1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕንድና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ሽርክና

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1 2000

ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን የኤኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ኒውዴልሂ ላይ ያስተናገደችው ሁለት ቀናት የፈጀ ዓቢይ ጉባዔ ዛሬ ተጠናቋል። ይህን መሰሉ የኢንዶ-አፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ በሁለቱ ወገን ግንኙነት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሲሆን ሕንድ በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ላይ በሰፊው ካተኮረችው ከቻይና ጋር ፉክክሯን የማጠናከሯም ምልክት ነው።

https://p.dw.com/p/E0cH
ምስል AP/DW

ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ 21ኛው ምዕተ-ዓመት የጋራ የኤኮኖሚ ጥቅምን ለማራመድ የእሢያና የአፍሪቃ የትብብር ዘመን መሆኑን እንደሚሹ በጉባዔው ላይ ገልጸዋል። ሕንድ በአፍሪቃ የምትሻው ሽርክና ከቻይናው ምን ያህል ይለያል? አፍሪቃስ ከሕንድ በምታደርገው ትብብር ተጠቃሚ የምትሆነው እንዴት ነው? ሕንድ በአፍሪቃ ብዙ ወጪን የማይጠይቅ አገልግሎት በመስጠትና ቀላል ኢንዱስትሪዎችን በመትከል በአንጻሩ በተፋጠነ ዕድገቷ ሳቢያ እየጨመረ የሄደውን የተፈጥሮ ሃብት ፍላጎቷን ለማሟላት ይበልጥ ተነስታታለች። ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር የምታካሂደው ንግድ በተለይ ባለፉት አምሥት ዓመታት በሰፊው ነው የጨመረው። በ 1991, 967 ሚሊዮን የነበረው ንግድ ዛሬ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
የሕንድና የአፍሪቃ የንግድ ልውውጥ እስከ 1999 ድረስ እንዲያውም ከቻይና የሚበልጥ ነበር። ዛሬ ግን የቻይናው በእጥፍ ገደማ ያመዝናል። የቻይና መዋዕለ ነዋይ አቅርቦት በአፍሪቃ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን ይህም ከሕንድ በአራት ዕጅ የሚበልጥ መሆኑ ነው። እርግጥ አብዛኛው በተፈጥሮ ሃብት ይበልጥ ወደታደሉት ወደ ሱዳን፣ አንጎላና ኮንጎ ነው የፈሰሰው። ቻይና ነዳጅ ዘይት፣ መዳብና ሌሎች ንጥረ-ነገሮችን ለማግኘት ለአፍሪቃ መንግሥታት በቀላል ሁኔታ ብድር ትሰጣለች። ሃቁ ይህ ሲሆን ሕንድ አሁን የምትፈልገው በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎዋን በማጠናከር ከቻይና ጀርባ ሾልካ ለመውጣት ነው።

የቻይና የአፍሪቃ ፖሊሲ ይበልጡን የሚንቀሳቀሰው በንግድ ሲሆን ሕንድ በበኩሏ አፍሪቃን በአቅም ግንባታና በሙያ ብቃት ለማጠናከር ተነስቻለሁ ትላለች።
ለነገሩ የሕንድና የአፍሪቃ ግንኙነት አሁን ከዓመታት በኋላ እንደገና መጠናከር ይያዝ እንጂ የቆየ ታሪክ ያለው ነው። የደቡብ አፍሪቃ ዓለምአቀፍ ጉዳይ ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ሉዊዘ ኮከንቤክ እንደሚሉት በወቅቱ ሽርክናውን ለማዳበር የተያዘው ጥረትም በቆየው ላይ የተመሠረተ ነው። “የጉባዔው ዓላማ ሕንድ ባቀረበችው ሃሣብ መሠረት ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ሽርክና ጥልቅ ማድረግና ማጠናከር ይሆናል። ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር ያላት ግንኙነት የረጅም ጊዜ ታሪክ አለው። አገሪቱ ብዙዎች የነጻነት እንቅስቃሴዎችን ትደግፍ እስከነበበት እስከ ቅኝ-አገዛዙ ዘመን መለስ ይላል። እና ይህ የአሁኑ ቀጣይና ግንኙነቱን በማጥበቁ ላይ ያለመ መሆኑ ነው”

በዕውነትም ሕንድ በሚቀጥሉት ዓመታት ለአፍሪቃ የምትሰጠውን’ ብድር በእጥፍ በመጨመር ወደ 5,4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ታቅዳለች። ባለፉት አምሥት ዓመታት ብድሩ በ 2,1 ቢሊዮን ተወስኖ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሢንግ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት ሕንድ ከአፍሪቃ ጋር በእርሻ ልማት፣ በመዋቅራዊ ግንባታ፣ በትምሕርት፣ በመለስተኛ ኢንዱስትሪ ግንባታና በመረጃ ቴክኖሎጂ ረገድ ለመርዳትና ሽርክናውን ለማራመድ ዝግጁ ናት። በርከት ላሉ የአፍሪቃ አገሮች ምርቶችም ልዩ የገበያ አስተያየት ይደረጋል። እነዚሁ ምርቶች ጥጥ፣ ኮኮ፣ ጥሬ መዳብን፣ ተሰፍተው ያለቁ አልባሣትንና ለኢንዱስትሪ ግልጋሎት የማይውል አልማዝን የሚጠቀልሉ ናችው።
በአፍሪቃ የኢንዱስትሪ ዘመን ጮራን ይፈነጥቃል ተብሎ ተሥፋ የተጣለበት ጉባዔ ከአሁኑ ስኬታማ ነው የተባለው። በኤነርጂና በኤኮኖሚ ዘርፎች የሚደረገውን ትብብር ከፍ እንደሚያደርግ፤ ሁለቱም ወገን ተጠቃሚ እንደሚሆኑም መታመኑ አልቀረም።
“ሕንድ አፍሪቃ በገፍ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ትፈልጋለች። በሌላ በኩል አፍሪቃም ከሽርክናው ተጠቃሚ ነው የምትሆነው። በንግድ፣ በመዋዕለ ነዋይ አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም ድህነትን ለመታገል የሚያስችሉ የልማት ዘርፎች! በአጠቃላይ የሕንድና የአፍሪቃ ሽርክና ሁለቱንም ወገን የሚጠቅም ነው”

እርግጥ የደቡብ አፍሪቃው የዓለምአቀፍ ጉዳይ ጥናት ኢንስቲቲቱት ባልደረባ ኮከንቤክ እንደሚሉት አፍሪቃ ተጠቃሚ እንድትሆን የዕድገት ግቧን መለየቷ ግድ ነው። “አፍሪቃ ከዚህ ግንኙነት እንድትጠቀም ተጨባጭ ሃቋን ማገናዘብ ይኖርባታል። የተፈጥሮ ጸጋዋን መዋቅራዊ ግንባታን ለማራመድ መገልገሏ ግድ ነው። ሕንድ የተፈጥሮ ሃብቱን የምትፈልገውን ያህል አፍሪቃም ይህን ሃብቷን ፍቱን በሆነ መንገድ መጠቀም መቻሏ ወሣኝ ነው የሚሆነው”

ታዲያ አፍሪቃውያን መንግሥታት ይህ ዕውን እንዲሆን በተለይ ቤት ሰራሽ የሆኑ የውስጥ ችግሮቻቸውን ማስወገድ መቻላቸው ወሣኝ ነው። ከቻይና ጋር ባላቸው ግንኙነት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች፤ ለምሳሌ የእርሻ ልማትን ለማስፋፋት የሚገባውን ያህል አድርገዋል ለማለት አይቻልም። የቻይና የአፍሪቃ ፓሊሲ ከቤይጂንግ በኩል ምንም እንኳ አድጎ-ማሳደግ የሚል መርሆ እንዳለው ቢነገርለትም ብዙ ትችትን አስከትሎ ነው የቆየው። አገሪቱ የኤነርጂ ጥሟን ለማርካት በያዘችው ዘመቻ ለሕዝብ ፍላጎት ብዙም ዋጋ አልሰጠችም የሚሉት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። የሕንድም የሽርክና ዒላማ በመሠረቱ በተቀዳሚ የአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ነው።
ግን ከቻይና ለየት ያለ መንገድ ትይዝ ይሆን? ኮከንቤክ እንደሚሉት “ቻይና በመዋዕለ-ነዋይ ፖሊሲዋ የበጎ አስተዳደር ወግ ያሌላቸውን መንግሥታት በመደገፍ ብዙ ስትወቀስ ቆይታለች። ይሁንና ከቻይና ጋር ያለውም ግንኙነት አፍሪቃውያን ለጥቅማቸው መደራደው እንዲማሩ የሚያደርግ ነው። ሕንድን በተመለከተ ሕንድም የቻይናን ያህል አይሁን እንጂ አፍሪቃ ውስጥ ሰፊ የንግድ ተሳትፎ አላት። እና ምናልባት ከሁኔታው በመማር ልትቆጠብ ትችል ይሆናል። ግን እንደገና ልናገር፤ ዋናው ነገር አፍሪቃውያን ከሕንድም ሆነ ከቻይና ጋር ባላቸው ግንኙነት ጥቅማቸውን ነቅተው መከታተላቸው ነው”

ለማንኛውም ግንኙነቱ እያደገ የሚሄድ መሆኑን የሚጠራጠር የለም። የደቡብ-ደቡቡ የኤኮኖሚ ትብብር መስፋፋት ለአፍሪቃ ልማት ጠቃሚ መንኮራኩር እንደሚሆንም በሰፊው ነው የሚታመነው። ሕንድና አፍሪቃ ብቻ ተጣምረው ዛሬ ከዓለም ስድሥት ሚሊያርድ ሕዝብ ሲሶው ናቸው። ግዙፏ ቻይና ስትታከልበትና የአፍሪቃ የሕዝብ ቁጥር በፍጥነት መጨመር ሲታሰብ ደግሞ የወደፊቱ ሰፊ ገበያ የት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። ሁኔታው ለአፍሪቃ ተሥፋ ሰጭ ነው ሊባል ይቻላል። እርግጥ አፍሪቃ ከቻናና ከሕንድ ጋር በያዘችው የንግድ ትብብርና ሽርክና ልማቷን በማፋጠን የሕዝቧን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ሁኔታውን በአግባብ መጠቀም መቻል ይኖርባታል።
መዋቅራዊው ግንባታ፤ የእርሻ ልማት፣ የምግብ ዋስትና፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምሕርትና የዕውቀት ክምችት መጠናከር ለወደፊት ዕድገት መሠረት ናቸው። አፍሪቃ ወደፊት በዓለም ንግድ ላይ የተሻለ ድርሻ እንድታገኝ የደቡብ-ደቡቡ ትብብል መጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አያጠራጥርም። እርግጥ አፍሪቃ ለረባ ልማት በመጀመሪያ የለውጥ መሰናክሎችን በማስወገድ ጥርጊያ ማመቻቸት ይጠበቅባታል። በጎ አስተዳደር እስከጎደለና ሙስና ነግሶ እስከቀጠለ ድረስ ክፍለ-ዓለሚቱ የተፈጥሮ ሃብቷን ለዕድገት ዓላማ ልትጠቀም ትችላለች ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው።