1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሒላሪ ክሊንተን ድል

ረቡዕ፣ ሰኔ 1 2008

ሒላሪ ክሊንተን ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንትነት በሚደረገው ፉክክር የዲሞክራቶቹ ፓርቲ ዕጩ ለመሆን የሚያበቃቸውን ድምጽ አገኙ። ተፎካካሪያቸው በርኒ ሣንደርስ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ የምርጫ ዘመቻችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

https://p.dw.com/p/1J2ga
USA Präsidentschaftskandidatin Hillary Clinton
ምስል Getty Images/AFP/T. A. Clary

[No title]

የዘንድሮው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንታዊ ቅድመ-ምርጫ ረዥም እና ውስብስብ ሆኖ ዘልቋል። እስካሁን በተካሄደ ቅድመ ምርጫ ለዲሞክራቶቹ ፓርቲ ሒላሪ ክሊንተን ለሪፐብሊካኖቹ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ የሚያስችላቸውን ድምጽ አግኝተዋል። የዲሞክራቶቹ ዕጩ ተፎካካሪ ሒላሪ ክሊንተን ፓርቲያቸውን ወክለው ለመወዳደር የሚያስችላቸውን በቂ የውክልና ድምጽ ማግኘታቸው የተረጋገጠው ትናንት ነበር። እናም ድላቸውን በደስታ ለተዋጡ ደጋፊዎቻቸው የገለጡት በኩራት ነበር።

«ሁላችሁንም አመሠግናለሁ። ወሳኝ የሆነ ቦታ ላይ ደርሰናል። በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ሴት ግዙፍ ፓርቲን የምትወክል ዕጩ ትሆናለች።»

የዛሬው ድል የአንድ ሰው ብቻ አይደለም። ይልቁንስ ይኽ ድል እውን እንዲሆን ለዘመናት ለታገሉ ሴቶች እና ወንዶች ነው የሚገባው ሲሉም ሒላሪ ክሊንተን አክለዋል። የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት እመቤት ሴናተር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የዘንድሮ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ተፎካካሪ ሒላሪ ክሊንተን ፣ የሪፐብሊካኖች ብቸኛ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዚዳንትነት «ብቁ አይደሉም» ሲሉም ተናግረዋል።

Bildkombo Hillary Clinton Donald Trump Vorwahlen USA Arizona
ምስል picture-alliance/dpa/Skidmore/

የዲሞክራቶቹ ፓርቲ ሌላኛው ተፎካካሪ በርኒ ሣንደርስ ለሒላሪ ክሊንተን የእንኳን ደስ አለዎ መልእክት አስተላልፈዋል። በሒላሪ ክሊንተን ድል ያልተደሰቱት የሣንደርስ ደጋፊዎቻቸው ግን በወቅቱ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። በርኒ ሣንደርስ በዕጩ ተፎካካሪነታቸውን እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚዘልቁበት ሲያስታውቁ በደጋፊዎቻቸው ሞቅ እና ረዘም ባለ የድጋፍ ጩኸት ታጅበው ነበር።

«የፊታችን ማክሰኞ የዋሽንግተኑ የመጨረሻ የምርጫ ዘመቻ ላይ ትግላችንን እንቀጥላለን።»

በዲሞክራቶቹ ፓርቲ ለዘብተኛ ክንፍ አባላት እና በተለይ በአሜሪካ ወጣቶች ዘንድ እጅግ የሚወደዱት በርኒ ሣንደርስ በቀጣዩ የዋሽንግተን ዲሲው የዲሞክራቶች ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ለማሸነፍም ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። ከዚያም ፊላዴልፊያ እና ፔንሲልቫኒያ ውስጥ በሚደረገው የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የከባቢ አየር ፍትኃዊ አሠራር ክርክር ላይ እንደሚሳተፉ አክለው ገልጠዋል። ለዕጩነት በቂ ድምጽ እንዳገኙ ከወዲሁ ያረጋገጡት ሒላሪ ክሊንተን የበርኒ ሣንደርስ በውድድሩ መግፋት ብዙም ግድ የሰጣቸው አይመስልም።

«ሴናተር ሣንደርስ በዘመቻቸው እና ባከናወኗቸው ጤናማ ክርክሮች ማለትም፦ ገቢን መጨመር፣ ኢ-ፍትኃዊነትን መቀነስ፣ ብሎም የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልን አስመልክቶ ያደረግናቸው ክርክሮች ለዲሞክራሲያዊ ፓርቲያችን እና ለአሜሪካ በጣም ጥሩ ናቸው።»

የሪፐብሊካኖቹ ፓርቲ ብቸኛ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ግን የዲሞክራቶቹ ፓርቲ ደጋፊዎች መከፋፈለን ሊጠቀሙበት የፈለጉ ይመስላል። የሒላሪ ክሊንተን ማሸነፍን የተቃወሙት የበርኒ ሣንደርስ ደጋፊዎችን፦ «እጆቻችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን» ሲሉ ተደምጠዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ