1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሎንዶኑ የሊቢያ ጉባኤና አፍሪቃ ኅብረት

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 2003

ትናንት በሎንዶን ሊቢያን የተመለከተ ጉባኤ ሲካሄድ የአፍሪቃ ኅብረት አልተገኘም።

https://p.dw.com/p/RDzI
ምስል picture-alliance/landov

ከኅብረቱ ሌላ አንዳንድ የአረብ አገራትም ራሳቸዉን ከዚህ ለሊቢያ የፖለቲካ ሽግግር መንገድ ይቀይሳል ከተባለለት ጉባኤ ማራቃቸዉ ተዘግቧል። በሊቢያ ተኩስ ቆሞ በተቀናቃኞች መካከል የፖለቲካ ዉይይት እንዲካሄድ የጠየቀዉ የአፍሪቃ ኅብረት ከጉባኤዉ መራቅን ለምን መረጠ?

በሰሜን አፍሪቃና በአረብ አገራት የተቀጣጠለዉ ህዝባዊ አመፅ ሊቢያ ላይ ሲደርስ መልኩን የቀረ መስሏል። ሊቢያዉያን ከአራት አስርት ዓመታት በላይ የመንግስት ስልጣን ይዘዉ የከረሙት የሙአመር ኤል ጋዳፊን አስተዳደር የማስወገድ ህልማቸዉ በደም አፋሳሽ ግጭትና ጦርነት ተበርዟል። ለወቅቱ የሊቢያ ቀዉስ የፖለቲካ ሽግግር ለመቀየስ ያስችላል በሚል ፈረንሳይና ብሪታንያ በግምባር ቀደምትነት ያስተባበሩት ትናንት በሎንዶን የተካሄደዉ ጉባኤ የተጠበቀዉን ያህል ተሳታፊዎችን የሳበ አይመስልም። ሌላዉ ቀርቶ በሊቢያ ሰማይ ከበረራ ነፃ ቀጣና እንዲደነገግ ሲወተዉት የነበረዉ የአረብ ሊግ የበላይም እንዲሁ ዘገባዎች እንደሚሉት የተወከሉት በአምባሳደር ብቻ ነዉ።

NO FLASH Libyen Krieg Gaddafi NATO Konferenz London
የሎንዶኑ ጉባኤ ተሳታፊዎችምስል AP

የአፍሪቃ ኅብረት በጉባኤዉ እንዲሳተፍ ጥሪ እንደደረሰዉ የገለጹት የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ቃል አቀባይ ኑረዲን ሜዝኒ ኮሚሽነሩ ባይገኙም ኅብረቱ ሊቢያን በሚመለከት ያለዉን አቋሙን ማሳወቃቸዉን አስረድተዋል፤

«በመጀመሪያ የአፍሪቃ ኅብረት በሊቢያ ማንኛዉንም የዉጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አይደግፍም። ይህ አቋሙ ዘላቂ መሆኑን የሚያሳየዉም በሊቢያ ላይ የአየር ጥቃት በወሰነዉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተካሄደዉ በፓሪሱ ጉባኤም አልተካፈለም። በተጨማሪም የአፍሪቃ ኅብረት ለሊቢያ ቀዉስ ሰላማዊ መፍትሄን የሚደግፍ ሲሆን ኅብረቱ ችግሩን ለመፍታት ያሳለፈዉን ዉሳኔ በመመርኮዝ በሊቢያ ቡድኖች መካከል ዉይይት እንዲደረግ ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል።»

የደቡብ አፍሪቃ የጸጥታ ጉዳይ ጥናት ተቋም ኃላፊ ጃኪ ሲለርስም የአፍሪቃ ኅብረት የምዕራባዉያን ግፊት ባመዘነበት የሎንዶኑ የሊቢያ ጉዳይ ስብሰባ አለመሳተፉ በዲፕሎማሲዉ ጥረት ለመግፋት ካለዉ አቋም ነዉ ይላሉ፤

«እንደሚመስለኝ የአፍሪቃ ኅብረት በሊቢያ ጉዳይ ላይ የዲፕሎማሲ ጥረት ድጋፍ እንዲደረግ መንገድ እየፈለገ ነዉ። ከመነሻዉ የአፍሪቃ ኅብረት በሊቢያ ጉዳይ የዲፕሎማሲዉ ማዕከል አልነበረም፤ እንደሚታወቀዉ የአረብ ሊግ ነዉ እኔ ዘመቻ የምለዉን ርምጃ እንዲደግፍም እንዲያማክርም የተጠራዉ። ለዚህ ነዉ የአፍሪቃ ኅብረት የሊቢያን ጊዜያዊ ሁኔታ የሚለዉጥ የፖለቲካ ሂደት ለማምጣት በዲፕሎማሲዉ ጥረት የገፋበት።»

ሊቢያን በተመለከተ እጅግ የተከፋፈለ አቋም እንዳለ የጠቆሙት ጃክ ሲለርስ ከአፍሪቃ ኅብረትና ከአረብ ሀገራት በተጨማሪ የጸጥታዉ ምክር ቤት ቋሚ አባላት መካከል ሩሲያም ጠንካራ አቋሟን ማሰማቷን ነዉ የገለጹት። ተንታኞች የአፍሪቃ ኅብረትን ያላካተተዉ ሊቢያን የሚመለከተዉ ዉይይትና ዉሳኔ በዚህ ረገድ ኅብረቱ ሊኖረዉ የሚችለዉን ሚና ዝቅ ማድረግ ይመስላል ቢሉም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ቃል አቀባይ ኑረዲን ሜዝኒ በዚህ አይስማሙም።

«አይመስለኝም፤ የአፍሪቃ ኅብረት ሚና በተመድ ዉሳኔ 19-73ትም ተካቷል። በተለይ ለሰላም ሂደት የኅብረቱን ሚና ይቀበላሉ። በተጨማሪም ሊቢያን በሚመለከት ባለፈዉ መጋቢት 1ቀን በመሪዎች ደረጃ ስብሰባ ማካሄዳችንን መግለፅ እፈልጋለሁ። በዚያን ጊዜም ሊቀመንበር ፒንግን ጨምሮ አምስት የአገር መሪዎችን ያካተተ ኮሚቴ ተመስርቷል። እናም ሰላም ሊሰፍን የሚችልበትን መንገድ የሚያመቻች መርሃ ግብር ዘርግተናል፤ በዚያን ጊዜ ቀዳሚዉ ጉዳያችን አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ነበር። ስለዚህ ከመጀመሪያዉ አንስተን እኛ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ ነዉ ጥረታችን።»

Afrikanische Union
ምስል picture-alliance/ dpa

ኅብረቱ አሁንም ለሊቢያ ቀዉስ ሰላማዊ መፍትሄን እንዳማራጭ ማቅረቡን ቀጥሏል። የዉጭ ሀገራትን የጦር ጣልቃ ገብነትም ተቃዉሟል። በሎንዶን ጉባኤ ባይሳተፍም ከአጋሮች ከሚላቸዉ ጋ ሰላም ለማምጣት መስራቱን እንደሚቀጥል ሜዝኒ ተናግረዋል፤

«ለማንኛዉም የእኛ ስልት በዉሳኔ ተላልፏል ሳይሆን ከስምምነት የተደረሰበት በሎንዶን ጉባኤ ከተሳተፉት አጋሮቻችን ጋ ሰላም የሚገኝበትን መንገድ በጋራ ለማፈላለግ እንሰራለን። ለሊቢያ ቀዉስ የሚሆን ወታደራዊ መፍትሄ የለም።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ