1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልማት ዕርዳታ ያላግባብ መባከን፤ የዓለም ንግድ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 1998

ለታዳጊ አገሮች በያመቱ ከሚቀርበው ዓለምአቀፍ የልማት ዕርዳታ ሩቡ፤ ማለት ሃያ ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ለድሃው ሕዝብ አይደርስም። ያላግባብ ነው የሚባክነው። ላጋሽ አገሮች ቴክኒካዊ ዕርዳታ ለሚሉት ተግባር ራሳቸው ይገለገሉበታል። ይህን በቅርቡ ያመለከተው Action Aid International የተሰኘው ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ያቀረበው አዲስ የጥናት ውጤት ነው።

https://p.dw.com/p/E0de
የዓለም ንግድ ድርጅት አስተዳዳሪ ፓስካል ላሚይ
የዓለም ንግድ ድርጅት አስተዳዳሪ ፓስካል ላሚይምስል AP

ቴክኒካዊ ዕርዳታ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ምርምርን፣ ሥልጠናንና ደሞዝ በገፍ የሚከፈላቸው አማካሪዎች የሚሰጡትን አገልግሎት ነው። በ 2004 ዓ.ም. ዳታዎች ላይ ተመሥርቶ የቀረበው ዘገባ እንደሚያመለክተው በልማት አማካሪነት ለሚሰየሙት አማካሪዎች በያመቱ የሚፈሰው ገንዘብ 200 ሺህ ዶላር ገደማ ይጠጋል። በልጆቻቸው የሚታሰብላቸው አበልና የትምሕርት ቤት ወጪ ራሱ የዚህን ሲሦ የሚያህል ነው። የአገር ውስጥ አማካሪዎችን እጅግ ዝቅ ባለ ወጪ በቀላሉ በተግባር ማሰማራቱ ብዙም ባላዳገተ ነበር።

የ Action Aid International የደቡብ አፍሪቃ ዘርፍ አስተዳዳሪ ካሮሊን ሣንዴ ሙኩሊራ እንዳስረዱት የውጭ አማካሪዎች በየቀኑ እስከ ሺህ ዶላር የሚደርስ ክፍያ ያገኛሉ። ይህ ደግሞ በታዳጊው ዓለም በሚገኙ ሙያተኞችና ሕዝብ ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱ አልቀረም። ለምሳሌ በጋና የትምሕርት አገልግሎት መምሪያ ተቋም አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በወር የሚያገኘው ደሞዝ 300 ዶላር ገደማ ቢደርስ ነው። ይህን ገንዘብ መጠነኛ ልምድ ያለው ጋናዊ አማካሪ በአንድ ቀን፤ ወይም የውጭ አማካሪ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ያገኙታል።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ በከፍተኛ ክፍያ የሚቀጠሩ የውጭ አማካሪዎች የረባ ጥቅም ሊሰጡ አለመቻላቸው ሲታሰብ ነው። Action Aid በዘገባው ስኬቱ ውስን ሆኖ የተገኘውን የታንዛኒያን የባጎሞዮ የመስኖ ፕሮዤ ጠቅሷል። ገበሬዎች በዘጠናኛዎቹ ዓመታት በጃፓን ዕርዳታ የውሃ ማመንጫ ፑምፓዎችን አጠቃቀም ቢማሩም በናፍታ ዋጋ መናርና መሣሪያዎቹን በሚጠግኑ የአገር ሙያተኞች እጥረት የተነሣ የተፈለገውን ውጤት ዕውን ለማድረግ ሳይችል ቀርቷል።

ቴክኒካዊው ዕርዳታ ከዚህ ባሻገርም የራስ ተጽዕኖን ለማጠንከር መሣሪያ ሆኖ ነው የሚገኘው። ለጋሾቹ አገሮች ቴክኒካዊ ዕርዳታቸውን የታዳጊ ሃገራት ፖሊሲዎችን ለመቆጣጠር ወይም ራሳችው የሚፈልጉትን ለውጥ ለመቅረጽ ይጠቀሙበታል። ራሳቸው የሚያቀርቧቸው አማካሪዎች የታዳጊ አገሮች መንግሥታት ብሄራዊ የድህነት ቅነሣ ስልቶችን በሚነድፉበት ጊዜ በቀጥታ እስከመሳተፍ የሚደርሱ ናቸው።

ከመጠን በላይ ውድ የሆነ ወይም ፍቱንነት የጎደለው ቴክኒካዊ ዕርዳታ የድሆች አገሮችን ሁኔታ ሊያሻሽል አይችልም፤ የይስሙላ ዕርዳታን ያህል ነው። የ Action Aid ዘገባ ዕውነተኛ ዕርዳታን ወደ አስመሳይ ዕርዳታ የሚለውጡ ሌሎች ሂደቶችንም ጠቁሟል። ይህ የዕዳ ስረዛን ራሱን የቻለ ዕርዳታ አድርጎ የመመልከቱን ዘይቤም ይጠቀልላል። ዕርዳታው ለጋሽ አገሮች ለሚያቀርቡት ምርትና ለሚሰጡት አገልግሎት እንዲውል መጠየቁ ራሱ ያለ ጉዳይ ነው።

የብሪታኒያ ዓለምአቀፍ የልማት ተቋም በ 2005 እና በ 2006 መካከል ከሰጣቸው የልማት ኮንትራቶች 80 በመቶውን የሸለመው አገሪቱ ውስጥ ተቀማጭ ለሆኑ ኩብንያዎች ነበር። እነዚሁ ኩባንያዎች ገንዘቡ ለልማት ተግባር ፈሷል ሊሉ ይችላሉ። ይሁንና ሃቁ ገንዘቡ እዚያው ብሪታኒያ ውስጥ መቅረቱ ነው። አንዳንድ ሃብታም መንግሥታት ዛሬ ከስደተኞች ጉዳይ በተያያዘ በአገር ውስጥ የሚያወጡትን ወጪ ዕርዳታ አድርገው መቁጠርም ይዘዋል። በተለይም በዚህ ረገድ የሚብሱት ስዊትዘርላንድና አውስትሪያ ናቸው። ከዕርዳታ በጀታችው 15 በመቶውን የሚያወጡት በውስጣቸው የሚገኙ ስደተኞችን ወጪ ለመሸፈን ነው።

በአጠቃላይ ከመላው የልማት ዕርዳታ ገሚሱ በዚህ መልክ ግልጋሎት ላይ የሚውል የተብዬ ዕርዳታ መሆኑ ይገመታል። ቴክኒካዊው ዕርዳታ ፍቱን አለመሆኑ በለጋሹ መንግሥታት ዘንድ ዛሬ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ሆኖም ሃራሬ ላይ ተቀማጭ የሆነው የአፍሪቃ የዕዳና ልማት መድረክ እንደሚለው ለድሆች አገሮች የሚፈልጉትን ዕርዳታ ለማግኘት መደራደሩ ቀላል ነገር አይደለም። ምርጫው ዝም ብሎ በመቀበልና በመተው መካከል ነው። ይወሰድ ከተባለ ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ አይሆንም። ቢተው ደግሞ ባዶ መቅረቱ ግድ ይሆናል። አስቸጋሪ ሆኔታ ነው።

Action Aid International ታዳጊ አገሮች የሚፈልጉትን የልማት ዕርዳታ ዓይነት ራሳቸው እንዲመርጡ የሚያበረታቱ በርካታ የመፍትሄ ሃሣቦችን ያቀርባል። በለጋሽ መንግሥታት አቅጣጫ የሚሰነዝረው ጥሪም በተቻለ መጠን የውጩን ሣይሆን የታዳጊ አገሮችን ምንጮች ተጠቀሙ የሚለውን ማሳሰቢያ ይጠቀልላል። የዘገባው አቀናባሪ ሮሚሊይ ግሪንሂል እንዳሉት ዕርዳታው የምዕራባውያን አማካሪዎች ኪስ መሙያ መሆን የለበትም። መጥቀም ያለበት በታዳጊው ዓለም ያሉትን ድሆች ነው።

የሆነው ሆኖ አብዛኛው የዕርዳታ ተግባር በለጋሾቹ አገሮች ቁጥጥር መራመዱን ቀጥሏል። መንግሥታቱ ከራሳቸው ብሄራዊ ኩባንያዎች ጋር ያስተሳስሩታል። በዚያ ላይ አቀነባበሩ ፍሬ ቢስ፤ የተዋቀረውም የውጭ አማካሪዎችን አስፈላጊነትና የተቀባዮቹን አላዋቂነት መሠረተ-ዓላማው አድርጎ ነው። በዚህ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድህነትን ለመቀነስ የያዘውን የሚሌኒየም ዕቅድ በተለይ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ዕውን ማድረጉ ይበልጥ የሚከብድ ነው የሚሆነው።

ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን እንሻገርና መሰናክል ገጥሞት የቆየውን የዓለም ንግድ ድርጅትን የዶሃ ድርድር ዙር መልሶ በማንቀሳቀስ ከአንድ ስምምነት እንዲደረስ በቅርቡ በሩሢያ ሣንት-ፔተርስቡርግ ላይ ተካሂዶ በነበረው የ G-8 ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ጉባዔ ሂደት ያልተባለ ነገር አልነበረም። ድህነትን ለመታገል ቆርጦ መነሣት ግድ ነው፤ ድርድሩን የግድ ከግቡ ማድረስ አለብን፤ ከያቅጣጫው የተሰማው መግለጫ ነበር። ሆኖም ችግሩ ዝርዝሩ ላይ ነው እንደሚባለው ባለፈው ሰኞ በንግድ ድርጅቱ መቀመጫ በጀኔቫ በሚኒስትሮች ደረጃ የተካሄደው ንግግር መክሸፍ ወይም ቢቀር ላልታወቀ ጊዜ መቋረጡ ግድ ሆኖበታል።
ለአዲስ ጅማሮ ወራት ወይም ዓመታት ማስፈለጋቸው አይቀርም የሚሉ ወገኖች አልታጡም። የዶሃው የድርድር ዙር ምናልባት ለአንዴና ለሁልጊዜ በከንቱ ተሰናክሎ መቅረቱ ይሆን? ከጀኔቫው ድርድር በኋላ ጎልቶ የሚታየው ተሳታፊዎቹ ወገኖች እርስበርስ አንዱ ሌላውን ወገን ጥፋተኛ አድርገው መውቀስ የያዙበት ሂደት ነው። የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን ለምሳሌ G-6 የሚባሉት ዋና ዋና የዓለም ንግድ ድርጅት መንግሥታት ንግግር እንዳበቃ እንደተናገሩት ሁሉም በአስታራቂ ሃሣብ አቅጣጫ ተንቀሳቅሰዋል፤ የቀረችው አሜሪካ ብቻ ናት።
ስድሥቱ ወገኖች የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ብራዚልና ሕንድ ናቸው። ማንደልሶን አሜሪካን የወቀሱት ለብሄራዊ የእርሻ ዘርፏ የምትሰጠውን ድጎማ ለመቁረጥ አንዳች ዕርምጃ ፈቀቅ አላለችም በማለት ነው። በርሳቸው አባባል የዋሺንግተን ልዑካን ቡድንም ቢሆን የሌሎቹን ተሳታፊዎች ያህል በጎ ፈቃድ አልታየበትም። ይህ ሁሉ ሆኖም የአውሮፓው ሕብረት ኮሜሣር የዶሃው ዙር መክሸፉ ገና ጨርሶ አልለየለትም ባይ ናቸው። ይሁንና በሌላ በኩል የድርድሩ መቋረጥ የዓለም ንግድ ድርጅትን የወደፊት ዕርምጃ አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውም አልቀረም።

የአሜሪካ የንግድ ነገረ ፈጅ ሱዛን ሽዋብ በበኩላቸው ዋሺንግተን በዶሃው ድርድር ጠንካራና ሚዛናዊ ውጤት ማስገኘቱን ሃላፊነቷ አድርጋ ትቀጥላለች ሲሉ በፊናቸው የአውሮፓ ሕብረት ወደ ገበዮቹ በሚገቡት የእርሻ ምርቶች ላይ የጣለውን ቀረጥ ዝቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። መወቃቀስ የያዙት እርግጥ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ብቻ አይደሉም። ታዳጊዎቹ አገሮችም ለዶሃው የድርድር ዙር መሰናከል በጠቅላላው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን መንግሥታት ተጠያቂ ማድረግ ቀጥለዋል።
ኮሎኝ ከተማ ላይ ተቀማጭ የሆነው የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዩርገን ማተስ የአውሮፓ ሕብረት አሜሪካን ተጠያቂ ማድረጉን ተገቢ አድርገው አላገኙትም። አሜሪካ ብቻ ናት ጥፋተኛዋ ማለቱ ቀላል ነው። ግን ጥፋቱ የሁሉም የዓለም ንግድ ተጓዳኞች ነው። አሜሪካ በከፍተኛ ግብ ላይ ነው የምታልመው። የአውሮፓ ሕብረትና ራመድ ያሉት ታዳጊ አገሮች በአንጻሩ የሚፈልጉት ውሱን የሆነ የንግድ ስምምነትን ነው” ብለዋል።

የጄኔቫው ድርድር ባለፈው ሰኞ ቀትር ላይ ሲቋረጥ ለፊታችን ሰንበት ታስቦ የነበረው ተጨማሪ ንግግርም መሰረዙ ግድ ሆኖበታል። ታሳታፊዎቹ ወገኖች በዚህ በሰንበቱ ንግግር ለሣምንታት ተሰናክሎ የቂ ቆየውን የዓለም ንግድ ድርድር እንደገና ለማንቀሳቀስ ውጥን ነበራቸው። ዓበይቱ የድርድሩ ነጥቦች ሁለት ናቸው በአንድ በኩል በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃብታም መንግሥታት ታዳጊዎቹና ከዚያም ራመድ ያሉት አገሮች ገበዮቻቸውን ይበልጥ ለውጭ የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲከፍቱ ይጠይቃሉ።
ታዳጊዎቹም በአንጻሩ ሃብታሞቹ አገሮች ለንግድ ፍትሃዊነት መሰናክል የሆነውን ብሄራዊ የእርሻ ድጎማ ማንሣት ወይም ቢቀር መቀነስ አለባቸው ባዮች ናቸው። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት መንግሥታት በቅድሚያ ለታዳጊ አገሮች የራሳቸውን ገበዮች በሚገባ መክፈታቸውም ሌላው ቁልፍ ጥያቄ ነው። የዶሃው አጀንዳ እርግጥ በንግድ ጥያቄዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ድህነትንና ረሃብን ለመታገል፣ በጎ አስተዳደርን፣ የዓለም ጸጥታንና ማሕበራዊ ፍትህ የሰፈነበት የኤኮኖሚ ልማት ማስፈኑንም የሚጠቀልል ነው።

ከዚህ አንጻር የድርድሩ መክሸፍ ቀላል ሆኖ ሊታይ የሚችል አይሆንም። ድህነትን በግማሽ የመቀነሱን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ዕቅድም ሆነ በታዳጊው ዓለም ፍትሕና ልማትን የማራመዱን ጥረት ከንቱ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። እርግጥ የድርድሩ አለመሣካት ምክንያቶች የተወሳሰቡ ቢሆኑም በአጠቃላይ ለንግግሩ መክሸፍ ተጠያቂነቱ በሃብታሞቹ አገሮች ላይ ያመዝናል። የታዳጊ አገሮችን ገበሬዎች የፉክክር አቅም የሚያዳክመውን ብሄራዊ የእርሻ ድጎማቸውን ሲሆን በመተው ወይም ቢቀር በሚገባ በመቀነስ ፍትሃዊ የገበያ ውድድር እንዲኖር ለማድረግ በቂ ዕርምጃ አልወሰዱም። ቅን ፍላጎት መኖሩም ያጠያይቃል።
ልዩነቱ የበለጸጉት መንግሥታት ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚያራምዱት ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሥርዓትና በፍትሃዊ ተሃድሶ መካከል ነው። እርግጥ የኋለኛው የማይቀር ነገር ነው። ጊዜ መፍጀቱ ላይ ነው ችግሩ!