1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የመሰንቆው ሊቅ» ጌታመሳይ አበበ

እሑድ፣ ሚያዝያ 16 2008

«የሽምብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ ሀገሬ» የዛሬ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን «የመሰንቆው ሊቅ» ጌታመሳይ አበበ ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ የባህል ሙዚቃ ጨዋታዎች በግንባር ቀደምትነቱ የሚታወቀዉ ነዉ። ሁለ ገቡ ከያኒ ጌታመሳይ አበበ «የጥበብ ገበሬም » በመባል ይታወቃሉ።

https://p.dw.com/p/1Ib7o
Äthiopien Getamesay Abebe
ጌታመሳይ አበበ መሰንቆዉን አላግባብ ሲነካበት አይወድም ነበር፤ «አዱኛ ቸኮል»ምስል Privat

«የመሰንቆው ሊቅ» ጌታመሳይ አበበ

ረዘም ላለ ዓመታት አብረዋቸዉ የሠሩት የሞያ አጋራቸዉ የዋሽንቱ ንጉስ ዮኃንስ አፈወርቅ ከጌታመሳይ ጋር ሙሉ እድሜያቸዉን አብረዉ እንደሆኑ እንዲህ ገልፀዉልናል።
«የመሰንቆው ሊቅ»፤ ጌታመሳይ አበበ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከአሥር በላይ በሚሆኑ ትያትሮች ላይ ተዉነዋል። የአቤ ጉበኛ «የደካሞች ወጥመድ» ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን «የለውጥ አርበኞች» እና የጌታቸው አብዲ «ስንት አየሁ» ትያትሮች ተጠቃሽ ናቸዉ። ከ38 ዓመታት በላይ በሀገር ፍቅር ትያትር በአገለገሉበት ዘመን ጌታመሳይን በቅርበት በቅርበት ለማወቅ እድሉ እንደነበራቸዉ የነገሩንና በአሁኑ ወቅት የዮድ አቢሲኒያ ሙዚቀኞች መሪ አቶ አዱኛ ቸኮል፤ ጌታመሳይ ሁለገብ ከያኒ መሆናቸዉን በሰፊዉ አጫዉተዉናል።

Äthiopien Getamesay Abebe
«የመሰንቆው ሊቅ» ጌታመሳይ አበበምስል Privat

አንጋፋዉ የዋሽንት ባለሞያ ዮኃንስ አፈወርቅ በበኩላቸዉ ጌታመሳይ አበበ የመሰንቆ ብቻ ሳይሆን የትዝታም ንጉስ ነዉ ሲሉ ነዉ ያስታወስዋቸዉ። አዲስ አበባ ላይ ለአንጋፋዉ ከያኒ ለጌታመሳይ አበበ ባህል ማዕከል የምስጋና ዝግጅት ከተተደረገላቸዉ ከሦስት ቀናት በኋላ ማረፋቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። እንደ ዋሽንት ንጉሱ ዮኃንስ አፈወርቅ በባህል ማዕከል በተዘጋጀዉ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ስርዓት ላይ ጌታመሳይ አበበ በዊልቸር እገዛ ተገኝተው እንደነበርና፤ የካባ፣ የአገር ባሕል ልብስ፣ የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማቶችም እንደተበረከተላቸዉ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና «የመሰንቆው ሊቅ »፤ በገጠማቸው የጭንቅላት ዕጢ ህመም ምክንያት መናገርም፤ መራመድም አይችሉም ነበር፤ በተለይ ከአራት ዓመት ወዲህ በሽታዉ ጠንቶባጠዉ እንደነበር የሞያ አጋሮቻቸዉ ተናግረዋል፡፡

ጌታመሳይ አበበ ቻልርልስ ሱተን የተባለ ታዋቂ አሜሪካዊ ሙዚቀኛን መሰንቆ አጨዋወት አስተምረዋል። በመሰንቆ፤ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮጳና አፍሪቃ በመዟዟር የኢትዮጵያን የባሕል ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቁ አንጋፋ ድምፃዊ፤ የሙዚቃ መሣርያ ተጫዋችና ተዋኝ ነበሩ። ጌታመሳይ አበበ ባለትዳር፤ የአስር ልጆች አባት፤ እንዲሁም 18 የልጅ ልጆችን ያዩ አንጋፋ ከያኒ ነበሩ። ሚያዚያ 8 ቀን 2008ዓ.ም በ 72 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሚያዝያ 9 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈፀመ። የዝግጅት ክፍላችን ለቤተሰብ ዘመድ ወዳጅ ጓደኛ ሁሉ መፅናናትን ይመኛል። የነፍስ ይማር!

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን መከታል ይቻላል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ