻጸም እንዳላት ያምናሉ።

Utopie Äthiopien
ምስል Gino Kleisen

የተመዘገበ የልማት እገዛ የሚቀበሉ ኢትዮጵያን መሰል አገሮች በህገ-ወጥ የገንዘብ ሽግግር እና ሙስና ችግሮች አሉባቸው የሚሉት ያስሚን አህመድ በኅዳር ወር ይፋ ባደረጉት ጥናት የችግሮቹን ጫና ለመፈተሽ መቸገራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ችግሮቹ በተመዘገበ የልማት እገዛ አጠቃቀም ላይ ጫና ቢኖራቸውም የኢኮኖሚያዊ ትብብርና እና ልማት ድርጅት እና የልማት አጋሮች ሙስና እና ህገ-ወጥ የገንዘብ ሽግግርን ለመቆጣጠር ተግባራዊ ያደረጉት አሰራር ለጊዜው አለመኖሩን ያስሚን አህመድ ተናግረዋል።

ሒሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ