1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕንድና የአፍሪቃ የልማት ትብብር

ረቡዕ፣ ግንቦት 10 2003

ሁለተኛው የሕንዳና የአፍሪቃ መድረክ የመሪዎች ጉባዔ ከፊታችን አርብ አንስቶ ለአንድ ሣምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

https://p.dw.com/p/ROaM
ምስል picture alliance/dpa

ሕንድና አፍሪቃ በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርጉት የልማት ትብብር እያደገ በመሄድ ላይ ያለ ነው። የሁለቱ ወገን የንግድ ልውውጥ ገና ከዛሬው አርባ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋል። ሁለቱ ወገኖች ትብብሩን በማዳበር ወደፊት ለማራመድ ያላቸው ፍላጎትም ከፍተኛ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ከፊታችን አርብ አንስቶ ሁለተኛው የኢንዶ-አፍሪቃ መድረክ የመሪዎች ጉባዔ የሚካሄደውም እንግዲህ በዚሁ መንፈስ ነው።

ታሪካዊ ግምት የተሰጠው የመጀመሪያው የኢንዶ-አፍሪቃ መድረክ የመሪዎች ጉባዔ የተካሄደው ከሶሥት ዓመታት በፊት እ.ጎ.አ. ሚያዚያ 2008 ኒው ዴልሂ ላይ ነበር። በዚሁ ጉባዔ ላይም የልማት ትብብሩን በተለያዩ ዘርፎች ለማራመድ አንድ የተግባር መርህ ዕውን መሆኑ ይታወሣል። ትብብሩ የእርሻ ልማትን፣ ኤነርጂን፣ ንግድን፣ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትን፣ ከቀረጥ ነጻ የሆነ የንግድ ልውውጥንና የሙያ ሥልጠናን፤ በአጠቃላይ መዋቅራዊ ዕድገትን የሚጠቀልል ነው። የሕንድ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በመጪው ሣምንት ሁለተኛ ጉባዔ በተለይም ለአፍሪቃ ሕዝብ የሚጠቅሙ ተጨማሪ ውሎች እንደሚፈረሙም ይጠበቃል።
በነገራችን ላይ በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ሁለተኛውን የመድረክ ጉባዔ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ አዲስ አበባ ለውይይቱ መመረጧ የአፍሪቃ ሕብረት መቀመጫ በመሆኗ ነው። ትብብሩ በአጠቃላይ ምን ይመስላል? ወደፊትስ ከግንኙነቱ ምንድነው ሊጠበቅ የሚችለው? በነዚህና በተያያዙ ጥያቄዎች ላይ በሰሜን ጀርመን ከተማ በሃምቡርግ የእሢያ ጥናት ኢንስቲቲዩት ውስጥ በልማት ዕርዳታ፣ በማሕበራዊና በኤኮኖሚ ፖሊሲ እንዲሁም በፖለቲካ ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ፕሮፌሰር/ዶክተር ዮአሂም ቤትስን ዛሬ አነጋግሬ ነበር። ባለሙያው እንደሚሉት የልማት ተራድኦው ዕርምጃ የሚታይበትና ከሞላ-ጎደል በጎ ግምት የሚሰጠውም ነው።

“አዎን፤ ሽርክናው በጣም እያደገ ነው የመጣው። በሕንድና በአፍሪቃ መንግሥታት መካከል የሚካሄደው ንግድ መጨመር ከወዲሁ ጎልቶ ይታያል። በሁለተኛ ደረጃ ሽርክናው ለአፍሪቃ ሃገራት የመንግሥታዊ የልማት ተራድኦ አዲስ ምንጭም ሆኗል። ሕንድ በተለየ አስተያየት የንግድ ድጋፍም ትሰጣለች። ይህ ደግሞ አፍሪቃ የንግድ ግንኙነቷን ብዙ-ወጥ እንድታደርግ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም። በቀድሞዎቹ ቅኝ-ገዢዎችና ከቅርብ ወዲህም በቻይና ላይ ያለውን ጥገኝነት አለዝቦታል። ይህ ታዲያ ለአፍሪቃና ለሕንድም ጠቃሚ ነገር ነው። ገበያን ያሰፋል፣ ከሕንድ አንጻር የጥሬ ዕቃን በተለይም የኤነርጂና የሌሎች ሚነራሎች ፍላጎትን መሸፈኑንም ያቃልላል። በጥቅሉ ሕንድ በአፍሪቃ ቻይናን ለመፎካከር ባትበቃም እንደ አማራጭ ልትታይ ትችላለች። በወቅቱ ግልጽ እየሆነ በመሄድ ላይ ያለውም ይሄው ነው”

ከሶሥት ዓመታት በፊት ኒውዴልሂ ላይ በመጀመሪያው ዓቢይ ጉባዔ የሰፈነው የተግባር መርህ ሰፊ የልማት ውጥኖችን ይዞ የተነሣ ነበር። እርግጥ የተወሰነ ዕርምጃ መታየቱ አይቅር እንጂ የዕድገቱን አሃዝ በተጨባጭ ማስቀመጡ ፕሮፌሰር ቤትስ እንደሚያስረዱት ቀላል ነገር አይሆንም።

“በዚህ ላይ ትክክለኛ ግምት መስጠቱ እርግጥ የሚያዳግት ነው። ሆኖም ቢቀር ንግዱ መስፋፋቱን ቀደም ብዬ ገልጫለሁ። ውሉን መለስ ብለን ከተመለከትን በወቅቱ የምንታዘበው የንግዱ አሃዝ በአብዛኛው በጥሬ ዕቃዎች ዋጋ ላይ ጥገኛ እንደሆነ ነው። በሕንድና በአፍሪቃ መካከል የሚካሄደው ንግድ በመጀመሪያ ደረጃ ሚዛን የጠበቀ አይደለም። ከአፍሪቃ በኩል በንግድ ልውውጡ ትልቅ ኪሣራ ነው ያለው። ሕንድ በበኩሏ የአፍሪቃ አገሮች ጥሬ ዕቃዎቻቸውን ወደ አለቀ የገበያ ምርትነት እንዲያበቁ ለማጠናከር ደጋግማ ቃል ብትገባም በዚህ በኩል ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። ጥቂት ዕርምጃ ብቻ ነው የተደረገው። ጠንከር ብሎ የሚታይ ነገር ካለ አፍሪቃውያንን በሕንድ ከፍተኛ ተቋማት የማሰልጠኑ ተግባር ነው። የሣይንስና የቴክኒክ ትብብሩም እንዲሁ ትልቅ ዕድገት ይታይበታል። ግን ይህ አፍሪቃውያን አገሮች ከቻይና ጋር ካላቸው በታች መሆኑ መዘንጋት የለበትም”

እርግጥም ቻይና የኤኮኖሚ ተሳትፎን በተመለከተ በአፍሪቃ ዋነኛዋ ሃይል መሆኗ ዛሬ ለማንም የተሰወረ አይደለም። በክፍለ-ዓለሚቱ ያልገባችበት ቀዳዳ አይገኝም። የቻይና የአፍሪቃ ፖሊሲ በብዙ ምክንያቶች በዓለምአቀፍ ደረጃ ሲነቀፍና ሲተች የቆየ ነው። የሕንድስ ግብ ለመሆኑ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል ወይ? እንደ ፕሮፌሰር ቤትስ መሆኑ ያጠራጥራል።

“ብዙም የተለየ የሚሆን አይመስለኝም። የሕንድ መንግሥት የኤነርጂ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ባለበት ግፊት የተነሣ ተባባሪውን ብዙ ሊያማርጥ የሚችል አይደለም። ስለዚህም ቻይናና ሕንድ ዛሬ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ የአፍሪቃ አገሮች መዋዕለ-ነዋይ ሲያደርጉ ነው የሚታዩት። ልዩነታቸው እንግዲህ በጣም ትንሽ ነው። ልዩነት አለ ለማለት የሚቻለው ምናልባት ሕንድ ሽርክናዋን የምታራምደው በአንጻራዊ ዝግታ ነው። ሰውም በገፍ አትልክም። ከዚሁ ሌላ ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር የምታካሂደው ትብብር የተመሠረተው እንደ ቻይናው በመንግሥት ደረጃ ሣይሆን በግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ነው። ይህም እርግጥ የተወሰነ ጠቀሜታ ይኖረዋል”

ከሰሞኑ ጉባዔና ወደፊትስ ምንድነው የሚጠበቀው? ፕሮፌሰር ዮአሂም ቤትስ በበኩላቸው በወቅቱ ግምት መስጠቱ ጥቂት ቢያድግትም የሕንድና የአፍሪቃ ትብብር ወደፊት እየጠነከረ የሚሄድ ለመሆኑ ግን ብዙም አይጠራጠሩም።

“አሁን እንዲህ ነው ብሎ መናገሩ ያዳግታል። ሁሉም ነገር የአፍሪቃ አገሮች በሚያደርጉት ዕርምጃ ላይ ጥገኛ ነው። ሕንድ በበኩሏ ትብብሩን ለማራመድ በምታደርገው ጥረት ይበልጥ ጠንክራ ትቀጥላለች። ከአንዳንድ የምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች ጋር ታሪካዊ ጠንካራ ግንኙነት ሲኖራት ከነዚህ ጋር ትብብሩ ይበልጥ እየተስፋፋ እንደሚሄድ አምናለሁ። ሕንድ በረጅም ጊዜም ለአፍሪቃ አመቺዋ ሸሪክ ናት። ከአፍሪቃ የዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመ መካከለኛ ቴክኖሎጂን ለማቅረብ ተስማሚዋ እንደምትሆን አልጠራጠርም”

የአፍሪቃ አገሮችስ በፊናቸው ግንኙነቱን ለራሳቸው ዕርምጃ በሚገባ ለመጠቀም ምን ማድረግ አለባቸው?

“አዎን፤ አፍሪቃውያን ከሕንድ ወገን ጥሬ ምርቶቻቸውን ወዳለቀ የገበያ ዕቃነት ለመቀየር ይበቁ ዘንድ ድጋፍ እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የኢንዱስትሪ አመራረት ብቃት ሊፈጠር ካልቻለና ምርቱ ለገበያ እንዲበቃ ካልተደረገ የንግድ አስተያየት ብቻውን በቂ አይሆንም። ይህ አሳዛኙ የአፍሪቃ ታሪክ ነው። ልዩ የንግድ አስተያየት ብቻውን እንደማይበቃ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ጋር የተደረጉ ውሎች አሳይተዋል። አፍሪቃ የራሷን ምርቶች ሰርታ በማውጣት ለገበያ እንድታበቃ መደረጉ ግድ ይሆናል ማለት ነው”

ለማንኛውም ሁለተኛው የሕንድና የአፍሪቃ መድረክ ዓቢይ ጉባዔ በበርካታ መሪዎች ንቁ ተሳትፎ የሚካሄድ ሲሆን ቢያንስ የ 16 የአፍሪቃ መንግሥታት ልዑካን የንግድ ተጠሪዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ