1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የልጅ ስደተኞች መበራከት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2008

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም እስከያዝነዉ የመጨረሻ ወር ድረስ ወደጀርመን 60 ሺህ የሚሆኑ ልጆች ስደተኞች ገብተዋል። ለአካለ መጠን ያልደረሱት ልጆች የመጡት ከተለያዩ ሃገራት ሲሆን ወላጅ ወይም መሪ አልተከተላቸዉም።

https://p.dw.com/p/1HRsf
Symbolbild Minderjährige Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler

[No title]

ኖህ ከማሊ አሊ ደግሞ ከሴኔጋል ነዉ የተሰደዱት። የ16ዓመቱ የማሊ ልጅ ከምዕራብ አፍሪቃ ወደአዉሮጳ ለመሻገር ስላደረገዉ አስቸጋሪ የስደት ጉዞ መተረኩ ከብዶታል። ፎቶ መነሳትም አልፈለገም። የሚያሳድድና የሚከታተለዉ እንዳለ ብጤ ፍርሃት ይታይበታል።

«ማሊ ዉስጥ ጦርነት ነበር። ቤታችን ዉስጥ ማንንም ማግኘት አልቻልኩም። በአንድ የጭነት መኪና ላይ ተሳፍሬ ከሌሎች ጋር ወደኒዠር ተጓዝን። እዚያ አንድ ዓመት ያህል ቆየሁ። ከዚያ ወዲህ ቤተሰቦቼ ጋር መገናኘት አልቻልኩም።»

እዚያ በነበረበት ጊዜ ያፈራዉ አንድ ጓደኛዉ ሊቢያ ዉስጥ ሥራ ማግኘት እንደሚቻል ነገረዉና ወደዚያ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተዉ ለአንድ ዓመት መኪና ሲያጥቡ ቆዩ። የነኖህ ሕገወጥ ኑሮ ተደረሰበት እና ላለመታሠር መሰደድ ግድ ሆነበት።

«በእዉነቱ በጣም አደገኛ ነበር። በመጀመሪያ ለአንድ ሳምንት ያህል በረሃ ዉስጥ ቆየን። ዉኃም ሆነ ምግብ አልነበረንም።»

Symbolbild Flüchtlinge Sahara
የሰሃራ በረሃ ጉዞምስል imago/CHROMORANGE

ኖህ የነበረዉ አማራጭ ዳግም ወደሊቢያ መመለስ ነበር። በመካከሉ ደግሞ እግሩን ክፉኛ ታመመ እና መንቀሳቀስ ተሳነዉ፤ መሥራት አልቻለም፤ የከፋዉ ችግር መጣ። የወደፊት ህይወቴን ማስተካከል የምችለዉ በጀመርኩት መንገድ ስቀጥል ነዉ ብሎ ወሰነ። ግን ደግሞ ወዴት መሄድ እንዳለበት የሚያዉቀዉ ነገር አልነበረም። ጀርመን የሚታሰብ አልነበረም። ብቻ ካለበት አካባቢ መሄድ እንዳለበት ወስኗል። አንድ ግለሰብ በጀልባ ወደጣሊያን ማሻገር እንደሚችል ነገረዉ። በአደገኛዉ የጀልባ ጉዞ መሞት መኖሩን ኖህ ሰማ። ግን ደግሞ ለዚህ ደንታ አልነበረዉም፤

«ምንም ነገር ቢደርስብኝ ግድ አልነበረኝም። መሞትም አላሳሰበኝም። 82 ሰዎች ነበርን በጀልባዉ ላይ፤ ያ በራሱ አስቸጋሪ ነበር። ሁለት ሰዎች ዉኃዉ ላይ ሞተዋል። ሁላችን ፀጥ ብለን ነበር፤ ምንም የሚናገር አልነበረም። ምክንያቱም ሁሉም እኛም እንሞታለን ብሎ ያስብ ነበር።»

ኖህ ባህሩ ላይ አራት የሰቆቃ ቀናት አሳልፏል። በመጨረሻም በጣሊያን ዓሣ አጥማጆች ህይወቱ ተረፈና የብስ ረገጠ። ከጣሊያን ወደጀርመን የሚያደርሰዉ አንድ የባቡር ትኬት ተሰጠዉ። ኖህ ከመኖሪያ ቀየዉ ከወጣ ያገኛት ታላቅ ስጦታ ነበረች። የፀጥታ ኃይሎች ጣሊያን ዉስጥ ዳግም ካገኙት ወደመጣበት እንደሚመልሱት ያዉቃል። ባየርን ጀርመን ዉስጥ ሃኪሞች የተጎዳ እግሩን አከሙለት እና ላንደስበርግ ወደሚገኘዉ SOS የህጻናት መንደር ተወሰደ። SOS የሕጻናት መንደር ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ካከተመ በኋላ ወላጆቻቸዉን ላጡ የተቋቋመ የሕፃናት ማሳደጊያ ስፍራ ነዉ። ኖህ በዚህ ስፍራ በፍቅር የሚንከባከቡት አንጌሊካ ፎን አዉ እና ማሪያ ሽቶክን የመሰሉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች አግኝቷል። በርካታ የልጅ ስደተኞች ወደጀርመን መግባት ከጀመሩ ወዲህ ሁለቱ ሴቶች የሕጻናት መንደሩ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልገዉ ሳይጠይቁ አልቀሩም። ተጨማሪ አሳዳጊዎች፤ መምህራን እና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በዚህ ስፍራ ያስፈልጋሉ። ይህ ግን ኖህን አያሳስበዉም፤ ለእሱ ከብዙ ስቃይ በኋላ መጠነኛ መረጋጋት ያገኘበት ስፍራ ነዉ። ረዥም ሰዓት ግን እንቅልፍ መተኛት አልቻለም። እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ አንጌሊካ ፎን አዉ በሚገባ ያዉቁታል።

Griechenland Syrische Flüchtlinge machen ein Selfie auf der Insel Kos
የባህሩ ላይ እንግልትምስል Reuters/Y. Behrakis

«ልጆቹ ሌሊት ላይ ልጆቹ ከእንቅልፋቸዉ ባንነዉ ይጮሃሉ። ላብ ያሰጥማቸዋል፤ ያሳለፉት ሁሉ በህልማቸዉ እየመጣ እጨነቃሉ። እነሱን የሚንከባከቡት ሠራተኞች በተቻላቸዉ ሊያረጋጉዋቸዉ ይሞክራሉ።»

ሴኔጋላዊዉ የ17ዓመቱ ዓሊ ኖህ ጀርመንኛ ቋንቋ የሚማርበት የሙያ ማሰልጠና ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኗል። በዚህም ደስተኛ ይመስላል። በመማር የተሻለ የሥራ እና የወደፊት እድል እንደሚኖረዉ የሚያምነዉ ዓሊ ማንኛዉንም የሙያ ስልጠና ለመዉሰድ ዝግጁነቱን ይናገራል።

«ከትምህርት ቤት ስመለስ ረዥም ሰዓት እቀመጣለሁ። ያ ደግሞ አሰልቺ ነዉ። ሁሌም የሚሠራ ነገር ቢኖረኝ እወዳለሁ። ለምትንከባከበኝ እናት የምሠራዉ ነገር እንደምፈልግ ነግሬያታለሁ። የእጅ ሙያም ሆነ ሌላ ቢሆን ግድየልኝም።»

Symbolbild Minderjährige Flüchtlinge
እፎይታ በሕፃናት መንደርምስል picture-alliance/dpa/B. Reichert

ዓሊ እንደታዘበዉ ጀርመን ብዙ ሕጎች ያሉባት ሀገር ናት። ሕግ መኖሩ ሥርዓት እንዲከበር ያደርጋል ባይ ነዉ ዓሊ። ከ11ዓመት በፊት እናቱን በሞት የተነጠቀዉ ዓሊ የወንድሞቹ ድብደባ ከእንጀራ አባቱ እንዲለይ እንዳደረገዉ ይናገራል። ከቤቱ ጠፍቶ በማሊ በኩል ወደቡርኪና ፋሶ ከዚያም ወደአልጀሪያ ገብቷል። እሥር ቤትንም ገና በለጋ እድሜዉ ቀምሷል። አብረዉት የታሰሩ የሶማሊና ኤርትራ ዜጎች በእድሜ ትላልቅ ስለነበሩ እስር ቤት ሰብረዉ ሲጠፉ አብሮ አመለጠ። ከዚያም በጀልባ ወደጣሊያን። 11 ሰዓት በፈጀዉ የጀልባ ጉዞ የሚደርሰዉን ማንኛዉንም መጥፎ አደጋ ላለማየት ራሱን ቀብሮ እንዳሳለፈዉ ያስታዉሳል። ሙቀቱ ቢያሰቃየዉም ጀርመን ለመግባት በመቻሉ ራሱን ከዕድለኞች አንዱ አድርጓል። አሊ እንደኖህ ላንድስበርግ SOS የሕፃናት መንደር ገብቷል። በመንገዱ ላይ ብዙ መማሩን ይናገራል። ከምንም በላይ ትዕግስትን፤ ከዚያም ጥሩና እና መጥፎ ጓደኞች መኖራቸዉን አዉቋል። ከጥሩዎቹ አንዱ የማሊ ተወላጁ ኖህ ነዉ።

ቮልፍጋንግ ዲክ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ