1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለመስቀል በርካቶች ወደ ጉራጌ ተጉዘዋል

ረቡዕ፣ መስከረም 17 2010

የመስቀል በዓል ዛሬ በክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተከብሮ ውሏል። በዓሉ በደቡብ ክልል የተለያዩ ቦታዎች እና በትግራይ አዲግራት ለየት ባለ መልኩ እንደሚከበር ይታወቃል። ከትውልድ ስፍራቸው ውጭ የሚኖሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ የጉራጌ ተወላጆችም ቤተሰቦቻቸው ወዳሉበት በመጓዝ በዓሉን አብረው ያሳልፋሉ።

https://p.dw.com/p/2kpnT
Meskel Urlaubsort Äthiopien
ምስል DW/R.Kifle

ለመስቀል በርካቶች ወደ ጉራጌ ተጉዘዋል

አዲስ አበባ  ተወልዳ ያደገችው ራሄል ክፍሌ የመስቀል በዓል ሲቃረብ በደቡብ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ወዳለ የገጠር መንደር ትጓዛለች፡፡ የ26 ዓመቷ ወጣት ይህን ልምዷን ላለፉት ስድስት ዓመታት ሳታስታጉል አድርጋለች፡፡ በዚህ ዓመትም እንዳስለመደችው ከሁለት የቤተሰብ አባላት ጋር ሆና አያቷ እና አጎቷ ወደሚገኙበት ቀጣነ መንደር ለቀናት ቆይታለች፡፡ ቤተሰብ መጠየቂያ ስጦታም አልረሳችም፡፡

“አጋጣሚ ስራ ስለነበረኝ ለበዓል የሄድኩት በ14 ነው፡፡ ያለህን ነገር እዚያ ላሉ ልጆችም፣ ለሰፈር ሰውም፣ ለቤተሰቦችህም [የተለያየ ነገር] ይዘህ ትገባለህ፡፡ እኔ ለአያቴ የወሰድኩት ብርድልብስ፣ አንሶላ፣ ትራስ፣ የጉራጌ እናቶች ሻሽ፣ ቡና፣ ጨው፣ ክብሪት በቃ አለ  አይደል ለሴት ጓዳ የሚያስፈልገውን ነገር ይዘህ ትገባለህ፡፡ ያው በባዶም ብትሄድ ያው እነርሱ መግባትህን ነው የሚፈልጉት፡፡ ምርቃት አለ፡፡ ምርቃት ደደረጋል፡፡ በሬ ይገዛል፡፡ የሴቶች ቀን ላይ የጎመን ቀን አለ፡፡ የእርዱ ቀን ደግሞ ወጪውንም ምኑንም ስለሚያወጡ እንደወንዶች ቀን ነው የሚወሰደው” ስትል በዓሉ እንዴት እንዳሳለፈች ትናገራለች፡፡    

Meskel Urlaubsort Äthiopien
ምስል DW/R.Kifle

ራሄል እንደገለጸችው በጉራጌ ተወዳጅ በዓል የሆነው መስቀል በቀናት ተከፋፍሎ ነው የሚከበረው፡፡ የጉራጌ ዞን ባህል፣ ቱሪዝም እና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊው አቶ ፍቅረአለም ከበደ ስለ በዓሉ አከባበር ማብራሪያ አላቸው፡፡ 

ከጉራጌ ዞን በተገኘ መረጃ መሰረት ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ የጉራጌ ተወላጆች በመስቀል እና አረፋ በዓላት ወቅት ወደ አካባቢው ይጎርፋሉ፡፡ እንደ ጉራጌ ሁሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በምትገኘው አዲግራትም በመስቀል በዓል ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ አገር ቤት መግባት ባህል ነው፡፡ በ“ውራይና” የትግርኛ የግል መጽሔት ዘጋቢ የሆነው ነጋ ዘርዑ ከስድስት ዓመት ወዲህ የመስቀል በዓል በአካባቢው በሰፊው በመከበር ላይ ነው ይላል፡፡ በመቀሌም በዚህ ዓመት ለየት ባለ ሁኔታ መከበሩን ያስረዳል፡፡

“አዲግራት ላይ ካቻምና አንድ ትልቅ መስቀል ቀንዳአሮ በተባለ አካባቢ ተተክሏል፡፡ ትላንትናም እዚያ ውያለሁ፡፡ በጣም ብዙ ሰው፣ ብዙ እንግዳ ነበር፡፡ ትላልቅ ባለስልጣኖች ዛሬ እዚያ ነው የዋሉት፡፡ አዲግራት ላይ በጣም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ የመቀሌው ታሪካዊ አመጣጥ አለው ተብሏል፡ እዚህ ጮማአ በተባለ ተራራ ላይ ‘ካሁን በፊት ግማደ መስቀሉ በአጼ ዳዊት ጊዜ ሲመጣ ያረፈበት ነው፣ ከጥንት ጀምሮ እየተከበረ የመጣ ነው’ ስለተባለ 52 ሜትር መስቀል ዘንድሮ በግለሰብ ደረጃ እንዲተከል ተደርጓል፡፡ ከዚያ ትላንትና በ10 ሺህዎች የሚቆጠር የመቀሌ ህዝብ እዚያ ሲያከብረው ውሏል፡፡ ትላልቅ ባለስልጣናት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ባሉበት ሲከበር ውሏል” ሲል በሁለቱ ከተሞች የነበረውን አከባበር ያስረዳል፡፡  

Meskel Urlaubsort Äthiopien
ምስል DW/R.Kifle

በትላንትናው የመቀሌ አከባበር ላይ በጮማኣ ተራራ የእንግዳ ማረፊያ ሎጅ እና ቤተ-መዘክር እንደሚገነባ ቃል መገባቱን ጋዜጠኛው ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ ምስሎች በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ እና ጎንደር አካባቢ በዓሉ በተለይ ደመቅ ብሎ መከበሩን አሳይተዋል፡፡ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ባሌ በዓሉ በደማቁ መከበሩን የአካባቢው ነዋሪ አቶ ኤርሚያስ አስቻለው ገልጸውልናል፡፡ በባሌ ጊኒር የሚኖሩት የህክምና ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ በዓሉን በባሌ ሮቤ ካሉት ቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር 130 ኪሎ ሜትር ተጉዘዋል፡፡   

“ትላንትና ደመራ በመለኮስ በስቴድየም ነው ያከበርነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ከቤተሰብ ጋር እያከበርን ነው፡፡ በጣም ደስ ይላል ዓመት በዓሉ፡፡ ባለፈው ትንሽ ችግር ነበር፡፡ ዘንድሮ የተረጋጋ ነው፡፡ ከተማዋም ህዝቡም የተረጋጋ ነው፡፡ ሰላማዊ ነው እስካሁን ድረስ ያለው ነገር፡፡ ዛሬ ጾም ቢሆንም ትላንት እርድ ነበር፡፡ ጎረቤትም ይጠራራል፡፡ ሙስሊም አለ፤ ህዝበ ክርስቲያንም አለ፤ በጋራ ሆነን ነው የምናከብረው” ብለዋል፡፡  

ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የዶይቼ ቬለ ተከታታዮች በዓሉን እንዴት እንዳከበሩት በዋትስ አፕ አድራሻችን መልዕክቶች አድርሰውናል፡፡ ጅቡቲ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከበረሃው እና ሙቀቱ ጋር እየተገሉም ቢሆን ደመራ ደምረው በዓሉን ለማክበር መሞከራቸውን በፎቶ አስደግፈው በላኩልን መልዕክት ገልጸውልናል፡፡ በዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ያሉ አንድ ተከታታያችንም በከተማይቱ ያሉ በበዓሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ማክበራቸውን ነግረውናል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ