1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሰንጠቅ አደጋ በዩክሬን

ዓርብ፣ የካቲት 14 2006

ዩክሬንን ለሶስት ወራት ግድም ያተራመሳት የተቃውሞ ሰልፍ በእዚህ ሳምንት ውስጥ ተባብሶ በመቀጥል ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ሰበብ ሆኖዋል። ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው ተቃዋሚዎች በኃይል ስልጣን ሊይዙ ይጥራሉ ሲሉ ይኮንናሉ። እስካሁን ቢያንስ 77 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1BDat
ምስል picture-alliance/dpa
Kiew Einigung zwischen Regierung und Opposition
ምስል Sergei Supinsky/AFP/Getty Images

«ስትመለከቱኝ የሆነ ነገር ያስፈራኝ እመስላለሁ?» ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪች ነበሩ ከሩስያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የሚንፀባረቅበት ፖለቲካቸው አንድ ቀን ዩክሬይንን ለመበታተን አደጋ ያጋልጥ እንደሆን በዶቸቬለ ተጠይቀው የሰጡት መልስ። ቃለ-መጠይቁ ከአራት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ነበር የተደረገው።

ዛሬ በእርግጥም ዩክሬን የመበታተን አደጋ አጥልቶባታል። በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍል ተቃዋሚ ሰልፈኞች ስልጣኑ በእጃቸው የገባ ይመስላል። የደኅንነቱ ክፍልን ጨምሮ መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶች በቁጥጥራቸው ስር ሆነዋል። በምስራቃዊ እና ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ፣ በአብዛኛው የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ከዩክሬይን የመገንጠል ጥያቄ በተደጋጋሚ እያቀረቡ ነው።

በዩክሬን ከሶስት ወራት ግድም በፊት አንስቶ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቀጥሎ በመዲናዋ ኪዬቭ የአደባባይ ሰልፍ ዕለታዊ ክስተት ከሆነ ሰነባብቷል። ካለፈው ማክሰኞ አንስቶ ደግሞ ተቃውሞው ወደ መገዳደል ተሸጋግሮ ቢያንስ 77 ሰዎች ሲሞቱ፤ አስሩ የፀጥታ ኃይላት መሆናቸው ተዘግቧል። ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በአስቸኳይ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። ፕሬዚዳንቱ ስልጣን መልቀቅ የማይታሰብ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታውቀዋል። የዩክሬይን ጉዳይ ጠበብት እና ጋዜጠኛ ዊንፍሬድ ሽናይደር በአንድ ወቅት ለዶቸቬለ የተናገሩት፦

«ፕሬዚዳንት ያኑኮቪች ስልጣን መልቀቅ አይፈልጉም፣ ምክንያቱም ስልጣናቸውን አጡ ማለት ችሎት ፊት መቅረብ እና ዘብጥያ መውረድ እንደሆነ ነው የሚሰማቸው።»

እጎአ የካቲት 2010 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ያኑኮቪች የመንግሥት መዋቅራቸውን በሩሲያ አምሳል ነው የቀረፁት። የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀድሞ KGB የተሰኘው የስለላ ድርጅት ባልደረባ እንደነበሩ የሚታወስ ነው። እናም በስልጣኑ ዙሪያ የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን እንዳሰባሰቡ ይነገራል። ዩክሬይን ውስጥም ፕሬዚዳንት ያኑኮቪች በተመሳሳይ የምሥራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ሰዎችን በብዛት ወደ ስልጣኑ አስጠግተዋል። 45 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ዩክሬይን በዋናነት በ«ዶኔስክ ጎሣ» አባላት ነው የምትመራው። ፕሬዚዳንቱ፣ ርዕሠ-ብሔሩ፣ ዋና አቃቤ ሕጉ በአጠቃላይ የዶኔስክ ጎሣ አባላት ናቸው።

እምቅ የከርሰ ምድር የድንጋይ ከሰል የታደለችው የዶኔስክ ግዛት ሌላም ታሪክ አላት። ዶኔስክ ውስጥ አደገኛ የሚባለው የወንጀለኞች ቡድን አሁንም ድረስ እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል። ፕሬዚዳንት ያኑኮቪች ራሳቸው በወጣትነት ዘመናቸው በዝርፍያ ወንጀል እና አንባጓሮአስነስተዋል በሚል ሁለት ጊዜ እስር ቤት ተወርውረዋል። ለእዚህም ነው በኪየቭ የነፃነት አደባባይ ሰልፈኞች ሰርክ «ሴካ ሔት» እያሉ የሚጮሁት። «እስረኛው ወጊድልን» እንደማለት ነው።

በዩክሬይን ፕሬዚዳንት ያኑኮቪች ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተቃዋሚዎች ዘብጥያ ተወርውረዋል። የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትም ከምንጊዜው በባሰ ሁናቴ ተጎድቷል። ፕሬዚዳንቱ እና ቤተሰቦቻቸው ግን የዩክሬይንን ሀብት እየተቀራመቱ ነው ሲሉ በርካታ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ይወቅሳሉ። ፎርቤስ እንደተባለው የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን መፅሔት ከሆነ የፕሬዚዳንቱ ወንድ ልጅ አሌክሳንደር ያኑኮቪች 190 ሚሊዮን ሀብት አካብቷል። ሌሎች ምንጮች እንደውም የልጁ ሀብት ግማሽ ቢሊዮን ይጠጋል ይላሉ።


ይህን ሁሉ ውጥንቅጥ በጓዳዋ ሸሽጋ የምትገኘው ዩክሬይን አሁን የመሰነጣጠቅ አደጋ እያንዣበበባት ነው። ያ ከመሆኑ በፊት ግን የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የፖላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዛሬ እንዳስታወቁት የዩክሬይን መንግስት እና ተቃዋሚዎችን ሊያስማማ የሚችል ዕቅድ ተነድፏል። በዕቅዱ መሰረት አዲስ ምርጫ እንዲከናወን እና የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ታቅዷል። በእርግጥ ፕሬዚዳንት ያኑኮቪችና ተቃዋሚዎች በእዚህ ተስማምተው ሀገሪቱን ከመበታተን ይታደጓት ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Ukraine Demonstranten Protestlager auf dem Maidan in Kiew
ምስል picture-alliance/dpa

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ